Get Mystery Box with random crypto!

የአማራው የፖለቲካ ኃይል ከፍዝ ተሳታፊነት ወደመሪነት መጥቶ ትግሉን ወደጡዘት ደረጃ ካላሳደገው | ዘሪሁን ገሠሠ

የአማራው የፖለቲካ ኃይል ከፍዝ ተሳታፊነት ወደመሪነት መጥቶ ትግሉን ወደጡዘት ደረጃ ካላሳደገው ህዝቡን እስከወዲያኛው ያስበላል!

እኔ ከብዙ ጓዶች ጋር የማልግባባው ፥ በአማራ የጥላቻ ትርክት ላይ ተመስርቶ በጦዘውና ፥ የአማራን ህዝብ ማዕከል ባደረገ የእለት ተእለት ሀገር አፍራሽና አሰቃቂ ትእይንት በታጀበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፥ " የአማራ ፖለቲካ መስከን አለበት" ከሚል ፥ በገዛ ድግሱ ፍዝ ተመልካች ከሚያደርገው አስተያየት አልፈው "መፍረስ አለበት" ወደሚል ከነአካቴው ከጨዋታው የሚያስወጣውን አስተያየት ሲሰጡ ስመለከት ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ፅንፍ የረገጠውና አማራን መጥላት የፖለቲካ ማደራጃ ያደረገው የብሔር ፖለቲካ በምኞት የማይቆምና የሀገሪቱ የፖለቲካ አሰላለፍ ሆኖ መቀጠሉ እሙን ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ከዘመናት "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ" ከሚል ሰሚ አልባ ጩኸት ነቅቶ በቅርቡ "አማራ ነኝ" ወደሚል መስመር የመጣው ፥ እንደህዝብ ወቅቱ በሚጠይቀው የፖለቲካ አሰላለፍ ተደራጅቶ አለመታገሉ ፥ ለሀገር ቀና አሳቢነቱን ለማስቀጠልም ሆነ የራሱን ህልውና ለማስከበር እንዳይችል አድርጎ በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ በመውደቁ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዋናነት ፥ የፅንፈኛ የብሄር ድርጅቶች በጠላትነት ፈርጀው ፥ በመኖር አለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱት "የአማራ ህዝብ" ልክ በስነፅሁፍ ውስጥ << ዋና/መሪ Protagonist >> በምንለው ገፀ-ባህሪይ የሚወከል ሲሆን ፥ አማራን በማጥፋት ፣ በመጥላትና የአማራ የሆነውን ሁሉ በማፍረስ ላይ የተጠመዱት ኦነግና/ትህነግን መሠል ፅንፈኛ የተቃርኖ የብሔር ፖለቲካ አደረጃጀቶች ደግሞ " ተቃዋሚ/አፍራሽ/ Antagonist" በሚለው መጠሪያ ይወከላሉ፡፡ ሌሎቹን ህዝቦች በመፅሐፍ ወይም በፊልም ታሪክ ውስጥ በተዋረድ የምንመለከታቸውን የገፀ-ባህሪያት ስያሜ ልንሰጣቸው እንችላለን፡፡

ታዲያ! የአንድ የመፅሀፍ ታሪክ ውስጥ Antagonist ገፀ-ባህሪያቱ ፥ ያለእረፍት ሊያጠፉት ፥ የሱ የሆነውን ሊወስዱበት ፣ ተስፋውን ሊያጨልሙበትና ከአላማው ሊያሰናክሉት ሲተጉ ፥ የታሪኩ ዋና/መሪ Protagonist ገፀ-ባህሪ የሆነው አካል ደግሞ ከዚህ ሁሉ ጥቃት ፣ በደልና መሳደድ አምልጦ አላማውን ለማሳካት ፥ ከ Antagonist ገፀ-ባህሪያቱ ጋር የሚመጥን ብቻ ሳይሆን የሚበልጥ ትግልና ትንቅንቅ ማድረግ አለበት፡፡ ይህን በሁለቱ ገፀ-ባህሪያት መካከል የሚደረግና በፈጣን የድርጊትና የግብግብ ክዋኔ የተሞላ ሁነት rising action ስንለው ፥ ከጫፍ /Climax ደረጃ ላይ ሲደርስ "ጡዘት" እንለዋለን፡፡ ከዚያ ግብግብ በኃላ መሪ ገፀ ባህሪው አሸናፊ እየሆነና ውስብስቡ ችግር መፍትሄ እያገኘ ፥ ድርጊቱም እየረገበ ሲመጣ falling action እንለዋለን፡፡

በቃ! በአሁኑ ሠአትም የአማራ ፖለቲካ መሆን ያለበት እንዲህ ነው፡፡ በዚህ ልክ ወደረኞቹን የሚመጥን የፖለቲካ ትግል ማድረግ ካልቻለ ፥ ለሀገሩም ሆነ ለራሱ የማይሆን ብሎም ለጠላቶቹ መተወኛ መድረክ ብቻ ሆኖ የሚያገለግል ፥ የገዛ ድግሱን የተቀማ ደጋሽ/ባለቤት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው!

አዎ! የአማራ የፖለቲካ ኃይል ሚናውንና ግቡን ለይቶ በአውዱ ልክ እንደውም ከፍ ብሎ መጦዝ ካልቻለ ፥ ኃላ በራሱ የመኖር ያለመኖር ትንቅንቅና የሀገር ባለቤትነት ዙሪያ ፥ የታሪክ ዶሴው ሲከተብ ፥ ትርጉም የሌለው የአጃቢ ገፀ-ባህሪን ወክሎ መቅረቡ ምንም አያጠራጥርም!