Get Mystery Box with random crypto!

#በሦስት_ቀን_ጾም_ጸሎት_የሕዝበ_እስራኤላውያን_የሞት_አዋጅ_ተቀለበሰ። ነገሩ እንዲህ ነው :- በ | ዝክረ ብሒለ አበው

#በሦስት_ቀን_ጾም_ጸሎት_የሕዝበ_እስራኤላውያን_የሞት_አዋጅ_ተቀለበሰ።

ነገሩ እንዲህ ነው :-
በፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ ዘመን እስራኤላውያን በምርኮኝነት በፋርስ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ በቤተመንግሥቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፡፡ በግብዣውም ላይ ባለሥልጣኖች፣ ባለሟሎች እና አገልጋዮች ተገኝተው እየበሉ እና እየጠጡ እጅግ በጣም ይደሰቱ ነበር፡፡ ነገር ግን በግብዣው ላይ የንጉሡ ሚስት ንግሥት እስጢን ስላልተገኘች ብዙ ሰዎች አለመኖሯን ይጠይቁ ስለነበር ንጉሡ ንግሥት እስጢን የንግሥት ዘውድ ደፍታ እንዲሁም በከበሩ ጌጣጌጦች አሸብርቃ በፍጥነት ወደ ግብዣው እንድትመጣ ታማኝ አገልጋዮቹን ላከ፡፡ ንግሥት እስጢን ግን በግብዣው ላይ እንደማትገኝ እንቢታዋን በመግለጿ ንጉሥ አርጤክስስ በጣም ተናደደ፡፡

ንጉሡ ከአማካሪዎቹ ጋር በመሆን ብዙ ከመከረ በኋላ እስጢን ንግሥት መሆኗ እንዲቀር እና በምትኳ ንግሥት የምትሆን ሴት እንድትፈለግ ተሰማማ፡፡ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት በፋርስ ይኖሩ የነበሩ መልከመልካም ሴቶች ከየሥፍራው ተሰብስበው ለምርጫ ቀረቡ፡፡ ከእነዚህ መልከመልካም እና ቆንጆ ሴቶች መካከል አስቴር አንዷ ነበረች፡፡ አስቴር በፋርስ በምርኮ ከሚኖሩ እስራኤላውያን መካከል አንዷ ስትሆን እናት እና አባት ስላልነበራት አጎቷ መርዶክዮስ ያሳድጋት ነበር፡፡ አጎቷ መርዶክዮስ የንጉሡን ዓዋጅ እንደሰማ አስቴር በጣም ቆንጆ ሴት ሰለነበረች በንጉሡ እንድትመረጥ አዘጋጃት፡፡ ከዐሥራ ሁለት ወራት ዝግጅት በኋላ ቆነጃጅቱ በንጉሥ አርጤክስስ ፊት ቀረቡ፡፡ ከቆነጃጅቱ መካከል አስቴር በንጉሡ እና በሚያዩአት ሰዎች ሁሉ ፊት ሞገስን በማግኘቷ አንደኛ ሆና ተመረጠች፡፡ ከዛን ዕለት ጀምሮ አስቴር የፋርስ ንግሥት ሆና የንግሥና ዘውድ ደፋች፡፡

ንጉሥ አርጤክስስ ቆንጆዋን እና ተወዳጅ የሆነችውን አስቴርን በማግኙቱ በጣም ተደስቶ ለአስቴር ክብር ታላቅ በዓል አድርጎ ሕዝቡን ጋበዘ፡፡ አስቴር በሰው ሀገር በምርኮ የምትኖር ሴት ስትሆን እግዚአብሔር ሞገስና ውበት ሆኗት የንጉሥ ሚስት ሆነች፡፡ በፋርስ መንግሥት ላይ እግዚአብሔር ንግሥት አድርጎ ሾማት፡፡

በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን በፋርስ መንግሥት ላይ የተሾመ ሐማ የሚባል ባለሥልጣን ነበር፡፡ ሐማ ከፍተኛ ባለሥልጣንና የንጉሥ አርጤክስስ የቅርብ ሰው ሰለነበረ ወደ ቤተመንግሥት ሲገባ እና ሲወጣ ብዙ ሕዝብ ይሰግድለት ነበር፡፡ ነገር ግን የንግሥት አስቴር አጎት መርደክዮስ ለሐማ እንደማይሰግድ እና እይሁዳዊ እንደሆነ የሐማ የቅርብ ሰዎች ክፉ ነገር ስለተናገሩበት ሐማ በጣም ተቆጣ፡፡ ሐማ ንጉሥ አርጤክስስን በውሸት አሳስቶ በፋርስ መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉ አይሁዳውያን ሁሉ እንዲገደሉ በንጉሡ ማኅተም ዓዋጅ እንዲወጣ አደረገ፡፡

ብዙ አይሁዳውያን በሐማ ተንኮልና በዓዋጁ በጣም አዘኑ፡፡ ነገር ግን መርዶክዮስ እግዚብሔር አስቴርን ንግሥት ያደረጋት ለዚህ ቀን እንደሆነ በማመን እና በአስቴር ምክንያት የሞት ዓዋጅ እንደሚቀየር ተስፋ በማድረግ ወደ አስቴር መልእክት ላከ፡፡ ንግሥት አስቴር እና ሕዝቡ ሦስት ቀን እና ሦስት ለሊት በጾም እና በጸሎት እግዚአብሔርን ከጠየቁ በኋላ አስቴር ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ገብታ ሁኔታውን አስረዳችው፡፡ ንጉሡም አስቴር ሰለ ሕዝቧ ያቀረበችውን ልመና እና ምልጃ ተቀብሎ የሐማን ዓዋጅ ሻረ፡፡

ሐማ ንጉሥ አርጤክስስን በሐሰት በማሳሳቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ አይሁድ በንግሥት አስቴር ምክንያት እግዚአብሔር የሞቱን ዓዋጅ በሕይወት እንደየቀረው፣ ሐማም እንደ ተፈረደበት ዜናውን ሲሰሙ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡

በምርኮ ይኖሩ ለነበሩ አይሁዳውያን ንግሥት አስቴርን ከሞት እንዲያመልጡ እግዚአብሔር ምክንያት አድርጓታል በዚህ ትምህርት አውቃችኋል፡፡ ሕዝቡ በፍጹም ልባቸው በመታመን እግዚአብሔርን በጾም እና ጸሎት ተስፋ በማድረጋቸው በአስቴር ልመና እንዲሁም ምልጃ የሞት ዓዋጅ ሊየቀር ችሏል፡፡

ጾም ጸሎታችንን በቸርነቱ ተቀብሎ
የእኛንም የሞት አዋጅ ያርቅልን!!!