Get Mystery Box with random crypto!

የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ አስለቃሽ ጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ኮንስታብል አንቡላ | አራይቫል የልማት እና መረዳጃ ማህበር

የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ አስለቃሽ ጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በዕለቱ በደረሰብኝ ድብደባ ግራ አይኔ እና ኩላሊቴ ላይ ጉዳት ደርሷብኛል ሲል ለፍርድ ቤቱ አስታወቀ።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ በዕለቱ አንድ የጭስ ቦንብ ሳይሆን 3 የጭስ ቦንብ ነው የፈነዳው ብሏል።

ዕረቡ ግንቦት 1ዐ ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ)

የኢዳልፈጥር በዓል ላይ በመስቀል አደባባይ አካባቢ አስለቃጭ ጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በዕለቱ በደረሰብኝ ድብደባ ግራ አይኑን እና ኩላሊቴ ላይ ጉዳት ደርሷብኛል ሲል ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስታወቀ። የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አድማ ብተና ዘርፍ ባልደረባ የሆነው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ባሳለፍነው ሚያዚያ 24 ቀን በተከበረው የኢዳል ፈጥር ባአል በአ/አ ከተማ በሰማታት መታሰቢያ ሙዚዬም አካባቢ በተመደበበት የወንጀል መከላከል ስራ ላይ እያለ ከፈነዳው አስለቃሽ ጭስ ቦንብ ጋር ተያይዞ ተጠርጥሮ ዛሬ ለኹለተኛ ጊዜ ካለጠበቃ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ተጠርጣሪው ኢድ አልፈጥር በዓል በተመደበበት ሥራ ላይ በአጋጣሚ ሳላውቅ የፈነዳብኝ አስለቃጭ ጭስ ቦንብ ሲፈነዳብኝ ጭሱ ወደ ህዝቡ እንዳይሄድ ወዲያው ሸገር ባስ ውስጥ ወርውሬ ከትቻለሁ፤ በአካባቢው የነበሩት ሰዎች ግን የፌደራል ፖሊስ ልብስ ለብሼ ሳለሁ አንገቴን አንቀው ባደረሱብኝ ድብደባ የግራ አይኔና ኩላሊቴ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪውን ያቀረቡት ኹለት መርማሪ ፖሊሶች ባሳለፍነው ሚያዚያ 26 ቀን ጀምሮ ለተጨማሪ ምርመራ በተሰጣቸው የ10 ቀን ጊዜ ውስጥ የሰሩትን የምርመራ ውጤት ለችሎቱ አቅርበዋል።

በዚህም የሦስት ሰዎች ምስክርነት ቃል መቀበላቸውንና የሥራ ሀላፊዎችን ቃል መውሰዳቸውን፣ የተጠርጣሪው የግል ስልክ ምርመራ እንዲደረግ ለብሔራዊ መረጃ ደህንነትና ለኢትዮ ቴሌኮም ደብዳቤ መጻፋቸውን አብራርተዋል። የፋይናንስ ድጋፍ እንዳለውና እና እንደሌለው ለማጣራት ለባንኮች ደብዳቤ መጻፋቸውን ተናግረዋል።

ግብረአበሮችን ተከታትሎ የመያዝ ሥራ ለመስራትና ምርመራ አጠናቀው ለሚመለከተው ዓቃቢህግ ለመስጠት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በፍርድ ቤቱ በኩል ግብረአበር ለመያዝ ማለት ምን ለማለት እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ከፍንዳታው በፊት ከአንዲት ሴት በአካል ማዋራቱን እና በወቅቱ ስልክ ተደውሎለት ሲያወራ እንደነበር ጠቁመው ይህን ተከትሎ ግብረአበር ካለ የመያዝ ሥራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ተጠርጣሪው በበኩሉ “የፈነዳው ቦንብ አውቄ አደለም ባጋጣሚ እንጂ ምንም አይነት ወንጀል እኔ አልሰራሁም በኔ የደረሰ ችግር የለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ከደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ለሥራ መምጣቱን ገልጾ፤ ጠያቂ ዘመድ እንደሌለው ወላጆቹን በሞት በማጣቱ ትንሽ ወንድሙን በሱ እርዳታ እንደሚያስተምር በመግለጽ ዋስትና እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

መርማሪዎቹ በበኩላቸው በዕለቱ አንድ የጭስ ቦንብ ሳይሆን 3 የጭስ ቦንብ ነው የፈነዳው ያሉ ሲሆን፤ ተጠርጣሪው ከተመደበበት የሥራ ምድብ ውጪ በህዝብ መሀል ሆኖ ነበር ያሉ ብለዋል። ሲጀመር አስለቃሽ ጭስ ቦንብ ይዞ ህዝብ መሀል መቆም አይፈቀድም ይሁንና እንዲወጣ ታዞ ሳይወጣ ቀርቷል ኹከትና ብጥብጡም በዚህ መነሻ ነው የተነሳው ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ መነሻ በመንግስትና በግል ድርጅቶች ላይ የደረሰው የንብረት ጉዳት ፍርድ ቤቱ እንዲረዳላቸውና ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀሪ ምርመራ ማድረግ እንደማያስፈልግ በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 13 ቀናትን በመፍቀድ የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለግንቦት23 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

አዲስ ማለዳ

@Abuki_Tube | @Abuki_Tube