Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን'። ሰኔ ፲ | ቤተ ውዳሴ

"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ሰኔ ፲፪ (12) ቀን።

እንኳን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለሚበር ንሥረ አርያም ለሚባል ውዳሴው እንደ ማር ለጣፈጠ ንዑድ ክቡር ለሆነ ለከበረ ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል በነገዱ ውስጥ በመላእክት ሁሉ ላይ በብዙ ክብር ለተሾመበት፣ የባሕራንን የሞት ደብዳቤ ቀዶ እርሱን ለታላቅ ክብር ላበቃባት ቅድስት አፎምያን ለአዳነበት (ለረዳበት)፣ ቅዱስ እለእስክንድሮስ አንድን ቤተ ጣዖት አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ቅዱስ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት ላከበሩበት ዕለት በዓል፣ ለቅዱስ አስተራኒቆስ ለሚስቱ ቅድስት አፎምያ ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል፣ ለእስክንድርያ ስድስተኛ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮስጦስና ለስልሳ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ቄርሎስ ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

+ + +
የዚህ ሳምንት መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፭ "ወረደ እግዚእነ ውስተ ሲኦል ወይቤሎሙ ለእለ ውስተ ደይን በእንቲአክሙ ተሰቀልኩ ዲበ ዕፅ ወተረግዘ ገቦየ በኵናት አንትሙኒ በዝኒ ኢነሣሕክሙ በእንቲአክሙ ተቀነዋ እደውየ ወእገርየ ወተጸፍዓ መልታሕቴየ፤ አዝ፣ በእንቲአክሙ አስተዩኒ ብሂዓ ከርቤ ቱስሐ ዘምስለ ሐሞት በቅድመ ጲላጦስ ወሊቃነ ካህናት፤ አዝ፣ ናሁ ወሀብኩክሙ ሰንበተ ክርስቲያን ዕረፍተ ትኩንክሙ በእንተ ሚካኤል መልአክ ምክርየ ወጳውሎስ ፍቁርየ ወኵሎሙ ቅዱሳንየ አእኰትዎ ኵሎሙ እለ ውስተ ደይን ወዘንተ ብሂሎ ዐርገ ኢየሱስ ሰማያተ አብሖሙ አሁሆሙ ሀገረ ቅድስት ኢየሩሳሌም አግዓዚት"። ትርጉም፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሲዖል ወረደ በሲዖል ውስጥ ላሉት ነፍሳት ስለእናንተ በእንጨት ላይ ተሰቀልኩ፤ ጎኔን በጦር ተወጋ፤ እናንተን በዚህ አልተመለሳችሁም፤ ስለእናንተ እጆቼና እግሮቼ ተቸነከሩ፤ ጉንጮቹ በጥፊ ተመቱ፤ ስለእናንተ በካህናትና በጲላጦስ ፊት ሐሞትና ከርቤ የተቀላቀለበትን መፃፃ ጠጣሁ፤ የምክሬ ባለሟል ስለሆነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ስለወዳጄ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ስለቅዱሳኖቼ እነሆ ዕረፍት ትሆናችሁ ዘንድ ሰንበተ ክርስቲያንን ሰጠኋችሁ። በሲዖል ውስጥ ላሉት ነፍሳት ሁላቸውም አመሰገኑት ነጻ በምታወጣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አባታቸው ሥልጣን ሰጣቸው ኢየሱስ ይህን ብሎ ወደ ሰማይ ዐረገ።

+ + +
የዕለቱ አንገርጋሪ፦ "አመ ይሰቅልዎ አይሁድ ለእግዚእነ ሚካኤል አርመመ ወገብርኤል ተደመ ፀሓይ ጸልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወሪዶ እመስቀሉ አብርሃ ለኵሉ"። ትርጉም፦ ጌታችንን አይሁድ በሰቀሉት ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ዝም አለ፤ ቅዱስ ገብርኤልም ተደነቀ፤ ፀሓይ ጨለመ ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ከመስቀሉ ወርዶ ለኹሉ አበራ።

+ + +
"ክብረ ሚካኤል ናሁ ተዐውቀ በትሕትናሁ ዐብየ ወልሕቀ ዲበ አእላፍ ዘተሰምየ ሊቀ ዘይትዐፀፍ መብረቀ ይተነብል ጽድቀ"። ትርጉም፦ የሚካኤል ክብረ እነሆ አኹን ታወቀ፤ በትሕናውም ፈጽሞ ላቀ ከፍ ከፍ አለ፤ በአእላፍ ነገደ መላእክት ላይ አለቃን የተባለ መብረቅን የሚጐናፀፍ ርሱ ጽድቅን ይለምናል። ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።

+ + +
በዚች ዕለት እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በነገዱ ውስጥ በላእክት ሁሉ ላይ በብዙ ክብር ሾመው። ይህም የከበረ መልአክ ክብር ይግባውና በጌታችን ፊት ስለ ሰው ልጆችና ስለ ፍጥረቱም ሁሉ ይለምናል ይማልዳል።

መድኃኒታችን በተነሣባትም ቀን ይህ ክብር መልአክ ሚካኤል ከውስጠኛው መጋረጃ ውስጥ ገብቶ በክብር ባለቤት ፊት እንዲህ እያለ ይለምናል "እውነት ስለሆነ ቃል ኪዳንህ በምድር መታሰቢያዬን የሚያደርገውን ትምርልኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ሆይ እኔ አገልጋይህና መልአክተኛህ ከቸርነትህ እለምናለሁ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና"። የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ ብሎ ይመልስለታል "የመንፈሳውያን ሰማያውያን መላእክት አለቃቸው ሚካኤል ሆይ መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ መሸከም እንደሚችል ከሲዖል ሦስት ጊዜ በክንፈሸችህ ተሸክመህ እንድታወጣ እንሆ እኔ አዝዤሃለሁ"። ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት የበዓሉን መታሰቢያ ከሚያደርጉት በክንፎቹ ተሸክሞ የእሳትን ባሕር አሳልፋቸው እነርሱንም ከብቻው ጌታ በቀር የሚቆጥራቸው የለም።

ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ሁሉም ይጠብቀን ዘንድ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይ ዘንድ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ የምድራችንንም ፍሬ ይባክ ዘንድ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻችንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በጤና ይመልሳቸው ዘንድ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና።

የክርስቶስ ወገኖች የሆኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላችነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ12 ስንክሳር።

+ + +
ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን እንደረዳው፦ እግዚአብሔር የሚፈራ አንድ ሰው ነበር እርሱም የከበረ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር። በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ። ይህም እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የቅዱስ የሚካኤልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበር። የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክብር መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛተሰ።

ከዚህም በኋላ ዐረፈና ገንዘው ቀበሩት ሚስቱም ፀንሳ ነበረች የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች "የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ"። ይንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ ከችግርም ዳነች መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው "ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል" ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ። ይህንንም በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመር ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ይጠብቀው ነበር።