Get Mystery Box with random crypto!

# ነሐሴ_24_እረፍቱ_ለጻድቅ_ተክለሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ” የሚለው ቃል ሕግን መፈጸም፣ | ዝክረ ብሒለ አበው

# ነሐሴ_24_እረፍቱ_ለጻድቅ_ተክለሃይማኖት
በመጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ” የሚለው ቃል ሕግን
መፈጸም፣ እንደ ሕግ መኖርና መመራት፣
ትክክለኛነትን እና እውነተኛነትን ያመለክታል፡፡
“ጻድቅ” የሚለውም ቃል በሕግ የጸና፣ እንደ ሕግ
የሚኖር እውነተኛ ሰውን የሚወክል ቃል ነው፡፡
ሰዎች አካሄዳቸውን በእግዚአብሔር ፊት
ሲያደርጉና እንደ እግዚአብሔር ሕግ ሲኖሩ ጻድቃን
ይባላሉ፡፡ ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖትም
በእግዚአብሔር ፊት እንደ እግዚአብሔር ሕግ
የኖሩ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ጻድቁ
ተክለሃይማኖት እግዚአብሔርን ከሚወዱ እና
ከሚያከብሩ ከአባታቸው ጸጋዘአብ እና ከእናታቸው
እግዚእ ሐረያ ታኅሣሥ 24 ቀን ተወለዱ፡፡
ጸጋዘአብ ማለት የአብ ጸጋ ማለት ሲሆን እግዚእ
ሐረያ ማለት ደግሞ በጌታ የተመረጠች ማለት
ነው፡፡ ጸጋ ዘአብ እና እግዚአ ሐረያ እግዚአብሔርን
በፍጹም ልባቸው የሚያምኑ፣ በተለያየ ሕመም
የሚሰቃዩ እና ችግረኞችን የሚረዱ ደጋግ ሰዎች
ነበሩ፡፡ በተለይ ለእግዚአብሔር መልአክ ለቅዱስ
ሚካኤል የተለየ ፍቅር ስለነበራቸው በየወሩ
በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት በመታመን
የመልአኩን በዓል ድሆችን በመንከባከብ ያከብሩ
ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቅዱስ ሚካኤል
በሕልም ተገልጾ እግዚአብሔር የተባረከ ልጅ
እንደሚሰጣቸው ነገራቸው፡፡ እግዚአብሔር
የሰጣቸውን ወንድ ልጅ ፍሥሐጽዮን ብለው
ጠሩት፡፡ ፍሥሐጽዮን ማለት የጽዮን ደስታ ማለት
ነው፡፡ ሕፃኑ ፍሥሐጽዮን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ
በሶስተኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ
ቅዱስ አሐድ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ
አመሰገነ፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበር
ፍሥሐጽዮን በልጅነቱ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፡፡
በአንድ ወቅት ረሃብ ነበር ቤተሰቦቹ በዚህ
ምክንያት የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር እንዳያቋርጡ
ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ዱቄትና ዘይት
በማብዛት ቤተሰቦቹ ዝክሩን ያለምንም ችጋር
እንዲዘክሩ አድርጓል፡፡
ዝክር ማለት በእግዚአብሔር፣ በቅዱሳን እና
በመላእክት ስም የሚደረግ መታሰቢያ ነው፡፡
ፍሥሐጽዮን እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ፡፡
በዐሥራ አምስት ዓመቱ ከአቡነ ቄርሎስ ሁለተኛ
ዲቁና ተቀበለ፡፡ ወደ ቤት ሲመለስ ቤተሰቦቹ
አንዲት ሴት እንዲያገባት እንዳጩለት ነገሩት፡፡
ነገር ግን ፍሥሐጽዮን ይህን ጥያቄ
አልተቀበለውም ነበር፡፡ አንድ ቀን ፍሥሐጽዮን
ከጓደኞቹ ጋር ለአደን እንደወጣ መልአኩ ቅዱስ
ሚካኤል ተገልጦ ከዚህ በኋላ ያለውን ቀሪ
ዘመኑን የሰዎችን ነፍስ በማዳን እግዚአብሔርን
እንዲያገለግል መመረጡን ነገረው፡፡ መልአኩ
የፍስሐጽዮንን ስም ተክለሃይማኖት (የሃይማኖት
ዛፍ (ተክል)) ብሎ ለወጠው፡፡ ከዚህ በኋላ
ተክለሃይማኖት ወደቤቱ ተመልሶ ገንዘቡን ለቤተ
ክርስቲያን እና ለድሆች ሰጥቶ ወደ ገዳም ሄደ፡፡
በገዳም እያገለገለ እና እየተማረ የቅድስና
ማዕርግን ተቀበለ፡፡ በትጋት ወንጌልን በመስበኩ
ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስትና ተመለሱ፡፡ በደብረ
ዳሞ ገዳም ለብዙ ዓመታት በአገልግሎት ከቆየ
በኋላ አንድ ቀን በገመድ ሲወርድ ገመድ ተበጥሶ
ሲጸልይ ክንፍ ተሰጠው፡፡
ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ሃያ ዘጠኝ ዓመታትን
ያሳለፈው ደብረ አሰቦ በተባለ ቦታ ቆሞ
በመጸለይ ነበር፡፡ ለረጅም ሰዓታት በመቆም
ይጸልይ ስለነበረ እግሩ ሊቆረጥ ችሏል፡፡ አንድ
እገሩ ቢቆረጥም ጸሎቱን እና ትጋቱን አላቋረጠም
ነበር፡፡ በአንድ እግሩ ለሰባት አመታት ጸልዮአል፡፡
ጻድቁ ተክለሃይማኖት ዘመኑን ወንጌልን ለማያምኑ
ሰዎች በመስበክ ብዙ ኢ-አማንያንን ክርስትናን
እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡ የቤተ ክርስቲያን
አገልግሎት እንዲሰፋ እና ገዳማዊ ሕይወት
እንዲጠነክር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን
በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ነሐሴ ሃያ አራት ቀን
በክብር አርፏል፡፡ ጸሎቱ ቃል ኪዳኑ እና በረከቱ
ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡