Get Mystery Box with random crypto!

#አርካኑል_ኢስላም(የኢስላም ማዕዘናት) ☞ አቀዋለሁና አላነብም አትበሉ ኢማናችሁን አድሱት ታተርፋ | Alifun Tube (አሊፉን ቲዩብ)

#አርካኑል_ኢስላም(የኢስላም ማዕዘናት)

☞ አቀዋለሁና አላነብም አትበሉ ኢማናችሁን አድሱት
ታተርፋላችሁ እንጂ አትከስሩም

☞ ኢስላም በአምስት መሰረቶች ላይ የተገነባ ነው እምነት ነው። ማንኛውም ሰው ትክክለኛ ሙስሊም ሊሆን የሚችለው በእነዚህ አምስት መሰረቶች አምኖ ተግባራዊ ሲያደርጋቸው ብቻ ነው። እነርሱም፦
በትኩረት ተከታተሉን

①_ «
#ላ_ኢላሀ_ኢልለላህ_ሙሐመዱን_ረሱሉላህ» ከአላህ(سبحن وتعلا)በቀር በሀቅ የሚመለክ አምላክ የለም፣ ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር ነው። ይህች ምስክርነት ወደ ኢስላም መግቢያ ቁልፍ ናት። ኢስላምም የሚገነባው እርሷን መሰረት አድርጎ ነው። «ኢላህ» ማለት «ማዕቡድ» ወይም የሚመለክ ማለት ነው። እውነተኛው አምላክ አላህ ብቻ ነው። ከእርሱ በቀር የሚመለኩ ሁሉ  ከንቱ አማልክት ናቸው::

በነብዩ ሙሀመድ( صلى الله عليه وسلم) መልዕክተኝነት ማመን ማለት ደግሞ ነብዩ( صلى الله عليه وسلم) የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል፣ ያዘዙትን መታዘዝ፣ ያወገዙትንና የከለከሉትን መከልከል እንዲሁም አላህ ከዚያም እርሳቸው በደነገጉት የአምልኮ ስርአት መሰረት ብቻ ማምለክ ማለት ነው።

②_ 
#ሰላት፦ በቀንና በማታ አምስት ጊዜ የሚፈፀሙ ሰላቶች(ስግደቶች)ናቸው። ሰዎች አላህ በባሮቹ ላይ ያለውን ሀቅ እንዲወጡ፣ ለፀጋዎቹም ምስጋና እንዲያደርሱ፣ ከአስፀያፊና ከተጠላ ተግባር ሁሉ እንዲርቁ ሰላትን ደነግጎላቸዋል። ሰላት በትክክል ከተከወነ በአላህ ፍቃድ ከዝሙትና ከፀያፍ ተግባር ሁሉ ይጠብቃል። በአንድ ሙስሊምና በጌታው መካከል አገናኝ ስለሆነም ሙስሊሙ በሰላቱ ውስጥ ጌታውን ይማፀናል በሚስጥርም ወደርሱ ዱዓ ያደርጋል።

አላህ የኢማን ጥንካሬና ፅድቅ እንዲሁም በዚህ አለምም ሆነ በመጪው አለም የሚገኝ መልካም ምንዳ ሰላትን ተከትሎ እንዲመጣ አድርጎል። እንዲሁም ታላቅ አካላዊና መንፈሳዊ እርካታን ይሰጣል። በዱንያም ሆነ በአኺራ ስኬታማ ያደርጋል።

③_ 
#ዘካ፦ ዘካ ማለት፤ ግዴታ የሆነበት ሰው በየአመቱ ለሚገባቸው ችግረኞችና ለሌሎች ዘካ እንዲወስዱ ለተፈቀደላቸው ሰዎች የሚከፍለው የግዴታ ምፅዋት ነው። አንድ ሰው ገንዘቡ የዘካ ኒሷብ(ዘካ ግዴታ የሚሆንበት አነስተኛው የገንዘብ መጠን) ላይ እስካልደረሰ ድረስ ዘካ ግዴታ አይሆንበትም። ግዴታ የሚሆነው በባለሀብቶች ላይ ሲሆን ይህም ሀይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና ኢስላማዊ ባህሪ በውስጣቸው እንዲያብብ ነው። ዘካን መክፈል ወንጀልን ያስምራል። በአንድ ሙስሊምና በንብረቱ ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ጥፋቶች አላህ ይጠብቀው ዘንድ ምክንያት ይሆናል። ለችግረኞችና ዕርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ፣ ብሎም ለማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ ነው። ከመሆኑም ጋር ለባለሀብቶች አላህ ከሰጣቸው ገንዘብና ንብረት ውስጥ መክፈል የሚገባቸው የዘካ መጠን በጣም ጥቂት ነው።

④_ 
#ፆም፦ ፆም ማለት በየአመቱ እንደ ጨረቃ አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር የተከበረውን ወርሃ ረመዳን መፆም ነው። በረመዳን በየቀኑ ጎህ ከቀደደበት ሰዓት ጀምሮ ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ በኢስላም ከተወሰኑ መሰረታዊ ፍላጎቶች(ከምግብና ከማጠጥ እንዲሁም ከስጋዊ ተራክቦ) በመቆጠብ የዓለም ሙስሊሞች በሙሉ በአንድ አይነት ሁኔታ ይፆሙታል። አላህም በዚህ መልካም ተግባራቸው ከችሮታው በጎን በመዋል፣ ዕምነታቸውን በመሙላትና ወንጀላቸውን በመማር ይክሳቸዋል። እርሱ ዘንድ ያላቸውን ደረጃ ከፍ ያደርግላቸዋል። እንዲሁም አላህ ለፆመኞች ካዘጋጀው የዱንያና የአኺራ መልካም ነገሮች ሁሉ ይቸራቸዋል።

⑤_ 
#ሐጅ፦ ሐጅ ማለት ወደ ተከበረው የአላህ ቤት(ካዕባ) ለየት ያለ ዒባዳ (አምልኮ) ለመፈፀም በተወሰነ የጊዜ ቀመር የሚደረግ ጉዞ ነው። ሐጅ በኢስላም ታላቅ ቦታ ያለው አምልኮ ነው። አቅም ባለው ማንኛውም ሙስሊም ላይ በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ አላህ ግዴታ አድርጎታል። ለሐጅ ስነስርዓት ሙስሊሞች ከመላው ዓለም በምድር ላይ ተመራጭና ቅዱስ በሆነው ስፍራ ይሰባሰባሉ። አንድ ዓይነት ልብስ በመልበስ አንዱን አምላካቸውን ያመልካሉ። በመሪና በሚያስተዳድራቸው ሰዎች፣ በሀብታምና በድሀ፣ በነጭና በጥቁር መካከል ልዩነት ሳይኖር በጊዜና በቦታ የተወሰኑ የሐጅ አምልኮ ተግባሮችን በአንድነት ያከናውናሉ። ከዋና ዋናዎቹ የሐጅ ተግባራት መካከል በዓረፋ መቆም፣ በተከበረው ካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግ እና ሰፋና መርዋ በተባሉት ተራራዎች መካከል መመላለስ ይገኙበታል። ሐጅ ለመቁጠርና ለመዘርዘር የሚያዳግቱ እጅግ ብዙ ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ጥቅሞች አሉት።

  (አላህ የላቀና ይበልጥ አዋቂ ነው)
የአላህ ሶለዋት ከፍጥረቱ ምርጡ በሆኑት፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸውም ይስፈን።

ኢላሂ እምነታችንን አጥርተን የምንይዝ አድርገን  
   የተውሂድና የኢኽላስ ባለቤቶችም አድርገን