Get Mystery Box with random crypto!

በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ላይ እርማት እንዲደረግ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጠየቀ | Assosa online

በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ላይ እርማት እንዲደረግ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጠየቀ።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዛሬ ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ የ12ኛ ክፍል መግቢያ ፈተና እና ውጤት ላይ እርማት እንዲደረግ ጠይቋል።
የመግቢያ ፈተናውን ውጤት ተከትሎ የሚወጡት መረጃዎች ያልተለመዱና አስደንጋጭ ናቸው ያለው የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በተወሰኑ ተማሪዎችና ወላጆች ግፊትና ጫና የተስተካከሉ ውጤቶች ለተፈጠረው ስሕተት ኹነኛ ማሳያዎች ናቸው ብሏል።
የአማራ ትምህርት ቢሮ የኹሉንም ትምህርት ቤቶች ውጤት ዝርዝር መረጃ በመሰብሰብ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባው የጠቆመው ፎረሙ ትምህርት ሚኒስቴርና የፈተናዎች ድርጅት ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው ለማረም እድል ያገኛሉ ብሎ እንደሚያምን በደብዳቤው ገልጿል።
በተማሪዎችና ወላጆች እየቀረበ ያለውን ጥያቄ ሁሉም ወገን በቅንነት ተቀብሎ የድጋሜ እርማትን እንዲሁም ተጨማሪ ማጣራት ማድረግ በዜጎች ዘንድ ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት ከማረጋገጡም በላይ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ይጠቅማል ሲልም ፎረሙ አሳስቧል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናውና ውጤቱ ላይ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች እንደ ፖለቲካ ጥያቄ አቻችሎና ሰምቶ በመተው የሚፈቱ ሳይኾን የትውልዱን እድል የሚወስኑ በመኾናቸው በፍጹም አካዳሚያዊ ሥነ ምግባርና ከፍተኛ መኾን አለበት ብሏል ፎረሙ።
ፎረሙ በጻፈው ደብዳቤም ኹሉም አካላት ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቋል።
ፈተና በደቦ እየተሠራ መልካም ትውልዶችን መፍጠር አይቻልም ያለው ተቋሙ ጉዳዩ ከብሔር አውድ ፍፁም ነጻ እንዲኾን ኹሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጠይቋል።
ተማሪዎችና ወላጆች ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ተረጋግተው እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርቧል።
(አሚኮ)
t.me/asosaonline