Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን!!!  #ግንቦት_20:- #የከበረ_ጻ | ዝክረ ብሒለ አበው

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን!!!
 #ግንቦት_20:-
#የከበረ_ጻድቅ_ኢትዮጵያዊው_ንጉሥ_ዐፄ_ካሌብ_ዕረፍቱ_ነው፡፡

<<እርሱም የናግራን ሰማዕታትን ደም የተበቀለና በኋላም ንግሥናውን ትቶ ዓለምን ንቆ በመመንኮስ ዋሻ የገባ ነው፡፡ የነገሠበትን የወርቅ ዘውዱንም በጌታችን መቃብር ላይ አስቀምጡልኝ ብሎ ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአባ ዮሐንስ ልኮለታል>>

ከክርስቶስ ልደት 524 ዓመት በኋላ በናግራን ሀገር በክርስቲያኖች በአይሁዶችና በአረማውያን መካከል ከባድ ፀብ ተነሣ፡፡ ማዝሩቅ ወይም ፊንሐስ የተባለው የሂማሪያው ንጉሥ የአይሁዶችንና የአረመኔዎቹን ምክር እየተቀበለ ክርስቲያኖቹን ፈጃቸው፣ አብያተ ክርስቲያናቱንም ሁሉ አቃጠለ፡፡ አረማዊው ንጉሥ ‹አምላካችሁን ክርስቶስን ብትክዱት ሕይወታችሁ ይጠበቃል።ሕዝቡም ‹‹ጌታችንን አንክድም›› እያሉ ተገደሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የተገደሉት ቁጥራቸው 4252 ሆነ።

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባ ጢሞቴዎስ ለሀገረ ናግራን ክርስቲያኖች ደማቸውን ይበቀልላቸው ዘንድ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዐፄ ካሌብ መልአክት ላከ፡፡
ዐፄ ካሌብም መልእክቱ ሲደርሰው ፈጥኖ ተነሣና በዋሻ ከሚኖር ከአቡነ ጰንጠሌዎን በረከትን ተቀብሎ ለአቡነ አረጋዊም በጸሎት እንዲያስቡት ፡ ‹‹ፊንሐስ የተባለ አረማዊ የናግራን ክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ያፈሰሰ፣ ቤተ ክርስቲያንን የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ወደሚሆን ሄጄ እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስለዚህ አባቴ ሆይ! አንተም በበኩልህ ጸሎት አድርግልኝ፣ የጻድቅ ጸሎት ትራዳለች፣ ኃይልንም ታሰጣለች፣ በጠላት ላይ ድልንም ታቀዳጃለችና›› የሚል ደብዳቤ ላከ።

አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ  ‹ወደ ጦሩ ግንባር ሂድ፣ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ከእግርህ በታች ያስገዛልህ፣ ለአንተም ግርማ ሞገስ ይስጥህ፣ በሰላም ይመልስህ›› ብለው መርቀው ላኩለት፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ ካሌብ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ጥሎ ማቅ ለብሶ በፍጹም ልመና ብዙ ጸሎት አደረገ፡፡

ከዚህም በኋላ ዐፄ ካሌብ ሰባ ሺህ ጦሩን አዘጋጅቶ ወደ የመን ሳባ በመርከብ ተጓዘና ከከሐዲው ፊንሐስ ጋር ጦር ገጠመ፡፡ ከሐዲውን ንጉሥ ፊንሐስን ራሱ ዐፄ ካሌብ ገጠመውና በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ባሕር ገልብጦ ጣለው፡፡ ከዚያም ዐፄ ካሌብ ዛፋር ወደምትባለው ከተማ ሄዶ እርሷንም ተቆጣጠራት፡፡ በእዚያም ያሉ የፊንሐስን ሹማምንቶች እያፈላለገ በአደባባይ እንዲገደሉ በማድረግ የክርስቲያኖቹን ደም በሚገባ ተበቀለ፡፡ የናግራንንም ሕንፃዎዋን አደሰ፤ የሰማዕታቱንም መታሰቢያ አቆመ፡፡ ወደ እስክንድርያው አባ ጢሞቴዎስና ወደ ሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም የድል መልእክት ላከላቸውና እነርሱም ሰምተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በአንጾኪያ፣ በእስክንድሪያ፣ በሮም፣ በቊስጥንጥንያና በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ሲሰሙ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ ይህም የሆነው በ525 ዓ.ም ነው፡፡ ጠፍተው የሄዱ ክርስቲያኖችንም ሰበሰባቸውና ወደቀደመ ቦታቸው መለሳቸው፣ ቤተክርስቲያናቸውን አነጸላቸው፡፡ ከሳባ ሀገር የማረከውን ንብረት ሁሉ ለቤተክርስቲያን ሰጥቶ ዓሥር ሺህ ጠባቂ ሠራዊት ሰቷቸው ወደ አክሱም በሰላምና በፍጹም ደስታ ተመለሰ፡፡

ከዚህ በኋላ ዐፄ ካሌብ ‹ይህን ያደረገልኝን አምላኬን በምን ላስደስተው?› ሲል አሰበና ዓለምን ንቆ፣ መንግሥቱንና ክብሩን ትቶ መንኩሶ በዋሻ ለመቀመጥ ወሰነ፡፡›› ዐፄ ካሌብ ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ የውኃ መንቀልና አንዲት ምንጣፍ ብቻ ይዞ አባ ጰንጠሌዎን ገዳም አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገባ።
አባ ጰንጠሌዎንንም ‹አመንኩሰኝ› አለውና የመላእክትን አስኬማ አልብሶ አመነኮሰው፡፡ ዳግመኛም ከዋሻው ወጥቶ ዓለምን በዓይኑ እንዳያይ ማለ፡፡ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ የጫነውን ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ወይም በር ላይ ይሰቀልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ላከለት፡፡ ዳግመኛም ንጉሡ ዐፄ ካሌብ ለአቡነ አረጋዊ ወደ ምንኩስናው ዓለም መግባቱን አሳወቀ እነርሱ በደስታ መረቁት፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረሃ በዋሻ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ተጋድሎ ሲኖር ቆይቶ በግንቦት 20 ቀን ዐርፎ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የማያልፍ ሰማያዊ ክብርን ወረሰ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!