Get Mystery Box with random crypto!

#ጥቅምት_28_ከተስዓቱ_ቅዱሳን_አንዱ_የአባ_ይምዓታ_ዕረፍታቸው ነው:: =>ጻድቁ አባ ይምዓታ ሃገ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ጥቅምት_28_ከተስዓቱ_ቅዱሳን_አንዱ_የአባ_ይምዓታ_ዕረፍታቸው ነው::

=>ጻድቁ አባ ይምዓታ ሃገራቸው የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ነው::

ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ::
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና 3.ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አባ ይምዓታን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ "ቤተ ቀጢን" ትባላለች:: አባ ይምዓታና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቁዋንቁዋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ ይምዓታ እንደ ገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ ይምዓታ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

የነ አባ ይምዓታ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::
*ዸንጠሌዎን በጾማዕት::
*ገሪማ በመደራ::
*ሊቃኖስ በቆናጽል::
*አረጋዊ በዳሞ::
*ጽሕማ በጸድያ::
*ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::

*አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

ጻድቁ ወደ ቦታው ሲሔዱ ወንዝ (ባሕር) ተከፍሎላቸዋል:: ወደ ቦታው ደርሰውም ገዳም አንጸዋል:: በቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠርተው በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል:: የአቡነ ይምዓታ ገዳም ገርዓልታ እንደምናየው እጅግ ድንቅና ማራኪ ነው:: ገዳሙ ከባሕር ወለል በላይ በ2300 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ያለበት የተራራው ርዝመት ብቻውን 300 ሜትር ነው::

ቤተ መቅደሱ በር ላይ ለመድረስ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ ተራራውን እንደዝንጀሮ በእጅ እየቧጠጡ መውጣት ይጠይቃል:: እርሱም ቢሆን በገዳሙ አባቶች እገዛና ድጋፍ ነው::

ቤተ መቅደሱ እጅግ የሚደንቀው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ብቻ አይደለም ውስጡ ያሉት የግድግዳ ላይ ሥዕሎችም በ6ኛው መ/ክ/ ዘመን የተሣሉ እጅግ ድንቅና ጥንታዊ ናቸው::

ጻድቁ በዚሁ ራሳቸው ባቀኑት ገዳመ ገርአልታ ለዘመናት ተጋድለው ጥቅምት 28 ቀን ዐርፈዋል::