Get Mystery Box with random crypto!

#ዕርገት † መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ † ጌታ ሆይ ዛሬ መላእክት የሰማይ ደጆቻቸውን ከፍተው በም | ማዕተብ

#ዕርገት
† መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ †

ጌታ ሆይ ዛሬ መላእክት የሰማይ ደጆቻቸውን ከፍተው በምስጋና በክብር ይቀበሉሃል ፤ ደመናን የምትሰውራት አንተ ፣ ደመና ሰውራ ተቀበለችው ተባለልህ ፤ ከሃዋርያት አይን መሰውርህን ለመናገር እንጂ ሰማይ ዙፋን የሆነልህ አንተን ደመና በምን አቅሟ መደበቅ ትችል ይሆን።

ጌታ ሆይ ወደተቀደሰው ዙፏንህ ዛሬ ዐረግህ ፤ በፈቃዴ ወዳረከስኩት ወደ እኔ ልብ’ስ መቼ ነው የምታርገው ? እኔ እንደመላእክቱ የምከፍተው ደገኛ በር የለኝም ፤ የልቤ በር ተቆልፎ ከቆየ ብዙ ዘመን አልፎታል ፣ መክፈቻ ቁልፉም ጠፍቶብኛል ፣ ላንተ የሚሆን ምስጋና የሚያዘጋጅ ንጹህ ህሊናም አልተረፈኝም ፣
" ለእኔ ምን አይነት ቤት ትሰሩልኛላችሁ ብለህ ነበር " አዎ ጌታ ሆይ የኔ ቤት የሚከረፋ በኃጢአት የቆሸሸ ቤት ነው ።

እንግዲህ ጌታ ሆይ ላንተ የሚሆን ምንም የቀረልኝ ነገር የለም ፤ ግን በጥበበኛ እጅህ ሠርተኸኛልና አድነኝ ፣ ወደ ልቤ ቤት ለመግባት አንተ ቁልፍ አያስፈልግህም ፣ በተዘጋ በር መግባት ታውቅበታለህ እና ና ግባ ፣ ያም ካልሆነ የመቶ አለቃውን ጸሎት ተውሼ እማጸንሃለሁ "ቃል ብቻ ተናገር ልቤ ይፈወሳል"



[_ዲያቆን ብንያም አለባቸው_]