Get Mystery Box with random crypto!

''አስመሳይ ህዝብ '' ራሱ የደገሰውን የመከራ ድግስ እየተቋደሰ ለመኖር ይገደዳል! ብዙ ጊዜ ከአ | ዘሪሁን ገሠሠ

''አስመሳይ ህዝብ '' ራሱ የደገሰውን የመከራ ድግስ እየተቋደሰ ለመኖር ይገደዳል!

ብዙ ጊዜ ከአንዳንድ ጓዶች ጋር ተወያይተን በሀሳብ የምለይበት ''ህዝብ ድብን አድርጎ ይሳሳታል!'' በሚለው አቋሜ ፅኑ ነው። አቶ ልደቱ በዚህ ረገድ ከነአመክንዮዎቹ ባቀረበው ሀሳብ የምስማማውም ለዚያ ነው።

በሌላ መልኩ ህዝብን የሚፈጥረው ፈጣሪ ቢሆንም የህዝብን ማህበረሰባዊ ስነ-ልቦናና እሳቤ የሚቀርፀው ግን የፖለቲካ ኢሊቱ ነው ብዬም አምናለሁ። ከዚህ አኳያ በአሉታዊም ሆነ በአወንታዊ መልኩ የህዝብን ስነልቦናና አስተሳሰብ በመቅረፅ ረገድ የፖለቲካ ኤሊቱ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል ማለት ነው።

በመሆኑም ብልሹ የፖለቲካ ሀይል የተበላሸ የፖለቲካ ማህበረሰብና ባህል የመገንባት እድሉ ከፍተኛ ነው። በተለይ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ኤሊት ስብስብ ለረዥም ጊዜ የህዝብን ስልጣን ይዞ የመቆየት እድል ካገኘ ፣ የራሱን መገለጫና ባህሪያት የፖለቲካ ማህበረሰቡ (የህዝቡ) ልማድ ወይም ባህል አድርጎ የማስረፅ ኃይል ያገኛል። በጥቅሉ የአፍሪካ ወረድ ስንል የኢትዮጵያችን ፖለቲካ ፣ በተመሳሳይ የብልሽትና ኃላቀር ፖለቲካዊ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቆ ለዘመናት የሚሽከረከረውም ለዚያ ነው።

የፖለቲካ ቡድኖቹ ተራማጅና ለትውልድ የሚተርፍ በጎ የፖለቲካ አስተሳሰብ ይዘው ከመጓዝ ይልቅ ፣ የሚነሱት ከእነሱ በፊት የነበረውን ሀይል ሞዴል አድርገው ነው። ለአብነት ህወሓትን ሞዴል አድርጎ የተነሳው ''ብልፅግና'' የፈለገ ስሙንና ድስኩሩን ቢቀያይረውም ፤ በግብር ግን ሞዴል አድርጎ ከተነሳው (ከቀራፂው) ህወሓት በእጅጉ ልቆ የተገኘ ነው። በሀገራችን ፖለቲካ ትናንት ከነበረው ተሽሎ መገኘት ማለት ይህ ነው። ክፉ ከነበረው በጣም ክፉ ሆኖ መገኘት....

ወደዋናው ነጥቤ ስመለስ ፣ ከላይ እንዳልኩት ከሰላሳ አመት በላይ በህዝብ ስልጣን ላይ የመቆየት እድሉን ያገኘው ''ብአዴን'' አብዛሀኛዎቹ እኩይ መገለጫ ባህሪያቶቹን በህዝቡ (የፖለቲካ ማህበረሰቡ) ውስጥ ተክሏቸዋል። ነባር ህዝባዊ እሴቶችና ስነልቦናዊ ውቅሮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፣ በውድም ሆነ በግድ ሸርሽሯቸዋል። በአጭሩ ከሞላ ጎደል ፣ ''ህዝብ'' በሚባል ደረጃ ''ብአዴናዊ'' አስተሳሰብ ያለው የፖለቲካ ማህበረሰብ ተፈጥሯል።

<< ብአዴናዊነት ምንድን ነው? >> የሚለውን ጥያቄ አብዛኛው የሚያውቀው በመሆኑ በዚህ አጭር ፅሁፍ አላብራራውም። ነገርግን የተሻለ ነገን ለመፍጠር ፣ የትውልዱን መፃኢ እጣፋንታ ተራማጅና ስልጡን ፖለቲካዊ እሳቤ የተመላበት የማድረግ አላማን አንግቦ ፣ << በማንኛውም መልኩ ለህዝብ እታገላለሁ ! >> የሚል የፖለቲካ ኤሊት (ፓርቲ ወይም አደረጃጀት ) ፣ ከተጋባን የብልሽት ፖለቲካ አዙሪት ባሻገር መመልከትና አርአያና ሞዴሎቹንም የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ከገነቡት አድርጎ በመውሰድ ፣ ለስር-ነቀል ለውጥ መታገል አለበት ባይ ነኝ!

ለመውጫ ግን ፦ ያኔ በሊቢያ በረሀ ኢትዮጵያውያን ሲታረዱ ፣ ድፍን ኢትዮጵያ ማቅ ለብሳለች ፣ ሀገር የብሄራዊ ሀዘን አውጃ አምብታለች ፣ ህዝብ ያለአንዳች ጎትጓች በመላ ሀገሪቱ ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሞና የሀዘን ሰልፎች አድርጓል።

ወዲህ መለስ ስል ፣ ያለፉትን አምስት አመታት አይኤስ ከፈፀመው በላይ የከፋ የዘር ፍጅትና እልቂት ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን (በአብዛኛው በአማራ ህዝብ) ላይ ፈፅመዋል ፣ በመፈፀም ላይም ናቸው። ከሰሞኑ እንኳ በቪዲዮ ከማይቀረፀው ህልቆ መሳፍርት ፍጅት ባሻገር ፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ልክ አይ ኤስ ሊቢያ ላይ እንዳደረገው ሁሉ ፣ የመንግስት ወታደሮች ንፁሀንን የፊጥኝ አስረውና አሰልፈው ሲረሸኑ በቪዲዮ ቀርፀው ልባችንን ደም እምባ እያስለቀሱት ይገኛሉ!

ታዲያ! ያ ሩህሩህና የኢትዮጵያውያን ሞት ያስቆጣው ህዝብ ወዴት ገባ ? የአምስት አመቱስ ይሁን ፥ የሌሎች ህዝቦችና ኢትዮጵያንም ከነመንግስቷ እርሷት ፣ ኧረ የአማራ ህዝብ አሁን እንኳ ከምን ገብቶ ይሆን ?

ስጀምር በመግቢያዬ <<አስመሳይ ህዝብ ራሱ የደገሰውን የመከራ ድግስ እየተቋደሰ ለመኖር ይገደዳል! >> ማለቴ ለዚያ ነው!