2022-06-17 08:41:34
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።
ሰኔ ፲ 10
እንኳን ለክርስቲያን ወገኖች በዓለሙ ሁሉ ታላቅ ደስታ ለሆነበት መላእክትም በሰማያት ደስ ለተሰኙባት ቀን በዓል (በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘንድ የጣዖት ቤቶች እንዲዘጉ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲከፈቱ ትዕዛዝ ወጥቷልና)፣ ለቅዱሳን ደናግል ደባሞንና ብስጣሞን ለእናታቸው ለቅድስት ሶፍያ ሰማዕታት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ ከእነ ቅድስት ሶፍያ ጋራ ሰማዕትነት ከተቀበሉ ከቅድስት ዮና ከቅዱሳን ዋርስኖፋና አውሎጊስ ከመታሰቢያቸው፣ ከሰማዕት ከቅዱስ አቅሊሞስ፣ ከአባ ነአንና ከይስካ ከዕረፍታቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
በዚች ዕለት ለክርስቲያን ወገኖች በዓለሙ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ መላእክትም በሰማያት ደስ ተሰኙባት። በዚች ቀን እውነተኛ ምዕመን ከሆነ ከንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘንድ የጣዖት ቤቶች እንዲዘጉ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲከፈቱ ትዕዛዝ ወጥቷልና።
ደስታን የተመላች ያች መልእክት ወደ እስክንድርያ ከተማ እንደ ዛሬዋ ቀን በደረሰች ጊዜ ፈጽሞ ደስ ተሰኙ ወደ ግብጽ አውራጃዎችም ሁሉ ላኳት ምዕመናን ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር ከፍ ከፍ ማለት ደስ አላቸው የጣዖታት ቤቶችንም ዘጓቸው አብያተ ክርስቲያናትንም ከፈቱአቸው እንደ ዛሬም በዚች ዕለት ሰኔ 10 ቀን በዓል አደረጉ ይኸውም ቈስጠንጢኖስ በነገሠ በዐሥራ አንድ ዓመቱ ነበር እለእስክድሮስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ነበር። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በእኛ ላይም ይቅርታውና ቸርነቱ ይደረግልን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
ቅዱሳን ደናግል ደባሞንና ብስጣሞን እናታቸው ቅድስት ሶፍያ፦ እንዲህም ሆነ ስሙ ዋርስኖፍ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በወደዱ ጊዜ ሸሽቶ ወደ ናባ አውራጃ እሊህ ደናግል ወዳሉበት ወደ ግሕሙን ደርሶ በዚያ አደረ። በዚያቺም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት "ከዚህ ለምን ትተኛለህ ተነሥተህ ተጋደል ለአንተና ሰማዕት መሆን ለሚሹ ሁሉ አክሊል ተዘጋጅተቀልና አሁንም ተነሥተህ ወደ መኰንኑ ሒድ በፊቱም ቁመህ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመን" አለው። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ራእይን እንዳየ ለቅዱሳን ደናግል ነገራቸው።
ሲነጋም ተነሥተው ከእርሱ ጋራ ወደ መኰንኑ ሔዱ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ታመኑ። መኰንኑም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸውና ወደ ወህኒ ቤት ጨመራቸው ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከቅዱስ ዋርስኖፍ ጋራ ወደ ስንሑር ላካቸው እናታቸውም ትከተላቸው ነበር። መኰንኑም "ለአማልክት ዕጣን ዕጠኑ" አላቸው ባልታዘዙለትም ጊዜ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ አጸናቸው ቊስላቸውንም ፈወሰ።
ከዚህም በኋላ መኰኑኑ ከእርሱ ጋራ ወደ አገረ ፃ ይዞአቸው ሔደ። የጣዖታቱ ካህናትም ጣዖታቱን እንደምትረግም ስለ ቅድስት ደባሞን ነገሩት እንዲሁም ባልጀራዋ ዮና የምትባል ሴት እንዳለች ነገሩት እርሱም ኅብራቸው በየራሱ የሆኑ መልካም ልብሶችን እየሠሩ ለምግባቸው ይሸጡ ነበር የተረፋቸውንም ይመጸውቱ ነበር። መኰንኑም የዮናን ዜና ሰምቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጥ ባለሰይፉን ላከው የሰያፊውም ስም አውሎጊስ ነው። ወደርሷም በቀረበ ጊዜ ፊትዋ እንደ መላእክት ፊት ብርሃንን ተመልቶ አየና ፈራ እርሷንም ወደ መኰንኑ እንዲወስዳት እንጂ እንዳይገድላት የእግዚአብሔር ጸጋ አስገነዘበችው ቤተ ሰቦቿም ተሰናባብተዋት ጸንፋ ከሚባል አገር ወጣች ወደ አገረ ፃ ደርሳም መኰንኑን ተገናኘችው ከቅዱስ ወስኖፍና ከባልንጀሮቹ ጋራ እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ። ሰያፊው አውሎጊስም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነና ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ እንዲሁም እሊያን ቅዱሳት ደናግልንም ራሳቸውን ቈረጧቸው ገድላቸውንም ፈጽመው የድል አክሊልን ተቀበሉ።
ቅድስት ደባሞንን ግን ጽኑዕ ሥቃይ ያሠቃዩአት ዘንድ በመንኰራኵር ላይ ሰቀሉአት። በዚህ ሥቃይም ውስጥ ለብዙ ቀኖች ኖረች የእግዚአብሔር መልአክም ያጸናት ያስችላትና ቊስሎቿን ይፈውሳት ነበር መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገባት በዚያም ጥቂት ቀን ኖረች ወደ ፍርድ ሸንጎም አስቀርቦ "ለአማልክት ሠዊ"" አላት ባልሰማችውም ጊዜ ራሷን እንዲቆርጡ አዘዘ። ራስዋንም ሊቆርጡ ከከተማ ወደ ውጭ በአወጧት ጊዜ ሴቶች ሁሉ እያለቀሱ ከብበዋት ነበር ራስዋንም በሰይፍ ቆረጥዋት እንዲሁም እናቷንና እኅቷን በሰይፍ ቆረጧቸው በመንግሥተ ሰማያትም የድል አክሊል ተቀበለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳት ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይድረስን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 10 ስንክሳር።
+ + +
"ሰላም ለሶፍያ ወለአዋልዲሃ ዲባሞን ወብስጣሞን ዘሳተፋ። ይሰነዓዋ ለስምዕ ምስለ ዋርስኖፋ። እማ ወዮና ዘሀገረ ጸንፋ። እምነ ወዲቅ ኪያየ ይሐቅፋ። ከመ ዕጐሊሃ ተሐቅፍ ዶርሆ በክንፋ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 10።
+ + +
የዕለቱ ምስባክ፦ "ተፈሣሕነ ወተሐሰይነ በኲሉ መዋዕሊነ። ወተፈሣሕነ ህየንተ መዋዕል ዘአሕመምከነ። ወህየንተ ዓመተ አንተ ርኢናሃ ለእኪት"። መዝ 89፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 7፥25-35፣ 1ኛ ዮሐ 1፥4-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 15፥30-36። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 11፥20-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ የዲዮስቆሮስ ወይም የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
183 viewsBereket Damene, 05:41