Get Mystery Box with random crypto!

#መስከረም_25_ዕረፍቱ_ለነቢየ_እግዚአብሔር_ዮናስ። ዮናስ ማለት የዋህ ርግብ ማለት ነው፡፡ ቁጥሩ | ዝክረ ብሒለ አበው

#መስከረም_25_ዕረፍቱ_ለነቢየ_እግዚአብሔር_ዮናስ።

ዮናስ ማለት የዋህ ርግብ ማለት ነው፡፡ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ነው፡፡ የተወለደው በሰራፕታ ነው፡፡ በዘመኑ የነበረ ነቢይ ኤልያስ ነው፡፡ ይህም ነቢይ በዘመኑ ንጉሥ አክአብ ንግሥቲቱ ኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣዖት አቁመው ጣዖት ሲያመልኩ ተው ቢሏቸው አልመለስም ቢሉ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሰማይ ዝናም እንዳይዘንም አድርጓል፡፡ 1ነገ.18፥1-46፤ ያዕ. 5፥17

ከዚህ በኋላ ምግቡን ያመላልሱለት የነበሩ ቁራዎች ቀርተውበት ውኃውም ደርቆበት ወደ ጌታ ቢያመለክት ‹‹ወደ ሰራፕታ ሂድ በዚያም አንዲት መበለት ሴት ትመግብሃለች›› ብሎት ሰራፕታ የዮናስን እናት አግኝቷት ‹‹ውኃ አጠጪኝ ጥቂት ቁራሽም አምጪልኝ›› አላት፡፡ ‹‹ሕያው እግዚአብሔርን እፍኝ ዱቄት አለችኝ ጋግሬያት አንተም እኔም ልጄም (ዮናስ) በልተናት እንሞታለን›› አለችው፡፡ ኤልያስም የረሀቡ ዘመን እስኪያልፍ ይበርክት አላት፡፡ ብትገባ ዱቄቱ በማድጋው ዘይቱ በማሰሮው መልቶ አገኘች፡፡

ልጅዋ ዮናስም ታሞባት በሞተ ጊዜ ሄዳ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስን ሳይገባኝ ከቤቴ ገብተህ ኃጢአቴን ተመራምረህ ልጄን ትገድልብኝ አለችው፡፡ እጁን ከእጁ እግሩን ከእግሩ ገጥሞ እየወደቀ እየተነሣ ቢጸልይ በሰባተኛው ተነሥቷል፡፡ 1ነገ. 17፥1-24

ዮናስ አርባ ዓመት ሲሞላው ሀብተ ትንቢት ተሰጥቶት ማስተማር ጀመረ፡፡ አንድ ጊዜ ጌታ ነነዌ ወርደህ ‹‹ነነዌ እስከ ሦስት ቀን ትጠፋለች ንስሓ ግቡ›› ብለህ አስተምር አለው፡፡ ዮናስም ‹‹እርሱ እንደሆነ ለቸርነቱ መስፈርት የለውምና ቢምራቸው ሐሳዊ ነቢይ ልባል አይደለምን?›› ብሎ ከፊቱ ለመሰወር ወደ ተርሴስ ሊሄድ መርከብ ተሳፈረ፡፡ በባሕሩ ማዕከል ሲደርሱ ጽኑ ማዕበል ተነሥቶ መርከበኞቹን አስጨነቃቸው፡፡ እሱም ከወደ ውስጥ ተኝቶ ነበር፡፡ ቀስቅሰው ‹‹ስንጠፋ ዝም ትላለህን?›› አሉት፡፡ ከእግዚአብሔር እንደሆነ አውቆ ‹‹እኔን አውጥታችሁ ጣሉኝ›› አላቸው፡፡ እነሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ንጹሕ ደም ልንጠፋ አይደለምን›› ብለው ዕጣ ተጣጣሉ በርሱ ላይ ወጣ፡፡ አውጥተው ጣሉት ማዕበሉም ጸጥ አለ፡፡
እሱም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሠ ዐንበሪ ቆይቶ በሦስተኛው ቀን ዐንበሪው በነነዌ የብስ ተፋው፡፡ ከተማም ገብቶ ‹‹ሀገራችሁ እስከ ሦስት ቀን ትጠፋለች ንስሓ ግቡ›› እያለ አስተማረ፡፡ ንጉሡም የጾም አዋጅ አስነግሮ ከዙፋኑ ወርዶ ሕዝቡም ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው አዘኑ አለቀሱ፡፡ ሕፃናት ከጡት ከብቶችም ከሣር ተከልክለዋል፡፡ ዮናስ ይህን አይቶ እንግዲህማ ሊምራቸው ነው እኔም ሐሳዊ ነቢይ ልባል ነው ብሎ እያዘነ ከከተማ ወጥቶ ዳስ ሠርቶ ተቀመጠ፡፡ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ተኘቶ ቢነቃ ከራስጌው ቅል በቅላ ፀሐይ ስትከላከለው አየ፤ ደስ አለው፡፡ ሁለተኛ ተኝቶ ቢነሣ ጠውልጋ ደርቃ አገኘ አዘነ፡፡ ጌታ ‹‹አንተ ላልተከልካት ውኃ ላላጠጣሃት ቅል እንዲህ ስታዝን አኔስ በዝናም አብቅዬ በፀሐይ አብስዬ ለምመግባቸው ሕዝቤ አላዝንምን?›› አለው፡፡ ፈቃዱንም ለመፈጸም /ሐሳዊ ነቢይ እንዳይሉት/ በሦስተኛው ቀን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከፍ ከፍ ያሉትን ዕፅዋት ጫፍ ጫፋቸውን በልቷል፡፡ (ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ 1-4) 

ነቢዩ ቅዱስ ዮናስ በምድር ያለውን አገልግሎቱን ፈጽሞ መስከረም 25 ቀን በክብር አርፏል።

" ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።" (የማቴዎስ ወንጌል 10:41)

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር