Get Mystery Box with random crypto!

40 ያውን የመጀመሪያውን አስር መዝሙር ያደርሳሉ ማለት ነው፡፡ይህን ሁሉ ማድረስ ያልተቻለው ግን የ | ዝክረ ብሒለ አበው

40 ያውን የመጀመሪያውን አስር መዝሙር ያደርሳሉ ማለት ነው፡፡ይህን ሁሉ ማድረስ ያልተቻለው ግን የተወሰኑ መዝሙራትን መርጦ በየእለቱ ያደርሳል፡፡

#2_ውዳሴ_ማርያም
ውዳሴ ማርያም ከተቻለ የሰባቱን ዕለታት ካልተቻለ የእለቱን ማድረስ ተገቢ ነው።የዘወትር ጸሎት ካደረስን በኋላ የዕለቱን ውዳሴ ማርያም አድርሰን ይዌድስዋ መላዕክትን ደግመን ከእመቤታችን በረከት ተሳታፊ መሆን ተገቢ ነው፡፡ በዋልድባ የሚኖሩ መነኮሳት ውዳሴ ማርያም ከቅዳሴ ማርያም ሳያደርሱ ውለው አያድሩም፡፡ በየአብነት ትምህርት ቤቱ የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች እና በየገዳማት ያሉ መነኮሳት ሁሉ ውዳሴ ማርያምን በየዕለቱ ያደርሳሉ፡፡እኛም ከአበው ተምረን ማታ ከመኝታ በፊት ወይም ጠዋት ስንነሳ ይህን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው፡፡

#3_ወንጌል_ዘዮሐንስ
የዮሐንስ ወንጌልን በየምዕራፍ ከፋፍለን በየእለቱ ማንበብ ሌላው ጸሎት ነው፡፡አባቶች ይህንን ጸሎት በየእለቱ እያደረሱ ብዙ ተጠቅመውበታል።

4.ሌሎች_ጸሎታት:-
ውዳሴ አምላክ፣ ሰኔ ጎለጎታ፣ መልክአ ኢየሱስ፣ መልክአ ማርያም ፣ በመዝገበ ጸሎት እንዲሁም በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍት ላይ ያሉትን ሌሎች ጸሎታት፣እንዲሁም ገድላት፣ተአምራትን፣እንደ ችሎታችን በየዕለቱ እናደርሳለን፡፡ቢያንስ ግን ይህ ሁሉ ባይሆንልን ከላይ የጠቀስነውን የመዝሙረ ዳዊትና ፣ውዳሴ ማርያምን ጸሎት ማድረስ ይገባናል፡፡

አጭር ጸሎት በተቻኮልን እና መጻሕፍትን ለማንበብ ጨርሶውን ጊዜ በማይኖረን ሰዓት ይህንን እንድንጸልይ አንዳንድ አባቶች ይመክሩናል።አቡነ ዘበሰማያት፣ጸሎተ ሃይማኖት፣ሰላም ለኪ /ስለ ውዳሴ ማርያም ፈንታ/፣አቡነ ዘመሰማያት፣አንድ ከመዝሙረ ዳዊት/ መዝሙር 150/ በመዝሙረ ዳዊት ፈንታ/በመጨረሻም አቡነ ዘበሰማያት ማድረስ ብንችል መልካም ነው ።ጸሎተ ሃይማኖት የህይማንት መግለጫ በምህኑ እንጸልየዋለን። በመካከል ሰላም ለኪ በመድገማችንም የውዳሴ ማርያም በረከት ይደርሰናል። መዝሙረ ዳዊት 150 ስናደርስ ደግሞ ሁሉንም መዝሙራት የደገምን ያህል ይሆንልንና የዳዊቱን በረከት እናገኛለን፡፡ይህንን ሁሉ ማድረስ ካልተቻለን ግን ቢያንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አቡነ ዘበሰማያት ብለን ከቤታችን ልንወጣ ይገባናል።

አጭር ጸሎት ከሥፍራ ሥፍራ ሊለያይ ይችላል፡;ዘጠኝ ሰላም ለኪ፣አስራ ሁለት አቡነ ዘበሰማያት በገዳማት ያሉ አበው ያደርሳሉ። አጭር ጸሎትን እነደ መደበኛ ማድረግ ለፈተና ያጋልጣል አጭር ጸሎት የምንጸልየው በጣም በተቸገርንበት፣ጊዜ ባጣንበት ሰዓት ነው።ይህንን ጸሎት እንደመደበኛ ይዞ በየእለቱ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ብቻ መድገም ግን ስንፍና እንዳይሆን ያስፈራል።ይልቁንም በክርስትና ሕይወት ጅማሬ ላይ ያሉ ምእመናን/ወጣንያን/ክርስትናውን እስኪላመዱ ጸሎታቸው አጭር ሊሆን ይችላል።እየቆዩ ሲሄዱ ግን በጸሎት እየበረቱ ወደ መደበኛው ጸሎት መድረስ አለባቸው።ሁል ግዜ ወተት መመኘት ሁል ግዜ አልበረታውም እያሉ አጭር ጸሎት እያደረሱ መተኛት ተገቢ አይደለም።ይህ አይነቱ አካሄድ የእግዚአብሔርን ቸርነት ለስንፍና ምክንያት አድርጎ መጠቀምም ነው።

ከዚህ ጋር በቤተክርስቲያን አገልገሎት ላይ ያለንም ዳዊት መድገም ውዳሴ ማርያም ማድረስ ይጠበቅብናል።የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ዲያቆናት፣ቀሳውስት፣ሰባክያነ ወንጌል፣መዘምራን……እነዚህን ጸሎታት መጸለይ ይጠበቅባቸዋል።አልያ ግን እያወቅን ጸሎት ማድረስ እንዳለብን ብዙ ጊዜ ተምረን እንዳልተምርን ቸል ብንል ለፈተና መጋለጥ ይመጣል።ከእግዚአብሔርም ቸርነት እንድንርቅ ያደርገናል።

አቡነ ዘበሰማያት የጸሎታችን መነሻና መድረሻ ጸሎት ስናደርስ የጸሎታችን መነሻ (መጀመሪያ) አቡነ ዘበሰማያት ነው፡፡በመካከል ጸሎት አቋርጠን ከሰው የምንነጋገርበት ጉዳይ ቢገጥመን በአቡነ ዘበሰማያት ማሰር ተገቢ ነው፡፡በአቡነ ዘበሰማያት አስረን የገጠመንን ጉዳይ ፈፅመን እንመለሳለን፡፡ ከዚያም አቡነ ዘበሰማያት ብለን ካቆምንበት እንቀጥላለን።ጸሎታችንን በአቡነ ዘበሰማያት ሳናስር በመሃል እንዳሻን እንዳናቋርጥ አበው ያስተምሩናል፡፡ የማህበር ጸሎት በቤታችን ከምንጸልየው ጸሎት በተጨማሪ በቤተክርስቲያን ተገኝተን ጸሎት ማድረስ ተገቢ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት እንደመሆና በእርሱአ የሚጸለይ ጸሎት ከጸሎታት ሁሉ የላቀ ነው።በካህናት እየተመራ ፣በሕብረት ሆነን የምናደርሰው በመሆኑ ታላቅ ኃይል አለው።እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ የምንጸልየውን ጸሎት እንደሚሰማ ሲያመለክተን እንዲህ በማለት ነግሮናል።”አሁንም በዚህ ሥፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ ፣ጆሮቼም ያደምጣሉ።ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዓይኖቼ እና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።”/2 ዜና መዋ 7-15/ ከዚህ አንጻር በቤተ መቅደስ እየተገኘን መጸለይ ተገቢ ነው።

በሰንበት ቀን ኪዳን ማድረስ ፣ ቅዳሴ ማስቀደስ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ተግባራችን መሆን አለበት።በሰንበት ያለ በቂ ምክንያት ቅዳሴ የሚያስታጉል በቀደሙ አባቶች /አባ ሚካኤል ወአባ ገብረኤል/ቃል መወገዙን የተአምረ ማርያም መቅድም ይነግረናል።ከዚህ ጋር በሰዓታት ፣በማኅሌት ጸሎታት ላይ በመገኘት ቤተ ክርስቲያናችን ካዘጋጀችልን የማይጠገብ ማእድ ልንሳተፍም ይገባናል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሃይማኖታችን ፍጹም ፍቅር የሚኖረን ከእነዚህ ጸሎታት ጋር ስንተዋወቅ ነው።አልያ የእንጀራ ልጅ መሆን ይመጣል።የመናፍቃንን አዳራሽ መናፈቅ ይመጣል። ከላይ በተመለከተው የጸሎት ጊዜ እየተጠቀምን፣የጸሎት ዓይነቶችንም በምትችለው መልኩ እያደረስን፣በቤተ መቅደስ እየተገኘን ኪዳን እያደረስን፣ቅዳሴ እያስቀደስን ከፈጣሪ ጋራ እለት እለት ተነጋገሩ::

ጸሎት ከሌለ መንፈሳዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ከጄነሬተሩ ተቋርጦ ገመዱ ተበጥሶ ብቻውን እንደተንጠለጠለ አምፖል መሆን ይመጣል፡፡ስለዚህ በርቱና ጸልዩ።

ፈጣሪ ለሁላችንም ብርታቱን ያድለን፡፡አሜን