Get Mystery Box with random crypto!

አስተዳደራዊ ድክመት የፈጠረው  የንግግር ለከት ማጣት ሀገርን የከፋ ቀውስ ውስጥ ይከታል !    | አንሙት አብርሃም

አስተዳደራዊ ድክመት የፈጠረው  የንግግር ለከት ማጣት ሀገርን የከፋ ቀውስ ውስጥ ይከታል !

       በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ
ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ አልፎም በመረጡት ቦታ የመኖር የሠው ልጅ ማንም ሊሠጠው እና ሊነሣው የማይችል የተፈጥሮ ሥጦታ   ከመሆኑም በተጨማሪ  በሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የተሰጣቸው መብት እንጂ አንዳንድ ባለስልጣናት ደስ ሲላቸው የሚቸሩት ካልፈለጉ ደግሞ የሚነፍጉት ጉዳይ አይደለም።
ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ህፃናትን , ታማሚዎችን , እናቶቻችን, አቅመ ደካማ የሆኑ አባቶችን ,  የሃማኖት አባቶችን  ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ሰበባ ሰበብ እየተፈለገ ሲፈጸም የነበረው ድብደባ   ማዋከብ፣ እንግልትና ማጉላላት, መሠወር  ከነገ ዛሬ መሻሻል ይታይበታል ተብሎ ተስፋ ሲደረግ ይባስ ብሎ “ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግሥትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው” በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በቀን 05/07/2015 ዓ.ም ለምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የገለጹበት መንገድ ያለፈውን ስህተት ከማረም ይልቅ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍግ ከመሆኑም በላይ አንዱ በዓንዱ ጥርጣሬን ፈጥሮ እንዲነሣ በማድረግ የቀጠለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ  የዘር ምንጠራ  በከፍተኛ ሴራና ፍረጃ ለበለጠው  ፍጅት የሚያመቻችና ዜጎችን ማግለልና የማሸማቀቅ አካል በመሆኑ ግልፅ ሰዓብዊ መብት ጥሰት ነው።
በሌላ በኩል ትናንት የሃማኖት መሪን በጠራራ ፀሃይ የደንብ ልብሥ የለበሡ የሥርዓቱ ህግ -አሥከባሪ መሠል ፖሊሦች  በጥፊ ሲመቱ፣ ሕጻናትንና ሴቶችን ሲያዋክቡና በማንነታቸው ሲያሸማቅቁ፣ ሲገድሉና ሲዘርፉ ለኖሩ ኃይሎች ሽፋን የመስጠትና ጥብቅና የመቆም አካል አድርገን እንወስደዋለን።
የክሩን ጫፍ ከተከተልነው ደግሞ እኩይ ድርጊቱ በኦሮሚያ ብልጽግና በንግግርም በተግባርም በተጠናና መዋቅራዊ በሆነ ኹኔታ እንደሚፈጸም መሠረታዊ  ማረጋገጫና በቀጣይም ሰቆቃና ማወከቡ ቢብስ እንጂ እንደማይረግብ ጉልህ ማሳያ ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚከለከሉ ዜጎቻችን ጉዳይ የሌላ ሀገር ድንበር አቋርጠው በሕገወጥ መንገድ ለመግባት የሚሞክሩ መንገደኞች እንጂ ከሀገራቸው አንድ ክፍል አባቶቻቸው ወደ አቀኑላቸው ዋና ከተማቸው የሚደረግ ሕጋዊ እንቅስቃሴ አይመስልም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዓለም በድፕሎማቲክ ከተማነት በመጀመሪያዎቹ ረድፍ የምትጠቀስ፣ በሰላሟ የሚቀናባትን ከተማ በምዝበራና ወረራ እንድትጠቀስ፣ ነዋሪዎቿን በኑሮ ውድነት የምትጠብስ፣ ሌብነትና ሙሥና  ሕጋዊ ሆኖ እግር አውጥቶ የሚሄድባት፣ የአፍሪካና የመላ ጥቁር ሕዝብ ድልና ኩራት የሆነው አድዋ በባለቤቱ ሕዝብ የማይከበርባት፣ ጤፍ ብርቁ፣ ሲሚንቶ ብርቁ፣ ስኳር ብርቁ፣ የምሥኪን ዜጎቿን ጎጆ በግብታዊነትና ዘረኝነት በወለደው የጥላቻ ቋሚ  ስካር የምታፈርስ ወደ ማድረግ አዘቅት መምራቱ ሳያንስ የንግግር ለከት ማጣቱና በጽንፈኛ ኃይሎች የተጻፈን ስክሪፕት(Script) በመንግሥት መዋቅር፣ በተከበረ ምክር ቤት ፊት አምጥቶ ማነበነብ እጅጉን ያሥቆጫል ያሣዝናልም ።
ምን አልባት ከዚህ ጀርባ ተስፋ መቁረጥ፣ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ቁርጥራጭ ሀገር የመገንባት ቅዠት፣ ከተማዋን ጥቅም አልባ የማድረግ ቀጣይ ፕሮጀክት፣ አፋርን , ሡማሌን ፣ አማራንና ትግራይን ከአዲስ አበባ የመነጠል፣ ለጥፋቱና ለአጥፊዎች ሽፋን የመስጠት አካሄድ ይመስለናል።
በሌላው ዓለም ቢሆን እንዲህ ያሉ እጅግ መርዘኛና ፍጅት ቀስቃሽ(genocidial motivetor speach)  ንግግሮችና ተናጋሪዎች ተገቢው እርምት በቶሎ በተሰጣቸው ነበር።
በእኛ ሀገር ኹኔታ ሕጋዊነት ሳይሆን ሕገ ወጥነት፣ “የእኛ” ሳይሆን “ለእኔ ብቻ” ባዮች፣ ተጠያቂነት ሳይሆን የተረኝነት መንፈሥ  የሰፈነበት አሠራር  በመሆኑ ለዚህ አልታደለንምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ህግ ንና ሥርዓት ሠፍነኖ  አጥፊዎች የፍትህ ደጃፍን እንዲያዮ  ሁሉም በህግ ፊት እኩል መሆኑንም አውቀው የአገሪቱ ሠላም, አንድነት እና ሉዓላዊነት ማሥከበር የሁላችንም ግዴታ ሥለሆነ ጥሪያችን  እናቀርባለን።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ
መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ