2021-05-09 02:19:34
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#የልደትሽ_ቀን_ልደታችን_ነው
" እንኩዋን ለ2013 ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ "
"ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ:
ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::"
" ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን:
ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን)"
የብርሃናት ንጉሥ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውለድ ዛሬ የብርሃን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት ተወለደች ። ከሊባኖስ ተራሮች ርግብ ጸዐዳ ተወለደች ፤ በሔዋን ምክንያት የተዘጋው የሕይወት መንገድ ይከፈትልን ዘንድ የሕይወት እናት ዛሬ ተወለደች፡፡ የዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ከእርሷ ይወለድ ዘንድ እመብርሃን ዛሬ ተወለደች፡፡
የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኩዋ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::
ኢያቄም እና ሐና ዳግሚት ሰማይ ተብላ የተጠራችውን ድንግልን ወለዱ ፤ እውነተኛው ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ይወለድ ዘንድ እመ ፀሐይ (የፀሐይ እናት) ቅድስት ድንግል ዛሬ ተወለደች ፤ ብርሃንን ለማስገኘት መወለድ መታደል ነው፤ ከሰው ልጆችም መካከል መመረጥ ዕፁብ ድንቅ ነው፤ የመድኃኔዓለም እናት ለመሆን መወለድ ሰማያዊ ፀጋ ነው።
እመቤታችን ከአዳም ስሕተት በሁዋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. ፩÷፱)
ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ቀን: በሊባኖስ ተራራ ከ፪፻፳፮(2,026) ዓመታት በፊት ተወልዳለች::
"ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" (መኃልይ. ፬÷፰)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር::
ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ::
እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዳያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ፵ ቀናትም ሲጸልይና ሲማልድ ቆየ:: በ፵ኛው ቀን ፪ቱም ሕልምን ያልማሉ::
እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::
እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ፯ ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በ፯ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .
ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . ."
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. ፩÷፱)
✞ እመቤታችን ነሐሴ ፯ ቀን ተጸንሳ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች::✞
የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-
*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=
*በእናቷ:--ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::
*በአባቷ በኩል:--ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::
የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::
በእውነት እመብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ ናት። ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን እመብርሃን ዛሬ ተወልዳልናለችና በእዉነት ደስ ይበለን እልልም እንበል።"
- ወስብሐት ለእግዚአብሔር -
@Africagibigubae
@Africagibigubae
544 views23:19