Get Mystery Box with random crypto!

#ኅዳር_23_ዕረፍቱ_ለነቢዩ_አብድዩ “አብድዩ” ማለት “ገብረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር አገ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ኅዳር_23_ዕረፍቱ_ለነቢዩ_አብድዩ

“አብድዩ” ማለት “ገብረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር አገልጋይ” ማለት ነው፡፡ ይኽ ስም በዘመኑ የታወቀ ስም ነበር፡፡

ነቢዩ አብድዩ ነገዱ ከነገደ ኤፍሬም ሲኾን አባቱ አኪላ እናቱም ሳፍጣ እንደሚባሉ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ ነቢዩ አብድዩ የአክአብ ቢትወደድ ነበር፡፡ ኤልዛቤል ነቢያት ካህናትን ስታስፈጃቸው ኃምሳውን በአንድ ዋሻ ኃምሳውን በአንድ ዋሻ አድርጐ ልብስ ቀለብ እየሰጠ ይረዳቸው የነበረውም ይኸው ነቢይ ነው /1ኛ ነገ.18፡ 3-13/፡፡

አክዓብ ሞቶ አካዝያስ ከነገሠ በኋላም አብድዩ ቢትወደድ ኾኖ ኖሯል፡፡ ነቢዩ አብድዩ ከጨዋነት ወደ ነቢይነት የተመለሰው በነቢዩ ኤልያስ አማካኝነት ነው፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ 1 ከቊጥር 13 ላይ የተጠቀሰውና ንጉሥ አካዝያስ የላከው ሦስተኛው አለቃም ይኸው አብድዩ ነው፡፡

በነቢዩ አብድዩ የተጻፈው ትንቢተ አብድዩ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በጣም ትንሿና 21 ቊጥሮችን ብቻ የያዘች ባለ 1 ምዕራፍ መጽሐፍ ነች፡፡ ነገር ግን ትንሽ ስለኾነች እግዚአብሔር ወደ እኛ እንዳትደርስ አላደረጋትም፡፡

ነቢዩ አብድዩ መቶውን የእግዚአብሔርን ነቢያት ገንዘቡን ሃብትና ንብረቱን ጨርሶ ተበድሮም ክፉውን ዘመን ካሻገራቸው በኋላ ብድሩን ሳይከፍል ኅዳር 23 አረፈ።

አበዳሪው ባለጸጋ የነቢዩ አብድዩን ቤተሰብ ብድሩን እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ በመምጣት አስጨነቃቸው ባለቤቱ ብድሩን ለመክፈል ሁሉንም የቤቷን ዕቃ ከዘይት ማሰሮ በስተቀር ሽጣ ግማሹን እንኳ መክፈል አቃታት።  ዘመድ አዝማዷንም ጠይቃ ብድሩን መክፈል የምትችልበትን ገንዘብ ማግኘት አልቻለችም።

አበዳሪው ግን ልጆቿን በባርነት መውሰድ የሚችልበትን ማረጋገጫ ከሃገረ ገዢው ዘንድ ተቀብሎ የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ከተታት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ልጆቿ በባርነት ሊወሰዱባት ስለሆነ ጽኑዕ በሆነ ሃዘን ውስጥ ሆና “የአብርሃም የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ስለ ባለቤቴ መልካም ስራ ብለህ እባክህ እርዳኝ” እያለች አምላኳን ተማጸነች።

የለመኑትን የማይነሳ ውለታን የማይረሳ አምላክ እግዚአብሔር ከጭንቀቷ ያወጣት ዘንድ ነቢዩ ኤልሳዕን ላከላት። እርሷም ወደ ቅዱስ ኤልሳዕ "ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል" ብላ ጮኸች። ነቢዩ ኤልሳዕም "አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም  "ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም" አለች።  እርሱም "ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ" አለ።
ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ያላትን ሁሉ አድርጋ በተአምራት ማድጋዎቹ በዘይት ተሞሉ። " መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም  "ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ" አላት።  (2ኛ ነገ. 4:7)

ይህ የነቢዩ አብድዩ መልካምነት ከእርሱ አልፎ ለልጆቹ ተርፎ ከጭንቀትና ከባርነት ሊያወጣቸው ችሏል።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ጸሎት ይማረን !!! አሜን