Get Mystery Box with random crypto!

የዲኤስ ቲቪ ገጠመኜ ጌቱ ባለፈው እሑድ የነበረው የአርሰናልና ማንችስተር ጨዋታ እጅ | BULBULA NEWS⏰

የዲኤስ ቲቪ ገጠመኜ

ጌቱ

ባለፈው እሑድ የነበረው የአርሰናልና ማንችስተር ጨዋታ እጅግ ግሩም ነበር፡፡ ለኔ ደግሞ ለየት የሚደርገው በልጅነቴ የዱርዬዎች ማዋያ እንደሆነ እየተነገረኝ እንዳልሔድ ወደምከለከልበት " DSTV ቤት" ከረዥም ጊዜ በኋላ የምሔድ መሆኑ ነው፡፡

ልጅ እያለሁ የአርሰናል ደጋፊ ነበርኩ፡፡ የድጋፌ ምክንያት ምንም አይነት ሎጂካዊ ምክንያት የለውም፡፡ በቃ ምናልባት በአጋጣሚ የአርሰናል ማልያ ተገዝቶልኝ ስለነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ በአውሮፓ የእግርኳስ እንቅስቃሴ ላይ ብዙም ትኩረት አልነበረኝም፡፡

ሰሞኑን ግን የአርሰናልና ማንችስተር ደጋፊ የነበሩ ጓዶቼ በየዕለቱ ሲያደርጉት የነበረው የጋለ ክርክር ሠላም ሲነሳኝ እነዚህን ሰዎች ስሜታዊ ያደረግው መንፈስ እኔንም በጉጉት እንድሞላ አደረገኝ፡፡ ጭራሽ አንዳንዶቹ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ መድበው መወራረድ ሲጀምሩ ነገርዬው ይበልጥ መጦዝ ጀመረ፡፡

"… በአንድ ሰው ላይ የተንጠላጠለ ክለብ ይዛችሁ ታወራላችሁ እንዴ፡ ሮናልዶ ቢወጣኮ ገደል ነው የምትገቡት ዝም ብላችሁ በድሮ ዝና ታወራላችሁ" ይላል የአርሰናሉ ደጋፊ፡፡ " ዝም በል ባክህ ወሬያም ትልቅ ክለብ ሁሌም ትልቅ ነው፡ አንድ ሲዝን አቋም መውረድ ያለ ነው- እስኪ እናንተ ጋር ከጄሱስ ውጪ እስኪ አንኳ ሚጠራ ተጫዋች ንገረኝ፤ ደህና ተጫዋች የላችሁምኮ፡ እሑድ እንተያይ የለ" ይላሉ ማንቼዎቹ፡፡

“እኛ” “እናንተ” እያሉ ሲያወሩ ከክለቡ የባለቤትነት ሼር የገዙ ነው ሚመስሉት፡፡ ራሳቸውን ለዚህ ስሜት ከልብ የሰጡበት መንገድ በጣም ስቦኝ ይህን ጨዋታ ማየት አለብኝ አልኩ፡፡

ሔድኩ፡ አብዛኛው Open air/ክፍት ያልሁኑ ዲኤስ ቲቪ ቤት ስትገቡ መጀመርያ ከውጪው ነፋሻማ ኣየር በተቃራኒ ወበቅ ውስጥ የሚገኝ ሙቅ አየር ከትነፋሽ ጥርቅም፣ ከጫማና ከሌሎች ጠረኖች ጋር ተዋሕዶ እንደመጋኛ ከውስጥ ሊጠልዛችሁ ይችላል፡፡ወድያው ግን ተላምዳችሁት ለሙቀቱ የራሳችሁን ሚና ማዋጣት ትጀምራላችሁ፡፡

12፡30 አናቱ ላይ ጨዋታው ጀመረ፡ ጭብጨባው ሌላ ነው፡፡ ተመልካቾቹ ስለተጫዋቾቹ በጥልቀት የሚውቀበት መንገድ ይገርማል፡፡ ካሜራው እያንዳዱን ተጫዋች ሲያሳይ “ትችላለህ አንተ፣ ብራቮ” እያሉ ተጫዋቹ ይሰማቸው ይመስል ያበረታቱታል፡፡ በጣም ልዮ ጨዋታ ነበር፡ በዛ ላይ በዙርያዬ ያለው ድባብ ደግሞ ቃናውን ይበልጥ እጥፍ አደረገው፡፡ አንዱ ቡድን ሲሞክር ደጋፊው በሞራል የጨበጭባል፤ የባላንጣውም ብድን ኳሱ ስላልገባ ያጨበጭባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጭብጨባው ስለማይቀር የደራ ስሜት ይፈጠራል ኦ አምላኬ! በጣም ልዩ ስሜት ነበረው፡፡

በአርሰናል ተከላካዮች "ነቅሎ በመውጣት" ክፍተት መፍጠርና በአንዳንድ ምክንያቶች ማንችስተር 3 -1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነጥብ ይዞ ወጣ፡፡ ሲያንቀለቅለኝ የአርሰና ደጋፊ መሆኔን ተናግሬ የማንቼ ደጋፊዎች ተረብና ፉገራ ዘነበብኝ፡፡ አርሰናል መዝናኛዬ እያሉ ጨፈሩብኝ፡ ገና መች አያችሁ፡ ትወቀጣላችሁ እያሉ ዛቱብኝ፡፡ ኦ አምላኬ እስከዛሬ ይሄን ስሜት ሳላጣጥመው ነው የኖርኩት ተመልካቾቹ በግድ የአርሰናል ውጤት የእኔ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንዲኖረው ለማሳመን ገፋፉኝ፡፡

ሳልፈልግ ቤት ገብቼ ኢንተርኔት ላይ የመድፈኞቹን የስከዛሬ ጉዞ የሚያስቃኙ ዶክመንተሪዎች፣ ትንታኔዎችን ስለተጫዋቾቹ ብቃትና ቀደምት ታሪክ ስራዬ ብዬ ማጥናት ከመጀመሬም በላይ ቀጣዩን ጨዋታ እስክታደም ቸኮልኩኝ፡፡

ይህን ያራሴን ስሜት የማጋራችሁ ዝም ብዬ አይደለም፥ አንድ ጠቃሚ ነገር ስላገኘሁበት ነው፡፡ ሰዉ ጡዟል፡ ሚዲያውም እንዳለ ሽብርና ችግር ችግሩን ብቻ በማውራት ተጠምደዋል፡፡ ውዱ አእምሮኣችን የሆነ እፎይ የሚልበት አንዳች ነገር ያስፈልገዋል፡፡ ቲሽ! ስንት ሺሕ ዓመት ልትኖሩ ነው ምትጨነቁት፡፡ የምሬን ነው፡ በደንብ አስቡበት በቀጣዩ ዓመት የሆነ ትኩረት የምትሰጡትን ተከታታይ ድራማ፣ መዝናኛ ሾው ወይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መርጣችሁ ወደሕይወታችሁ ቀላቅሉ፡፡ እመኑኝ ታ! ተ! ር! ፉ! በ! ታ! ላ! ች! ሁ!!

መልካም አዲስ አመት!!

ስለምወዳችሁ

@BBN_info