Get Mystery Box with random crypto!

#ጥር_29_የ2015_ዓ_ም_ጾመ_ነነዌ_የሚጀምርበት_ዕለት። እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ጥር_29_የ2015_ዓ_ም_ጾመ_ነነዌ_የሚጀምርበት_ዕለት።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ ወደ ሕዝቡ ከላካቸው ነቢያት መከካል አንዱ ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡
ዮናስ ማለት ርግብ ማለት ነው።
ታዲያ አንድ ቀን ፣ ወደ አንዲት ታላቅ ከተማ ሔዶ እንዲሰብክ የእግዚአብሔር ቃል ለነቢዩ ዮናስ መጣለት፡፡ ይህች ታላቅ ከተማ ነነዌ ትባላለች፡፡ በዚህች በነነዌ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአታቸው እጅግ በዝቶ ነበር፡፡ ርኅሩኁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ ጥፋቱን ስለማይፈልግ ንስሐ ግቡ ብሎ እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን የፈጣሪውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ሊኮበልል አሰበ፡፡ ከዚያም ተርሴስ ወደምትባል አገር የምታልፍ መርከብ አግኝቶ በእርሷ ተሳፈረ፡፡ ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል ወይም መሸሽ አይቻልም።

ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ተሳፍሮ ሲሔድም እግዚአብሔር ታላቅ ነፋስን አምጥቶ በባሕሩ ላይ ታላቅ ማዕበልን አስነሣ፡፡ በዚህ ጊዜ መርከቢቱ ልትሰበር ደረሰች፡፡ ይህ ሁሉ የደረሰው ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ በማሰቡ ነው፡፡ መርከቢቷ ውስጥ ያሉ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ መርከቧ ክብደት ስለበዛባት ነው ብለው አስበው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ዅሉ ወደ ባሕር ቢጥሉትም መርከቢቱ ግን ልትረጋጋ አልቻለችም ነበር፡፡ ማዕበሉም አልቆም አለ፡፡

ይህ ዅሉ ሲኾን ግን ነቢዩ ዮናስ ተኝቶ ነበር፡፡ ከዚያም የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀረበና ‹‹ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደኾነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ›› አለው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ ዕጣ እንጣጣል›› ተባብለው ዕጣ ሲጣጣሉ ዕጣው በነቢዩ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን?›› አሉት፡፡ ነቢዩ ዮናስም ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለሉን በነገራቸው ጊዜ ሰዎቹ በፍርኀት ኾነው ‹‹ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?›› አሉት፡፡ ባሕሩንም ሞገዱ እጅግ ያናውጠው ነበርና ‹‹ባሕሩ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ፡፡ አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፡፡ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤›› አላቸው (ትንቢተ ዮናስ ፩፥፩-፲፫)፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ባሕሩ ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡

ባሕሩ ሲናወጥ የነበረው ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትቶ ለመሸሽ በመርከቡ በመሳፈሩ ነው! እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ ያሰብንበት ቦታ መድረስ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ዓለሙን ዅሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነውና በባሕርም ኾነ በየብስ (በደረቅ መሬት) ብንጓዝ ከእርሱ መሰወር ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ቦታና ከእርሱ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና፡፡

እናም ሰዎቹ ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕር ሲጥሉት እግዚአብሔር ያዘጋጀው ታላቅ ዓሣ ዋጠው፡፡ ነቢዩ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፡፡ ነቢዩ ዮናስም እግዚአብሔር እንዲያወጣው በዓሣው ሆድ ውስጥ ኾኖ አብዝቶ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም የነቢዩ ዮናስን ጸሎት ሰምቶ ዓሣውን እንዲተፋው አዘዘው፡፡ ዓሣውም ነቢዩ ዮናስን በየብስ (በደረቅ መሬት) ላይ ተፋው፡፡ ነቢዩ ዮናስም ‹‹ይህቺ አገር ማን ትባላለች?›› ብሎ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሲጠይቅ አገሪቱ ነነዌ እንደ ኾነች ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔርን ቃል እሺ ብሎ ተቀብሎ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ገብቶ ‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች)›› ብሎ አስተማረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ቃሉን ሰምተው ከኀጢአታቸው ተመልሰው፣ ማቅ ለብሰው ንስሐ ገቡ፡፡ ከከንጉሡ ጀምሮ ሕፃናትም ጭምር፣ እንስሳትም ሳይቀሩ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ፣ ውኀም ሳይጠጡ ለሦስት ቀን ጾሙ፡፡ እንዲምራቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውንና ንስሐ መግባታቸውን አይቶ ይቅር አላቸው፤ ነነዌንም ከጥፋት አዳናት፡፡ ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔርን አልታዘዝም ያለው እኔ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች) ብዬ ባስተምር ሕዝቡ ተጸጽቶ ይቅርታ ቢጠይቁ እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው እኔ ውሸታም ነቢይ እባላለሁ ብሎ ፈርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የነነዌ ሰዎች ነቢዩ ዮናስንም ውሸታም ነው አላሉትም፡፡ ትምህርቱን ተቀብለው ከጥፋት በመዳናቸው እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል ሩኅሩኅና ቸር እንደኾነ በዚህ ታሪክ እንረዳለን።
ምንም እንኳን እኛ ብንበድለውም፣ ብናሳዝነውም ተጸጽተን ንስሐ ከገባን የቀደመውን በደላችንን ደምስሶ ኀጢአታቻንን ይቅር ይለናል፡፡

ነነዌ ከመቶ ሃያ ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡ እነኚህ ዅሉ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ ኖሮ ነነዌን እሳት ይበላት ነበር፡፡ የነነዌ ሰዎች ከበደላቸው ተጸጽተው፣ ንስሐ ገብተው በመጾማቸውና በመጸለያቸው እግዚአብሔር ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡
እኛም ዛሬ እግዚአብሔርን በድለነዋል እርሱ የማይወደውንም ክፋት ፈጽመናል። ስለዚህ እንደ ነነዌ ሰዎች ተጽጽተን ንስሐ ከገባን አምላካችን ቸር፣ ታጋሽ እና ይቅር ባይ አምላክ ስለኾነ ኀጢአታችንን ይቅር ብሎ ከጥፋት ያድነናል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ጾመ ነነዌን የምንጾመውም እግዚአብሔር ኀጢአታቻንን ይቅር እንዲለን ነው፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡