2022-06-15 17:51:51
በስመ ሥሉስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እንዴት አላችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች።
ቸሩ አምላካችን ምስጋና ይድረሰው!
ቅዱስ ዮሐንስ ሳባ (አረጋዊ መንፈሳዊ) እንደጻፈው
ድርሳን 34
+ ወንድሜ ሆይ፡ ድንቅ ነገር እነግርህ ዘንድ እወዳለሁና ጸጥ ብለህ ስማኝ፡፡
+ አሳብህን ከመበታተን ሰብስበህ ስማኝ።
+ ልብህንም ከሥጋዊ ስሜት ለይ፡፡
+ እንዲህ የሆነ እንደሆነ በትሩፋት የተነገረውን ጸጋ ታገኛለህ፤ የዚህን ጸጋ መዓዛንም ታሸታለህ፡፡
+++ ሕፃናትን የፈጠረ ጌታ ትሕትናን የዕለት ጽንስ በመሆን እንደ ጀመረ እወቅ።
+++ ትህትናን ከእርሱ ተማር።
+++ ስላንተ የሠራውን ሥራ ሁሉ ታውቅ ዘንድ በትህትና ኑር፡፡
+++ በእርሱ አምሳል ይወልድህ ዘንድ በአንተ አምሳል ተወለደ፡፡
+++ በጨርቅ ተጠቀለለ፤ በተናቀ ቦታ በበረት አደረ።
+++ የሥጋ ብልጽግና እና የነፍስ ጸጋ መገኛ ሲሆን፡ ለዘላለም ነግሦ የሚኖር ንጉሠ ነገሥታት ጌታ በጨርቅ ተጠቀለለ ።
+++ የስደተኞች ማረፊያ የሚሆን እርሱን፡ እሽኮኮ ብለው ወደ ግብጽ አሸሹት።
+++ የሁሉ ደስታ የሚሆን ጌታን፡ ሄሮድስ ይገድለዋል ብለው እየፈሩ አሳደጉት፡፡
+++ መንግሥትን ሁሉ የሚሽር፤ መከራን የሚያሳልፍ እና ጸብ ክርክርን የሚያጠፋ
. እርሱን፡ የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደበት ሰው ከአገር አስወጥተው ሰደዱት።
+++ ሞትን የሚያጠፋ እርሱ ሲሆን፡ እንገድለዋለን ከሚሉት ፊት ሸሸ።
+++ ከተለዩ የተለየ፡ ከከበሩት የከበረ ሲሆን፡ አንተን ያከብር ዘንድ በውኃ
. ተጠመቀ።
+++ ልዕልናውንም አብ በዮርዳኖስ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክር ተሰማ።
+++ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍበት ታየ፡፡
+++ ይህም የሆነው ከአባቱ ጋር ያዋሕድህ ዘንድ አንተን ፈልጎ የመጣ እርሱ እንደሆነ ታውቅ ዘንድ፤ ከእርሱ ጋር በመኖርም በጎ ሥራ ብትሠራ ወደ አባቱ እንደሚያቀርብህ ትረዳ ዘንድ ነው።
+++ በትሩፋት መጋደልን እና ድል መንሳትን ያስተምርህም ዘንድ አርባ ቀን ጾመ።
+++ አንተ ቡሩክ ተብለህ ትመሰገን ዘንድ "የቡሩኩ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ"ብለው አይሁድ ዘበቱበት።
+++ በአጋንንት እጅ በኃጢአት በትር የተመታ የልቡናህን ራስ ያከብር ዘንድ ራሱን መቱት።
+++ የሰይጣንን ምክር ሰምታ የሚያሳዝን ኃጢአት የሰራች ሰውነትህን ጣዕም እንዲገኝባት ያደርጋት ዘንድ መራራ ከርቤን ጠጣ፡፡
+++ በዕፀ በለስ ምክንያት ከመጣ ሞት ያድንህ ዘንድ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፡፡
+++ ከመቃብር ያስነሳህ ዘንድ ወደ መቃብር ወረደ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣህም ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡
+++ ይህን ሁሉ ላደረገልህ ጌታ አንተ የምተሰጠው ምንድነው?
+++ ጌታህን በማየት ደስ ይልህ ዘንድ ትወዳለህን?
+++ ከሆነ የእርሱን ነገር በመናገር የምታደንቅ ብቻ አትሁን፡፡
+++ እንደ ዮሐንስና እንደ ጴጥሮስ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከተው እንጂ።
+++ ዘወትር ጌታህን በማሰብም ጸንተህ ኑር ።
+++ ይህን ካደረግህ፡ በእውነት ይገለጽልሀል፡፡
+++ የተወደደ ውብ መልኩን አይተህ ለማድነቅ ያበቃሀል።
+++ ነፍስህንም በበጎ ፍቅሩ ያቃጥላትል።
+++ በእርሱ ዘንድ ሞገስን ሰጥቶ ደስ ያሰኝሀል።
+++ እንደ እመቤታችን ማርያም በክንድህ እቀፈው።
+++ ሰውነትህም እንደ እመቤታችን የእርሱ ሞግዚት (አገልጋይ) ትሁን።
+++ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) እጅ መንሻውን ይዘው ወደእርሱ በመጡ ጊዜ
. ከእነርሱ ጋር እጅ መንሻህን አቅርብለት።
+++ ከእረኞችም ጋር መወለዱን ስበክ (አውጅ)።
+++ ምስጋናውን ከመላእክት ጋራ ዘምር።
+++ ወደ ቤተ መቅደስም ባገቡት ጊዜ እንደ ስምዖን በክንድህ ታቀፈው።
+++ ወደ ግብጽም በወረደ ጊዜ እሽኮኮ ብለኸው ውረድ።
+++ አቅፈኸውም ከዮሴፍ ጋራ ሂድ፡፡
+++ እንደ ምድረ ግብጽ በረሃ የሆነች ነፍስህን እንደ ኢየሩሳሌም በጸጋ ያለመልማት ዘንድ።
+++ ጌታ ኢየሱስን ከሕፃናት ጋር ሲድህ: ሰርቀህ ሳመው።
+++ በመዓዛው ደስ ይላት እንደ ነበረች እንደመቤታችን፡ ሁሉንም ሕያው
. የሚያደርግ የጌታን መዓዛ አሽት።
+++ እንደ እመቤታችን ያቅፈው የነበረ፡ በመዓዛውም ደስ ይለው የነበረ አንድን ሰው አውቃለሁ።
+++ ሕፃናትን መስለህ፡ ጌታ በሕፃንነቱ ጊዜ በሄደበት ቦታ ሁሉ ተከተለው፡፡
+++ ይህን ካደረግህ፡ ፍቅሩ በአንተ ታድራለች።
+++ ከእርሱ ጋራ አንድ በመሆንህም ይዳሰስ ከነበረና ከሕያው ሥጋው ያለ መዓዛን ከሟቹ ሥጋህ ታሸታለህ፡፡
+++ ጌታ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለ፡ የአይሁድ መምህራን በጠየቁት ጊዜና እርሱም በመለሰላቸው ጊዜ የቃሉን ጥበብ ሰምተህ አድንቅ፡፡
+++ ለማጥመቅ ከዮሐንስ ጋራ በአንድነት ኑር።
+++ በዮርዳኖስ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚለውን የአባቱን ምስክርነት ስማ።
+++ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ሲቀመጥበት እይ፡፡
+++ በሚጾምበትም ጊዜ ከእርሱ ጋራ ጹም፡፡
+++ ውኃዉን ለውጦ ወይን ባደረገ ጊዜ ጋኖቹን ውኃ እየሞላህ ተመልከት፡፡
+++ ከውኃው ጉድጓድ አጠገብ ከሳምራዊቷ ጋራ በተቀመጠ ጊዜ ያስተማረውን ትምህርት ስማ።
+++ እግዚአብሔር አብ የሚወደውን እና በመንፈስ የሚደረገዉን ስግደት "የሚሰግዱለትም በመንፈስ ይሰግዱለታል" ብሎ ሲያስተምር ስማ፡፡
+++ ሙታንንም ባስነሳ ጊዜ ትንሣኤ እርሱ እንደሆነ ዕወቅ፡፡
+++ ኅብስቱንም ባበረከተ ጊዜ እንቅቡን ይዘህ ለተሰበሰቡት አድል።
+++ ወደገዳም በሔደ ጊዜ ሔደህ ሸኘው።
+++ በሚያስተምርበት ቦታ፤ በመርከብ ውስጥም፤ በበረሃም ከእርሱ ጋራ ኑር።
+++ ወደ ደብረ ዘይት ከእርሱ ጋር አብረህ ውጣ።
+++ በምኵራብም “እኔ ግን እላችኋለሁ…” እያለ ሲያስተምር ስማ።
+++ በኃጢአት ለሞተው ማንነትህ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ከአልዓዛር ጋር ወደ መቃብር ግባ።
+++ እንደ ኃጢአተኛዪቱ ሴት በእንባህ እግሩን እጠበው፤ በጸጉርህም አብሰው (ሉቃ. 7፡ 38)፡፡
+++ “ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” ሲልህ ትሰማለህ።
+++ በማዕድ ጊዜም እንደ ዮሐንስ ባጠገቡ ተቀመጥ፡፡
+++ ኅብስቱን ባርኮ “ይህ ሥጋዬ ነው” ባለ ጊዜ ከእጁ ተቀበል።
+++ የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበ ጊዜ ከኃጢአት ያነጻህ ዘንድ ቀርበህ እጠበኝ በለው፡፡
+++ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ሰውነትህን ንጹሕ አድርገው፡፡
+++ ዘወትር እርሱን ለማመስገን የተጋህ ሁን፡፡
+++ በምግባር በሃይማኖትም ያጌጥህ ሁን፤ የመንፈስ ቅዱስን ነገር ለመማር የበቃህ ትሆን ዘንድ፡፡
+++ ከእርሱ ጋር መከራን ተቀበል፡፡
+++ ስለጌታህ ስድብን፤ መናቅን፤ የምራቅ መተፋትን እና በሚስማር መቸንከርን በጸጋ ተቀበል።
+++ ከእርሱ ጋር በመስቀል ተሰቀል፡ ከእርሱም ጋር ሙት፤ እርሱ እንደተነሣ ትነሣ ዘንድ (ሮሜ 6፡5)።
+++ ሰውነትህ (ነፍስህ) እንደ ማርያም መግደላዊት በፍርሀት ሁና ከመቃብሩ አጠገብ ትቁም።
+++ መላእክት “ምን ያስለቅስሻል?” ብለው ይጠይቋት ዘንድ።
+++ የምትወደውን ጌታ ባየችውም ጊዜ የአትክልት ጠባቂ መስሏት “ጌታዬን ወዴት ወሰድከው?” ብላ
እንደጠየቀችው ትጠይቀው ዘንድ (ዮሐ 20፡ 15)።
+++ ያን ጊዜ እንድታውቀው ሆኖ ያናግራታል።
+++ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት በገባ ጊዜ ተነሥተህ ተቀበለው።
+++ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ “ልጆች፡ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” (ዮሐ 21፡5) ብሎ በጠየቀ ጊዜ ጴጥሮስን ምሰለው።
+++ መላእክት ያዘጋጁትንም ማዕድ ከእርሱ ጋር ተመገብ (ዮሐ. 21፡9)።
172 viewsMule negn, 14:51