Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ የዜጎች ፈተና ሆኖ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት ፥ በቀጣይ ወራት አሁን ከሚገኝበት በ50% ሊ | ዘሪሁን ገሠሠ

በኢትዮጵያ የዜጎች ፈተና ሆኖ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት ፥ በቀጣይ ወራት አሁን ከሚገኝበት በ50% ሊያድግ ይችላል!

በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችውና የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላት ናይጄሪያ   ፥ ማዕከላዊ ባንኳ የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሆነውን  ናይራ/ naira የመግዛት አቅም የማዳከም እርምጃ ከወሰደበ በኃላ  ፥  የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ወር ከነበረበት 21.91 በመቶ ወደ 22.04 በመቶ ማደጉን የስታስቲክስ ቢሮው ዛሬ ቅዳሜ  ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ዜጎቿ እየተሰቃዩ የምትገኘው ኢትዮጵያ ፥ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ለመጣው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት  ፥ የሀገሪቱ መንግሥት ካለፉት አመታት ጀምሮ የብርን የመግዛት አቅም በተከታታይ በማዳከሙና በየጊዜው እያተመ ወደኢኮኖሚው ስርአት የሚያስገባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የገንዘብ ኖት በመሠረታዊ ምክንያትነት ሲጠቀሱ ቆይተዋል፡፡

ሠሞኑን ኢትዮጵያ በታሪኳ በአንድ ጊዜ የጠየቀችውን የ2 ቢሊየን ዶላር ብድር ፥ ሂደት አስቻይ ሁኔታዎች ለመገምገም አዲስአበባ የሰነበቱት የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የአለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት አስተያየት ፥ ሀገሪቱ ካለባት ያልተከፈለ ከፍተኛ ብድር  አንፃር አሁን የተጠየቀውን ብድር የሚፈቅዱት ከዚያ አኳያ ገምግመው መሆኑን ጠቅሰው  ፤ ነገርግን  ብድሩን ሙሉ በሙሉም ሆነ የተወሰነውን ቢፈቅዱ እንኳ በቅድሚያ የሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ "ብር/birr " የመግዛት አቅም አሁን ካለበት በ50% ማዳከምን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ማስቀመጣቸው ታውቋል፡፡

እንግዲህ ይህ የአለም ባንክ ቅድመ ሁኔታ ከተተገበረ ፥ የ1 ዶላር ዋጋ አሁን በሀገሪቱ ባንኮች ከሚሸጥበት 54 ብር ገደማ በቀጥታ ወደ መቶ ብር ማደጉ ይጠበቃል፡፡ የሀገሪቱ የወጭ ንግድ ከውጭ ከምናስገባው አንፃር 1/3ኛ እንኳ የማይሸፍን ሆኖ ባለበት ሁኔታ ፥ የብርን የመግዛት አቅም በ50% ማዳከም ማለት አሁን ለህዝቡ ፈተና ሆኖ የሚገኘውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት በአንድ ጊዜ በ50% መጨመር እና በቀጥታ ግሽበቱን ወደ Hyper Inflation ደረጃ ማሸጋገር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በቀላል ስሌት በዶላር የምንገዛው ነዳጅ አሁን ካለበት ዋጋ 50% ሲጨምር ፥ በሀገሪቱ የሸቀጦች ዋጋና መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ መገመት የሚያዳግት አይሆንም፡፡

ከወር በፊት በወጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ድርጅቶች "ምርቶቻችንን ለአለም ገበያ በርካሽ ዋጋ እያቀረብን ከውጭ በውድ ገዝተን ከማስገባት  ይልቅ በሀገር ውስጥ ገበያ መሸጥ ያዋጣናል " ብለው ስራ ወደማቆም የገቡበትን አጨቃጫቂ ሁኔታ መዘገቤ ይታወሳል፡፡

እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ወደስልጣን በመጡ በወራት ውስጥ የብርን የመግዛት አቅም ያለበቂ ጥናት በተከታታይ የማዳከምና ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኖት ፥ ከሀገሪቱ ብሄራዊ ባንክ በማይመለስ ብድር መልክ እየታተመ ወደኢኮኖሚ ስርአቱ እንዲገባ የማድረግ እርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ ፥  በመላ ሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ለተከታታይ አመታት ፈታኝ እንደሆነ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በአሁኑ ሠአት ሀገሪቱ ያላት የዶላር ክምችት ለ15 ቀን እንኳ የማይበቃ መሆኑና በከፍተኛ የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ እንደምትገኝ ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች አመላካች ናቸው፡፡

"በእንቅርት ላይ ጆሮገድፍ" ማለት ይኸው ነው!