2023-04-25 20:47:59
በፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫውን ማረፊያ የወሰኑ የመሪዎቹ ክለቦች የእርስ በእርስ ግጥሚያዎች
አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ ነገ ምሽት ወደ ኢትሀድ አቅንቶ ማንቺስተር ሲቲን የሚገጥምበት ጨዋታ የሊጉ ክብር ማረፊያን የሚጠቁም እንደሚሆን በሰፊው እየተነገረ ይገኛል።
ሲቲ ከመሪው አርሰናል አምስት ነጥቦች አንሶ ሁለተኛ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከሰሜን ለንደኑ ክለብ አንጻር ግን ሁለት ቀሪ መርሀ ግብሮች ይቀሩታል።ከዚህ ቀደም በሁለት ክለቦች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ተደርጎ በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው የሊጉ ማረፊያ የተወሰኑ አምስት አይረሴ የሊጉ ጨዋታዎችን ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ማንቺስተር ዩናይትድ 1995-96
የኬቨን ኪገን ቡድን በሴንት ጀምስ ፓርክ ማንቺስተር ዩናይትድን ያስተናገደበት ግጥሚያ ነበር።
ማክፓይሶቹ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሊጉን መሪነት ከተከታያቸው በእጅጉ በማስፋት የዋንጫ ተስፋቸውን በእጅጉ ማለምለም ይችሉ ነበር።
የቲንሳይዱ ክለብ ከጨዋታው በፊት ከዩናይትድ በአራት ነጥቦችም በልጦ ተቀምጧል።
በዚያ የውድድር ዘመን በሙሉ የኪገን ቡድን በሜዳው ምንም አይነት ሽንፈት አላስተናገደም።
በጨዋታው ዴንማርካዊው ግብ ጠባቂ ፒተር ሽማይክል አስደናቂ ብቃቱን ባሳየበት ጨዋታ የሰር አሌክስ ፌርጉሰን ቡድን በኤሪክ ካንቶና ብቸኛ የሁለተኛ አጋማሽ ጎል ማሸነፍ ቻለ።
ዩናይትድ የነጥብ ልዩነቱን በማጥበብ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የሊጉን ክብር በአራት የውድድር ዘመናት ለሶስተኛ ጊዜ ማሳካት ቻለ።
በዚያ የውድድር ዘመን ፌርጊ በኪገን ላይ የተጫወቱት የአእምሮ ጨዋታም ሁልጊዜም የሚታወስ ነው።
ማንቺስተር ዩናይትድ 0-1 አርሰናል 1997-98
አርሰናል በመጋቢት ወር ወደ ኦልድትራፎርድ ያቀናው ከመሪው የፌርጉሰን ቡድን በዘጠኝ ነጥቦች አንሶ ነው።
ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች ግን ይቀሩት ነበር።
ማርክ ኦቨርማርስ መድፈኞቹ ጣፋጩን ሶስት ነጥብ እንዲያገኙ ያገዘች የማሸነፊያ ጎል ከመረብ አገናኘ።
ፌርጉሰን ከጨዋታው በኋላ ተቀናቃኛቸው ቀሪ ሶስት ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ ከእነሱ በላይ እንደሚሆኑ እንደሚያውቁ ነገር ግን ያንን ማድረግ እንደማይችሉ እና ነጥቦችን እንደሚጥሉ ተናገሩ። ስኮትላንዳዊው ግን ንግግራቸው ስህተት እንደሆነ በስተኋላ ታየ።
የቬንገር ቡድን አጠቃላይ የቀሩትን ተስተካካይ ጨዋታዎች ጨምሮ ስምንቱን በማሸነፍ የሊጉን ክብር አሳካ።
ቼልሲ 2-1 ማቺስተር ዩናይትድ 2007-08
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተደረገው በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር 2008 ነው።
ዩናይትድ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ያቀናው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከነበሩ ሶስት ጨዋታዎች በፊት ነው።
ሁለቱን ክለቦች የለያቸው ደግሞ ሶስት ነጥብ ብቻ ነው።ሰማያዊዮቹ በማይክል ባላክ ጎሎች ታግዘው ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ቻሉ።
ዩናይትድ ከዚያ ጨዋታ ሽንፈት አገግሞ ግን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በሁለት ነጥቦች ብልጫ የሊጉን ዋንጫ አነሳ።
ማንቺስተር ዩናይትድ 1-2 ቼልሲ 2009-10
ቼልሲ ወደ ኦልድትራፎርድ ያቀናው በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2010 ነው።
ቼልሲ ከፌርጉሰን ቡድን በአንድ ነጥብ ብቻ አንሶ ተቀምጦም ነበር።
በአሽሊ ኮል እና ዲዲዬ ድሮግባ አወዛጋቢ የጨዋታ ውጭ ጎል ሰማያዊዮቹ ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ቻሉ።
ቼልሲ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ቀን ዊጋንን ስምንት ለዜሮ በማሸነፍ የሊጉን ክብር ማሳካት ቻለ።
ማንቺስተር ሲቲ 1-0 ማንቺስተር ዩናይትድ 2011-12
ዩናይትድ ወደ ኢትሀድ ያመራው ከጎረቤት ክለቡ በሶስት ነጥቦች ብልጫ ይዞ ነው።
የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ ደግሞ የሚቀረው የሶስት ጨዋታ እድሜ ብቻ ነው።
አቻ መውጣት የፌርጉሰንን ቡድን ትርፋማ የሚያደርግ ነበር ።
ሲቲ በቪንሰንት ኮምፓኒ የግንባር ኳስ ጎል አንድ ለዜሮ ማሸነፍ ቻለ።
በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ቀን በአይረሴው ጨዋታ የሮቤርቶ ማንቺኒ ቡድን በማትዘነጋው የሰርጂዮ አጉዊሮ የጭማሪ ሰአት ጎል ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን ሶስት ለሁለት በማሸነፍ ከአርባ አራት አመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ አነሳ።
Website : www.hattricksportofficial.com
Website : www.bestsportet.com
Facebook : facebook.com/hattricksportofficial
Facebook : facebook.com/bestsportet
Telegram : t.me/bestsportet
Twitter : twitter.com/bestsportet
#ሀትሪክ_ስፖርት_ኦፊሺያል
ስፖርትን እንመግባለን !!
We Feed Sport...
614 viewsYishak Belay, edited 17:47