Get Mystery Box with random crypto!

#መስከረም_26_አስቸጋሪው_ወርሃ_ክረምት_አልቆ_አስደሳቹ_ወርሃ_ጽጌ_ይጀምራል። ሕፃኑን እና እናቱ | ዝክረ ብሒለ አበው

#መስከረም_26_አስቸጋሪው_ወርሃ_ክረምት_አልቆ_አስደሳቹ_ወርሃ_ጽጌ_ይጀምራል።

ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሸሽ፡፡” (ማቴ 2፣13)

ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከመስከረም 26 - ኅዳር 6 ያለውን ወቅት ዘመነ ጽጌ ትለዋለች፡፡ /የአበባ ወራት ማለት ነው፡፡/ አበቦች በምድር ላይ የሚያብቡበት ወቅት ስለሆነ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

በአርባው ቀናት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እቅፍ እና ጀርባ ሆኖ፣ በዮሴፍ መሪነት ከምድረ እስራኤል ወደ ግብጽ መሰደዳቸው ይታሰባል፡፡ በዛሬው ትምህርታችን የስደቱን ታሪክ እና በቤተ ክርስቲያን ለስደቱ መታሰቢያ የሰየመችውን ወቅት ከሥርዓቱ ጋር እንማራለን፡፡

1.#የስደቱ_ምክንያት፡- ጌታችን በተወለደ በሁለተኛው ዓመት ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከብን በምሥራቅ Aይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡” (ማቴ 2÷2) በዚህም ንጉሡ እና ኢየሩሳሌም ታወኩ፡፡ በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበረው ንጉሥም ሄሮድስ ይባላል፡፡ የካህናት አለቆችን፤ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠይቆ፤ ሰብአ ሰገልን ጠርቶ ሲመለሱ መንገዳቸውን በእርሱ በኩል አድርገው፤ ‹‹እርሱም እንድሰግድለት ንገሩኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ቤተልሔም ሄደው በበረት የተወለደውን ጌታችንን አግኝተውት ፣ ሰግደው ፣ ስጦታ አቅርበው ፣ ሲመለሱ ÷ በሕልም ሄሮድስ ሊገድለው እንደሚፈልገው በሕልማቸው ተገለጠላቸውና በሌላ መንገድ ሄዱ፡፡ ሄሮድስ የመግደል ሐሳቡ እንዳልተሳካለት ሲያውቅ ሁለት ዓመት የሞላቸውን ሕፃናት በሙሉ ሰብስቦ አስገደለ፡፡

2. #ስደት ፡- በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ሕፃኑን እና እናቱን ይዞ ፤ ወደ ግብጽ እንዲሸሽ ነገረው ፡፡ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው ፡፡ ሄሮድስም እስኪሞት ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በዚያ ተቀመጡ፡፡ የበረሐው ሙቀት÷የውኃ ጥም እና የሄሮድስ ወታደሮች ክትትል ለሰብአዊ አእምሮ ከባድ ፈታናዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሄሮድስ ከነጥፋቱ ሞተ፡፡

3. #የስደቱ መታሰቢያ በቤተ ክርስቲያን፡- በቤተ ክርስቲያን ይህ የስደት ወቅት በየዓመቱ ይታሰባል፡፡ የስደቱ መታሰቢያ ወቅት በቅዱስ ያሬድ ዘመነ ጽጌ ይባላል ፡፡ ይህ ወቅት ከመስከረም 26 - ኀዳር 6 ቀን ሲሆን በምድር ላይ የሚገለጡት አበቦችን ለማመልከት የተሰጠው ስያሜ እና በዚህም ዘመናትን ለሚመግብ ጌታ ለእግዚአብሔር ምሥጋና የሚቀርብበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ማሕሌተ ጽጌ እና ሰቆቃወ ድንግል የተባሉ መጻሕፍት በዜማና በንባብ ይደረሳሉ፡፡

#ማሕሌት:- (ምስጋና ማለት ነው፡፡) መዘምራን በቤተ ክርስቲያን በቀን እና በሌሊት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ምስጋና ነው ፡፡ በዘመነ ጽጌ የጌታችንን ስደት የሚያመለክቱ ዜማዎች ይቀርባሉ፡፡

#ማሕሌተ_ጽጌ:- በቁሙ የጽጌ ምስጋና ማለት ሲሆን የጌታችንን እና የእመቤታችንን ስደት አስመልክቶ በአባ ጽጌ ድንግል የተደረሰ በያሬድ ዜማ የሚቀርብ ምስጋና ነው፡፡

#ሰቆቃወ_ድንግል:- (የድንግል ሐዘን ማለት ነው፡፡) ይሄም በአባ ጽጌ ድንግል የተደረሰ ሲሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጅዋን ከሄሮድስ ወታደሮች እና ከበረሐ ወንበዴዎች ለማዳን በስደቱ ወቅት ያሳለፈችውን መከራ በግጥም የሚያስታውስ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በዜማ እና በንባብ ይደረሳል፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ በየቤተ ክርስቲያኑ ማሕሌተ ጽጌ እና ሰቆቃወ ድንግል ይደረሳሉ፡፡

#ይህንን_ወቅት_ለመዘከር:- ምዕመናንም የወርኃ ጽጌን እሑዶች በየነፍስ አባቶቻቸው ተከፋፍልው አገልጋዬችን የሚያስተናግዱበት እና ችግረኞችን የሚመግቡበት ትውፊት አለ፡፡

#የፈቃድ_ጾም፡- በዚህ ወቅት የታወጀ ጾም የለም፡፡ ነገር ግን በገዳም ያሉ መነኮሳት እና መናንያን እንዲሁም አንዳንድ ምዕመናን የጌታችንን እና የእመቤታችንን ስደት ለማሰብ በፈቃዳቸው ይጾማሉ፡፡


ድንግል ሆይ ከሚያስብ ሁሉን ከማይዘነጋ ከልጅሽ ዘንድ አሳሳቢ።

ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን ካገር ወደ አገር ከእርሱ ጋር ስትሸሺ ካንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ።

ድንግል ሆይ ከአይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደው ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ።

ድንግል ሆይ ረኃቡንና ጥሙን ችግሩንና ኃዘኑን ከእርሱ ጋር የደረሰብሽን ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ።

ድንግል ሆይ ጥፋትን አይደል ይቅርታን አሳስቢ።

መዓትን አይደለ ምህረትን አሳስቢ።

ለጻድቃን አይደለ ለኃጥአን አሳስቢ።

ለንጹሐን አይደለ ለተዳደፉ አሰስቢ። አሁንም
አብንና ወልድን መንፈ ቅዱስን እናመሰግንዋለን ለዘላለሙ አሜን።

መልካም የጽጌ ወር!!!