Get Mystery Box with random crypto!

#ሐሙስ_ግንቦት_25 ✣✢✣✢✣✢✢✣ #የ2014_ዓ.ም_የጌታችን_ዕርገት_መታሰቢያ_ዕለት_ነው | ዝክረ ብሒለ አበው

#ሐሙስ_ግንቦት_25
✣✢✣✢✣✢✢✣
#የ2014_ዓ.ም_የጌታችን_ዕርገት_መታሰቢያ_ዕለት_ነው

‹‹አምላክ በእልልታ ፤ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ›› (መዝ.46:5)


✥ጌታችን ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሐዋርያት ሦስት ጊዜ ተገልጦላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው መግደላዊት ማርያም ለሐዋርያት ትንሣኤውን ካበሠረቻቸው በኋላ እሑድ ማታ ሐዋርያት በአንድነት በተሰበሰቡበት 
‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ብሎ ተገለጠላቸው እፍ ብሎም ሥልጣነ ክህነትን ሰጣቸው፡፡ 
ሁለተኛው ደግሞ ሐዋርያው ቶማስ ጌታ ትንሣኤውን ሲገልጥላቸው በቦታው ስላልነበረ ካላየሁ አላምንም ብሎ ነበረ ፤ ጌታችን የቅዱስ ቶማስን ጥርጣሬ ለማራቅ ዳግመኛ በተሰበሰቡበት ተገለጠላቸው ፤ ሦስተኛው ደግሞ ሐዋርያት ዓሣ ለማጥመድ በጥብርያዶስ ባሕር ወርደው ብዙ ደከሙ ነገር ግን አንድም ዓሣ አላገኙም ፤ ኋላ ጌታችን ተገልጦ መረቡን ወደ ቀኝ እንዲጥሉ በማዘዝ 153 ታላላቅ ዓሦችን እንዲያገኙ አደርጓል፡፡ 
✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢
ጌታችን ለሐዋርያት ከሞት ከተነሣ በኋላ በኅብረት እንዳለ ሦስት ጊዜ ተገልጦላቸዋል ፤ ከትንሣኤው በኋላ ባሉት ፵ (40) ቀናትም ለሐዋርያት መጽሐፈ ኪዳን የተባለውን የቤተ ክርስቲያናችንን ጸሎት አስተምሯቸዋል፡፡ 
✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤✤
ጌታችን ከሞት ከተነሣ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፉ ብዙ ተአምራትን አድርጓል ፤ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ አለ ‹‹ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ›› (ዮሐ. 20፤30)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሐዋርያት አለቃ ለቅዱስ ጴጥሮስ የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑትን ምዕመናን እንዲጠብቅ ትልቅ መንፈሳዊ ሓላፊነት ሰጥቶታል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ 40 ቀን በሆነው ጊዜ ፤ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ መከራ እንደተቀበለ እንደሞተ ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደተነሣ በመስበክ ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ‹‹እስከ ምድር ዳርም ድረስ መስክሮቼ ትሆናላችሁ›› በማለት ነገራቸው፡፡ አያይዞም ‹‹አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› በማለት አባታዊና አምላካዊ አደራን ሰጣቸው።
✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣✣
 ቀጥሎም ሐዋርያትን ወደ ቢታንያ ይዞአቸው ወጣ ፤ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ላይ ሆኖ ፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው ፤ እያዩትም ከፍ ክፍ አለ ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው ፤ በሰማያት ሰማያዊ የሆነ ምስጋና ተሰማ ፤ ሉቃነ መላእክት አምላካቸውን ሉቀበለ ወረደ ፤ ነገደ መላእክትም ሁሉ ያመሰግኑ ነበረ፡፡ መድኃኔ ዓለምም በክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ምድር ወድቀው ሰገደለት ፤ ቀና ብለውም ወደ ሰማያት ሲያርግ ትኩር ብለው ሲመለከቱት ሳለ ሁለት መላእክት ተገልጠው ‹‹ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል፡፡›› (ሐዋ. 1፤11) በማለት አሰናበቷቸው ፤ ሐዋርያትም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተው ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ፤ በተነገራቸውም ትእዛዝ መሠረት ሐዋርያት አንድ ልብ ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበረ፡፡
(ሉቃ. 24 ፤ 50 ፤ ሐዋ. 1 ፤ 1 - 12) 
✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢✢
የጌታችን ዕርገት ልዩ ነው ፤ በሥልጣኑ በፈቃዱ ይህን አድርጓልና፡፡ አስቀድሞ ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰማያት አርጓል ነገር ግን የእርሱ ዕርገት በእግዚአብሔር ኃይል ፣ ፈቃድና ሥልጣን ነበረ፡፡ ሁሉ የሚቻለው መድኃኔ ዓለም ግን በክብር በምስጋና በፈቃዱ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡ 
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥
#ጥያቄዎችን_በመመለስ_በረከት_ያግኙ

1.ጌታችን ከተነሣ በስንተኛው ቀን ዐረገ? 

2.ጌታችን ያረገበት ተራራ የትኛው ነው? 

3.በዚያ ተራራ ላይ ከዕርገቱ በፊት የተፈጸመ አንድ ታሪክ ጥቀሱ? 

4.የጌታችን ዕርገት ከቅዱሳን ዕርገት በምን ይለያል? 

5.ጌታ ሲያርግ ለሐዋርያት የሰጠው ተስፋ ምንድን ነበር?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር✥