Get Mystery Box with random crypto!

ባሏም ከዐረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረች ሰይጣንም ግን ቀናባት በመበለት ሴት መነኵሲት ተ | ቤተ ውዳሴ

ባሏም ከዐረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረች ሰይጣንም ግን ቀናባት በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋራ ተነጋገረ እንዲህም አላት "እኔ አዝንልሻለሀለ እራራልሻለሁም ገንዘብሽ ሳያልቅ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅ ትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ ባልሽም መንግሥተ ሰማያት ወርሷል ምጽዋትም አይሻም"። አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት "እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገኛኝ ለእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ ርግቦችና መንጢጦች እንኳ ሌላ ባል አያውቁም በእግዚአብሔር አርያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህ ሊሆን እንዴት ይገባል"። ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት እንዲህም አላት እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ" እርሷም የከበረ የመላኩ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው።

ከዚህም በኋላ ሰኔ ዐሥራ ሁለት የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት ስታዘጋጅ ሳለች ብርሃናዊ መልአክ መስሎ ሰይጣን መጣ "አፎምያ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምዕመን ሚስት ትሆኚ ዘንድ ጌታ አዞሻል ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ እንደ አብርሃምና ያዕቆብ እንደ ዳዊትም እንደእነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገቡ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት" ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ያመጣላት ጀመረ።

ቅድስት አፎምያም መልሳ "አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋራ ወዴት አለ የንጉሥ ጭፍራ የሆነ ሁሉ የንጉሡን ማሕተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድምና" አለችው። ሰይጣንም ይህንን በሰማ ጊዜ መልኩ ተለውጠና አነቃት እርሷም ወደከበረው መልአክ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ጮኸች ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት። ያንንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ ሰይጣኑም ጮኸ "ማረኝ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና" እያለ ለመነው ከዚያም ተወውና አበረረው። የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲህ አላት "ብፅዕት አፎምያ ሆይ ሒደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለዪአለሽና እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል"። ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት ወደ ሰማያትም ዐረገ።

የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋላ ወደ ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ ሁሉ ላከች ወርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ሁሉ አስረከበቻቸው። ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች የከበረ የመላአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንስታ ታቅፋ ሳመችው ያን ጊዜም ሰኔ 12 ቀን በሰላም አረፈች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አፎምያ በጸሎቷ ይማረን የዚህም የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
ቅዱስ እለእስክድሮስ የቅዱስ ሚካኤል በዓል እንዳከበረ፦ የሚከብሩበትም ምክንያት እንዲህ ነው። እስክንድርያ በምትባል ከተማ "አክሊወባጥራ" የተባለች የንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኵራብ ነበርና በየዓመቱ ሰኔ በባተ በዐሥራ ሁለት ቀን በዚያ ምኵራብ ሕዝቡ ተስብስቦ ታላቅ በዓል ያደርጉ ነበር። በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል የሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣዖት ነበርና በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ብዙ ፍሪዳዎችን ያርዱለት ነበር።

አባ እለእስክንድሮስም እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣዖት እንዲህ ሲያደርጉ ኖሩ። ይኸውም ሦስት መቶ ዓመተ ምሕረት ተፈጽሞ በአራተኛው ምዕት ውስጥ ነበር። አባ እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት ስለ ተስፋፋች ያን ጣዖት ሊሠብረው ወድዶ ሳለ ጐስቋሎች ሰዎች ከለከሉት እንዲህም አሉት "እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም"።

አባ እለእስክንድሮስ ግን ገሠጻቸው አስተማራቸውም ስሕተታቸውንም በመግለጥ እንዲህ ብሎ አስተማራቸው "ይህ ጣዖት የማይጎዳና የማይጠቅም ነው እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ ይኸውም ጣዖቱን እንድንሰብረው ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ መልአክ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን። የሚታረዱትም ላሞችና በጎች ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች፣ ለችግረ ኞችም በከበረው መልአክ ስም ምግብ ይሁኑ። እርሱ እግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለሆነ ስለእኛ ይማልዳልና" ይህንንም ብሎ በዚህ በጎ ምክር አስወደዳቸው እነርሱም ታዘዙለት።

ከዚህም በኋላ ያንን ምኵራብ አድሰው በዚህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አደረጉት በዚችም ዕለት ሰኔ12 አከበሩዋት። እርሷም የታወቀች ናት። እስላሞችም እስከ ነገሡበት ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አፈረሱዋት። ይህም በዓል ተሠራ እስከ ዛሬም ጸንቶ ይኖራል። ምንጭ፦ የሰኔ 12 ስንክሳር።

+ + +
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦"ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዓውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታምእሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8 ወይም መዝ 48፥10-11 ። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 24፥30-36 ወይም ማቴ 25፥14-31።

+ + +
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "ሠረገላቲሁ ለእግዚአብሔር ምዕልፊተ አዕላፍ ፍሡሐን። እግዚአብሔር ውስቴቶን በሲና መቅደሱ። ዐረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ፄዋ"። መዝ 67፥11-18። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 3፥14-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥15-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥6-12። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 22፥31-37። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል በዓል፣ የጻድቁ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።