Get Mystery Box with random crypto!

⁽⁽ቤተክርስቲያንን አጠቃህ⁾⁾ እንዳትባል ምን ታደርጋለህ ..!? | አንሙት አብርሃም

⁽⁽ቤተክርስቲያንን አጠቃህ⁾⁾ እንዳትባል ምን ታደርጋለህ ..!?
... ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅመህስ!?

[አንሙት አ.]
--
የወቅቱ፡ "አገር አፍርሶ-አገር ገንቢዎች" ፡ እንደብሒሉ "የኃይማኖት ተቋማትን በታማኞችህ ሳትቆጣጠር ስልጣን ትርጉም የለውም" ከሚል አተያይ በላይ፤ "የእምነት ተቋማትን አፍርሰህ-ሳትሠራ፡ አገር አፍርሰህ ሠራህ ማለት አይቻልም" የሚል እምነት እንደያዙ ነው የገባኝ።

"በወንጌላውያን ሕብረት" እና "በመጅሊሱ" የተሳካ ቁጥጥር ተፈፅሞ አፍርሶ-ግንባታው በመጀመሩ ብዙዎች ከእነ'ቅራኔያቸው እየተቆጩ አሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ አመራሮች በመቀየር ተቋሟን ተቆጣጥሮ በራስ-አምሳል የመሥራት ተልዕኮን ለማሳካት ብልፅግና ስልጣን ከያዘበት ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ስልቶች እንደተሞከሩ መረዳት ይቻላል።

3ኛ ሲኖዶስና 3ኛ ፓትርያርክ እንዳይኖር ለማድረግ፡ ከተወሰዱ፡ አባቶችን አስታርቆ የማሰባሰብ አካሔዶች፡ እስከ ተጨማሪ ሲኖዶስ ማቋቋም ብዙ ስም ማጥፋቶችና ክሶች አልፎም ከአገር-የማሰደድ ፍላጎቶች ተሞክረዋል።
አዲስ ሲኖዶስ መሥርቶ በእርቅ ሥልጣን ተጋርቶ የመቆየት እና በሒደት የመቆጣጠር አካሔዱ፡ በመንግስታዊ ጣልቃ-ገብነት እና ተቋማዊ ጥቃት ስለተወሰደ ፡ ታላቅ የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሷል።

እናም አሁን፡ አዲስ፡ ግን ሲሠራበት የነበረ ስልት፡ ወደሥራ እየገባ ይመስላል፤

ይሔውም ⁽⁽የኃይማኖት ጣልቃገብነት⁾⁾ ቅራኔውን፡ ወደ ⁽⁽መፈንቅለ መንግስት⁾⁾ ክስ በመቀየር፡ ⁽⁽የቤተ-እምነቷን ድምፅ እና አቅሞች⁾⁾ ለማዳከም የሚረዳ ስራ ተጀምሯል።

1) ከሽምግልናው በኋላም ስለእምነትና ተቋማቸው ሲቆረቆሩ የነበሩ ግለሰቦችና የተቋሟ አገልጋዮች እስራት እየተሠራ ነው።
በአዲስአበባም ለምናልባቱ ከቤተ-እምነቷ ጋር ሊቆሙ የሚችሉ እና "በአመፅ ሊሳተፉ ይችላሉ" ተብለው የሚጠረጠሩ ወጣቶች እየታሠሩ ነው።
ይሔ ምናልባት ፡ የቤተክርስቲያኒቱን የመብት ጥያቄዎች በኃይል በመጨፍለቅ ቁጥጥሩን ለማስፈፀም ሲሞከር እምቢ ባይ ወጣቶች እንዳይኖሩ ታስቦ ይሆናል።
እስከከዚያው፡ ደግሞ "ቤተክርስቲያኗን አጠቃህ" ሳይሆን "መፈንቅለ-መንግስት ያሰበን ተቆጣጠርክ" ያስብላል የሚል እምነት ተይዞ ይሆናል።

2) ከ5 አመት በፊት ጀምሮ የዲሞግራፊ አላማ ተይዞለት "ከአዲስአበባ ዙሪያ ሌሎች ተወላጆችን የማስወጣት/ማፅዳት" ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። አሁን ደግሞ ⁽⁽መፈንቅለ መንግስት ለመፈፀም፡ እና አመፅ ለማድረግ ታስቧል⁾⁾ የሚለው ክስ ምቹ ሰበብ ተደርጎ፡ (ምናልባትም የቤታቸውን መፍረስ የሚቃወሙ) በጅምላ እየታሠሩ ነው።
የአዲስአበባ ዙሪያ፡ "መንግስታቸው የሚነካባቸው ዜጎች" ብቻ መኖሪያ እንዲሆን የማድረግ ፕሮጀክቱ ቀጥሏል።

3) በኦሮሚያ ኢ-መደበኛ ታጣቂ ግድያ ሲዘጋ የቆየው የአባይ መውጫ የፌደራል መንገድ ፡ አሁን ደግሞ በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ማለፍ ተከልክሏል። እየተቀባበሉ የሚያስተዳድሩት መንገድ ሆኗል።
ወደ አዲስአበባ ከሚያስገቡ 5/6 መስመሮች መንገደኛ የሚገደልባቸው እና "አመፀኛ የሚገባባቸው" ያሏቸው ከአማራ ክልል የሚነሱት ናቸው።
"ማስወጣት እንጂ ማስገባትን" የሚከለክለው ፕሮጀክት አላማ ሆኖ፡ "የአማራዎችን ወደመሐል አገር የመግባት ፍላጎት እና ስነልቦና መግታት" አይደለም ብሎ የሚያሳምነኝ አላገኘሁም።
"መፈንቅለ መንግስት እና አመፅ ሊፈፅምብኝ የተዘጋጀ አካል ስላለ ዘጋነው" የሚለውን ለዓመታት ሰማነው። በፊት "የወያኔ ተላላኪ ስለሚገባ" የሚለው ሽፋንም ለዛሬ ስለማይሠራ አረዳዴን አይለውጥም ።

የታጠቀው የኦሮሚያ ኢ-መደበኛ ቡድን የሚንቀሳቀስበት ምስራቅ ሸዋ ወይም ምዕራብ ሸዋ መስመሮች ግን አይዘጉም። የግል ጉዳይና ኑሮ የሚያመላልሳቸው ሲቪል አማራዎች ናቸው "የስልጣን ስጋት" የተደረጉት።

በእርግጥ የብልፅግና አመራር ፡ የአዲስአበባ ከተማን ፖሊስ 50ሺህ የማድረስ ሥራ እና በከተማዋ "100ሺህ ሕዝባዊ ሠራዊት" አደራጅቻለሁ ብሏል።

ይሔ ሁሉ ተደማምሮ፡ ⁽⁽ ብልፅግና ወለድ፡ መፈንቅለ-መንግስትን የመከላከያ ስልት⁾⁾ ሊባል ይቻል ይሆን!?

----
* ልዩ ነገራችን
➙ ከየትም መጥተን ስልጣን እንያዝ፣ የእኛ ነገር የመጀመሪያ እና የመጨረሻ አድርገን በማመን መድከማችን !

➙ አቢዮታዊት ኢትዮጵያ ፣ አዲስቷ ኢትዮጵያ ፣ የበለፀገች ኢትዮጵያ እያልን በዜሮ ድምር ፖለቲካ የምንታክት አጥፍቶ ጠፊዎች አልሆንም!?