Get Mystery Box with random crypto!

#ሐ_የዕዳ_ደብዳቤያችንን_ይደመስስ_ዘንድ #3_ጥምቀት_ለምን_በውኃ_ሆነ? ጌታችንና መድኃኒታችን | ዝክረ ብሒለ አበው

#ሐ_የዕዳ_ደብዳቤያችንን_ይደመስስ_ዘንድ

#3_ጥምቀት_ለምን_በውኃ_ሆነ? ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እንድንጠመቅ የታዘዝነው በውኃ ነው ለምን በውኃ ሆነ ጌታችን ጌትነቱን ለመግለጽ ለምን በወተት ፣ በማር አልተጠመቀም? እኛስ ለምን በውኃ እንጠመቃለን፣ በማር በወተት ለምን አለደረገውም ቢሉ በኖኅ ዘመን ፍጥረት ሁሉ በውኃ ጠፍቶ ነበር ከዚህም የተነሣ ውኃ ለመዓት እንደተፈጠረ ይታሰብ ነበር። ዳሩ ግን ውኃ ለምሕረትና ለድኅነት የተፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ጌታም ጥምቀቱን በውኃ አድርጓል።

ማርና ወተት በማንኛውም ሰው ቤት አይገኙም ውኃ ግን በሁሉም ቤት ይገኛል። ጥምቀት በማር ወይንም በወተት አንዲሆን ቢደረግ ኖሮ ድኅነት ለሀብታሞች ብቻ በሆነ ነበር። በሁሉም ቤት በሚገኘው ውኃ በማድረጉ ጥምቀት ለሀብታም ለድሀ ሳይባል ለሁሉም እኩሉ እንዲደርስ መደረጉን እንረዳለን። ሌሎች ፈሳሾች አትክልት ላይ ቢያፈሱአቸው አትክልቱን ያደርቃሉ እንጂ አያለመልሙም። ውኃ ግን ያለመልማል እናንተም በውኃ ብትጠመቁ ልምላሜ ሥጋ ልምላሜ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል ነው።

ማርና ወተት ልብስ ቢያጥቡባቸው እድፍ አያጠሩም ውኃ ግን ያጠራል። ከኃጢያት እድፍ በውኃ ተጠምቃችሁ ትጠራላችሁ ለማለት። ውኃ መልክን ያሳያል እናንተም በውኃ ብትጠመቁ የሥላሴን መልክ በመንፈስ ታያላችሁ ሲል ነው። ውኃ እሳትን ያጠፋል እናንተም በውኃ ተጠምቃችሁ የልጅነት ጸጋ ካገኛችሁ ከገሃነም እሳት ትድናላችሁ ሲል ነው። ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርሳል ጥምቀትም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ተዳርሷል ። ባጠቃላይ የጌታችን መድኃኒታችን ጥምቀት በዓል ከዘጠኙ ዓበይት የጌታችን በዓላት አንዱ ነው። በጥምቀት ልጅነት አግኝተናል።

አንዳንዶች በየዓመቱ የምናከብረው ጥምቀት እና በካህናት የተባረከ ውሃ መረጨታችንን እያዩ በየዓመቱ የምንጠመቅ የሚመስላቸው አሉ። ሆኖም የልጅነት ጥምቀት አንዴ የምትፈፀም ነች። ጥምቀት ከማይደገሙ ምስጢራት ውስጥ ነው። ስለሆነም ወንድ በአርባ፣ ሴት በሰማንያ ቀኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ አንዴ ልጅነት ያገኛሉ ወይንም እኛ ሁላችን አግኝተናል። በየዓመቱ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ጌታችን የሰራልንን አምላካዊ ሥራ የምናደንቅበት እና የምናከብርበት፣ በማክበራችንም የምንባረክባት ቀን ነው።

ልዑል እግዚአብሔር ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል።