Get Mystery Box with random crypto!

#ጥቅምት_27_የመድኃኔዓለም_ክርስቶስ_የስቅለቱ_መታሰቢያ_በዓል_ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ጥቅምት_27_የመድኃኔዓለም_ክርስቶስ_የስቅለቱ_መታሰቢያ_በዓል_ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት በሰው ባህርይ ተገለጠ ፥ በዓለም በሰዎች መካከል ተመላለሰ ፥ ዓለም ከጥፋት ይድን ዘንድ ዓለሙ የሚድነበትን ሁሉ ሠራ፥ አስተማረም ። ዓለም የሚድነውም በአንድ በራሱ በእግዚአብሔር ልጅ መሥዋዕትነት ነበረ ። ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ በመስቀል ላይ እስከ አቀረበባት ዕለት ድረስ ፥ ብዙ ሠርቶአል፥ አስተምሯል ፥ ተናግሯልም።

በመስቀል ላይ ሁኖ (ተቸንክሮ) የተናገራቸው ቃላተ ርኅራኄ ሰባት ናቸው ። እነርሱም:-

1. " አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው"

መላእክት በቀትር ፈጣሪያቸውን ሊያመሰግኑ ሲመጡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁቱን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ፊቱ ደም ለብሶ ሲያዩት ደንግጠው እንደ ሻሽ ተነጸፉ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ ከዚህ በኋላ መልአኩ ሚካኤል ዝም ሲል መልአኩ ገብርኤል ግን በጣም ተበሳጭቶ አይሁድን በሰይፍ ሊያጠፋቸው ሰይፉን አነሣ የዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱን ተዋቸው አታጥፋቸው የሚሠሩትን እና የሚደርጉትን ስለማያውቁ ነው ብሎታል፡፡ ገብርኤል ግን የአንተ ቸርነት አያልቅም ብሎ ተቆጥቶ ሰይፉን ወረወረው ሰይፉም የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለሁለት ከፍሎ ወደ መሬት ገባ እስካሁንም ድረስ ወደታች ሲሄድ ይኖራል፡፡ በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ  "እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ" ተብሎ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ አገኘ (ኢሳ.53:12)።

2."አምላኬ አምላኬ ሆይ ስለምን ተውከኝ?"

ጌታችን ይህን የተናገረበት ምክንያት አንደኛ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ስላቀረበላቸው ምእመናን ተገብቶ ነው ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው (ዮሐ 17:11) ብሎ ያቀረበውን ያስቧል። አንድም በመዝሙረ ዳዊት 22:1 የተጠቀሰውን ትንቢት አይሁድ ስለሚያውቁ ፥ መሲሕ ክርስቶስ መሆኑንና ትንቢት መፈጸሙን መግለጡ ነው ።
ሁለተኛ ለአቅርቦተ ሰይጣን ነው ። ሰይጣንም ይህንን ቃል ከጌታችን ሰምቶ መሲሑ ክርስቶስ መስሎኝ ነበር እሩቅ ብእሲ ነው ብሎ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ለመውሰድ ሲቀርብ በእሳት አውታር ወጥሮ ኃይሉን አጥፍቶ በነፍሳት ላይ ያለው ሥልጣኑን ገፎ ጥሎታል ።
መናፍቃን ግን አብ በልጁ ስለ ጨከነበት፥ ፊቱን ስለ አዞረበትና ስለ ተወው ጸሎት ማሰማቱ ነው ይላሉ ።

3. "ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ"

ከጌታ ጋር 2 ወንበዴ ሽፍቶች አብረው ተሰቅለው ነበር፡፡ አንደኛው በቀኝ ያለው ጥጦስ በሰማይ 3 በምድር 4 ተአምራት ሲደረጉ አይቶ "ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እያለ ሲጸልይ ጌታ ወደ የማናይ አንገቱን ዘንበል አድርጎ "ግብጽ ስንወርድ የነገርሁህ ሁሉ ደረሰ" አለው፡፡ "ስለዚህ ከሞቴ በቀር የቀረኝ የለምና አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ" ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶት አዳምን ቀድሞ ገነት ግብቷል፡፡
መናፍቃን ይህን ሥልጣኑን ባለመገንዘብ ዛሬም አብን / ወደ አብ እየለመነ ያማልደናል ይሉናል።

 4."እነሆ ልጅሽ ፥ እነኋት እናትህ"
 ጌታችን የተሰቀለ ዕለት እመቤታችን በከተማው ውላ ነበርና ጌታችን ዮሐንስን ጠርቶ እናቴን ጥራልኝ መከራየን ትመልከት አለው፡፡ ዮሐንስም ሄዶ እመቤታችንን እነሆ ልጅሽን ሰቀሉት ሲላት እርሷም ደንግጣ በሐዘን እያለቀሰች እየወደቀች እየተነሣች ከተሰቀለበት ቦታ ደርሳለች፡፡ በዚያም ራቁቱን ተሰቅሎ ስታይ ምርር ብላ አለቀሰች መልአኩ ጌታን ትወልጃለሽ ብሎ ያበሰረኝ ብሥራት ሞት ሆኖ በገደለኝ ነበር እያለች አለቀሰች፡፡ ጌታም እናቴ ሆይ ብታለቅሽ ብታለቅሽ አይታክትሽምን እኔ ካልሞትሁላቸው 5500 ዘመን በዲያብሎስ ቁራኝነት የተያዙ ነፍሳት አይድኑም ዛሬ መከራው ሐዘኑ እንደበዛብሽ ነገ ዘመዶችሽ ብርሃን ለብሰው ከሲዖል ሲወጡ ስታዪ ደስታሽ ይበዛልና ተዪ አታልቅሽ አላት፡፡ የታመመ ሰው ልጄን ሚስቴን አደራ እንዲል እንዲሁ ጌታም እናት ትሆነው ዘንድ እርሱም ልጅ ይሆናት ዘንድ ለዮሐንስ አደራ ብሎታል፡፡ ይህን ቃል የተናገረው ለዚሁ ነው፡፡
ምእመናንንም ለቅድስት ድንግል ማርያም የአደራ ልጆች ፥ ድንግል ማርያምንም ለምዕመናን የአደራ እናት አድርጎ ሰጠ ። ይህም ለእመቤታችን ከአንድ ልጅዋና ከደቀ መዛሙርቱ በቀር ምንም ዘመድና ረዳት እንዳልነበራት ያስረዳል ። መናፍቃን ግን ሌሎች ልጆች ወልዳለች ፤ ለዮሐንስም እንዲንከባከባት ተሰጠች እንጂ ለምእመናን አልተሰጠችም ብለው ክህደትን ያስተምራሉ።

5. "#ተጠማሁ" 
ሲላቸው ወሃቤ ማየ ሕይወት ለሆነው ክርስቶስ አይሁድ መጣጣ አቀመሱት። ይህም የሆነው "በመብሌ ሐሞት ጨመሩ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ (መዝ 69:21) ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው ። አንድም ከሰው ልጅ ምግባር ፈልጌ አጣሁ ሲል ነው ።

6."#አባት_ሆይ_ነፍሴን_በእጅህ_አደራ_እሰጣለሁ"
ብሎ በራሱ ሥልጣን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው የለየበት ቃል ነው (ዮሐ 10:11-17 ተመልከት) ። በዘመነ ኦሪት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ነፍስ ከሥጋቸው እየተለየች ሲዖል ትወርድ ነበር አሁን ጌታ ከተሰቀለ በኋላ ግን ገነት ይገቡ ጀመር፡፡ ስለዚህ ነፍሳችን እንደ ኦሪቱ ሲዖል ብቻ ሳይሆን ገነት መንግሥተ ሰማያትም እንደምትገባ ሲናገር ነው፡፡ አንድም አዳምን ተቀድሞ ጥጦስ ገነትን በደመ ማኅተሙ ከፍቶ ገብቷልና ገነት መግባት መጀመሩን ያሳያል፡፡

7. "ሁሉ ተፈጸመ"
ተፈጸመ ብሎ የተናገረው የመጨረሻው ቃል ነው ። አምላክ የመጣበት የድኅነት ሥራ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ሥጋውን በመቁረስ እንደፈጸመው እንደደመደመው ሲናገር ነው፡፡ በመጻሕት የተጻፈው በነቢያት የተነገረው ሁሉ ደረሰ ሁሉ ነገር ተፈጸመ ሲል ነው፡፡

እነዚህን ሰባቱን የርኅራኄ ቃላትን መጋቢት 27 ዕለት በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡

#ምስጋና_ይሁን_ለአብ_ምስጋና_ይሁን_ለወልድ_ምስጋና_ይሁን_ለመንፈስ_ቅዱስ፡፡ አሜን!!!