Get Mystery Box with random crypto!

የዳግማዊ ዘመነ-መሳፍንት ማብቂያው መቼ ይሆን ? 'የስልጣን ጥም ግን እጅግ ክፉ በሽታ ነው!' | ዘሪሁን ገሠሠ

የዳግማዊ ዘመነ-መሳፍንት ማብቂያው መቼ ይሆን ?

"የስልጣን ጥም ግን እጅግ ክፉ በሽታ ነው!"

ከ1769 – 1855 ድረስ ለ86 አመታት የዘለቀው ፥ በታሪክ ውስጥ "ዘመነ-መሳፍንት" እየተባለ የሚወሳው ዘመን ፥ ኢትዮጵያና አስተዳደራዊ ስርአቷ የተዳከመበት ፥ የእርስበርስ ጦርነትና መከፋፈል መገለጫው የነበረበት ፥ መሳፍንቱና መኳንንቱ በአውራጃ ተከፋፍሎ " አንጋሽና አውራጅ ወይም ሿሚና ሻሪ" ለመሆን በስልጣን ሽኩቻ አንዱ አንዱን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሠራበት ፥ በጥሩ ጎኑ የማይነሳ ጊዜ ነበር፡፡

ሁሉም መኳንንቶችና መሳፍንቶች አንዱ ሌላኛውን አሸንፎ ዘውዱን ጭኖ ለመንገስና "ሿሚና ሻሪ" የሚያደርግ ስልጣን ለማግኘት እርስበርስ ተራኮቱና ሀገርሪቷንም ሲያዳክሙ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ክፍፍሉም ፣ ጦርነቱም ፣ ሽኩቻውም ፣ …. የዘር ፣ የሀይማኖት ወይም የጎጥ የበላይነት ለመቀዳጀት ሳይሆን ፥ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ ለመግዛት የሚደረግ የስልጣን ጥም ነበር፡፡ መሳፍንቶቹ የሸዋው ከወሎው ፥ የጎጃሙ ከጎንደሩ ፥ የትግሬው ከኦሮሞው ፣ … ሲያደርጉት የነበረ የስልጣን ቅርምት ነበር፡፡

ታዲያ! ዛሬ " አንድ አርገን ናና…!" የምንለው ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ " በዘመነ መሳፍንት ማቀብቂያ በ1847 የካቲት 11 ቀን ነገሰ፡፡ ያንን የ86 አመታት የእርስበርስ ትርምስና የመገዳደል ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፋይሉን መዝጋት የቻለው አባ ታጠቅ ካሳ ነበር!

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በ13 አመታት የንግስና ዘመኑ የኢትዮጵያን አንድነት መልሷል ፥ ሩቅ አስቦ ከቅርብ ቢያድርም ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ታላቅ ሰው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ዘመነ-መሳፍንት ማክተሙ ቢገለፅም ፥ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በንግስና ዘመኙ ከባድ ፈተናና ውጣውረድ ሲያሳዩት የነበሩት አኩራፊ መኳንንትና መሳፍንቶች እንደነበሩ ግልፅ ነው፡፡ ናፒየር የተመራው የእንግሊዝ ወራሪ ሰራዊት አፄ ቴዎድሮስን ለመዋጋት ወደኢትዮጵያ ሲገባም በወቅቱ በሽፍትነትም ሆነ በአውራጃ ገዢነት ላይ ከነበሩ መኳንንቶች ጋር ስምምነትና አወንታዊ ድጋፍ ማግኘቱም በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ያም ሆኖ ግን ሽኩቻቸው አንዱ አንዱን ጥሎ ለመንገስ እንጂ በሀገር ጉዳይ ፈፅሞ አይደራደሩም ነበር፡፡ ይህን ለመረዳት እንግሊዞች በወቅቱ ወደመቅደላ ሲገሰግሱ "የወንድ በር" ለማግኘት ሲሉ ፥ በሽፍትነት ካሉት የቴዎድሮስ ተቀናቃኞችን " የመጣነው ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ሳይሆን የታሰሩብንን ሚሲዮናውያን አስፈትተን ለመመለስ ብቻ ነው!" በማለት እንዳግባቧቸው በታሪክ ተፅፎ የምናገኘው ፥ እንግሊዞች ኢትዮጵያውያኑ በምንም መልኩ በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ስለገባቸው ይመስለኛል!

በጣም የሚያሳዝነው የስልጣን ሽኩቻ የወለደው የዘመነ-መሳፍንት ፖለቲካዊ ባህሪይ ፥ አዳዲስና አስከፊ ገፅታዎችን ጭምር ተላብሶ ፥ በዚህ ዘመን ፖለቲከኞችና መሪዎች ላይ መገለጫ ባህሪ ሆኖ መመልከታችን ነው፡፡ ታሪክ በታሪክነቱ ይዘከራል ፥ ይወሳል፡፡ ትውልዱ ከጥሩው ታሪክ ይማራል ፥ ከክፉው ታሪክ እንዳይደገም ይማራል፡፡ ይህ የሚያጣላና እርስበርስ የሚያባላ ሊሆን ባልተገባም ነበር፡፡ አቶ ኢብራሒም ሙሉ ሸዋ በአንድ ወቅት ‹‹የሚያጣላን የፖለቲካ ታሪክ ሳይሆን የታሪክ ፖለቲካ ነው›› ሲል የገለፀውን ሀሳብ የምጋራውም ለዚህ ነው፡፡

የዘመነ-መሳፍንት የፖለቲካ ታሪክ ሊያጣላንም ሆነ አጀንዳችን ሊሆን ባይችልም ፥ በዘመነ መሳፍንት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የነበረውን የስልጣን ሽኩቻና የእርስበርስ ክፍፍል እንደመገለጫ ባህሪ አድርገው ዛሬ ላይ ለስልጣን ጥማት ማርኪያ ሲሉ ህዝብን ከህዝብ ፥ አንዱን መንደር ከሌላኛው ፥ አንዱን ሀይማኖት ከሌላው ሀይማኖት ፥ እያናከሱና እያጋጩ በደም የጨቀየች ፥ አንድነቷ የላላና ድህነትና ኃላቀርነት የተጫናትን ሀገር እየፈጠሩ ያሉት የዳግማዊ ዘመነ-መሳፍንት ፖለቲከኞቻችን ግን ግንባር ቀደም የዚህ ዘመን የሀገርና የህዝብ ፀር ብሎም የታሪክ ተጠያቂዎች ናቸው!

አብዛሀኞቻችን ዳግማዊው ዘመነ-መሳፍንት እስከወዲያኛው ያበቃ ዘንድ ፥ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ዳግም ውልደት የምንመኘው ! "አንድ አርገን ናና ..!" ስንልም የቴዎድሮስን መንፈስ የምንማፀነው ለዚያ ነው!

<< አንድ አርገን ናና….! >>