Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሉ ? ማነው ብሔር ? ማንኛውስ ነው ብሔረሰብ ? | ዘሪሁን ገሠሠ

ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሉ ? ማነው ብሔር ? ማንኛውስ ነው ብሔረሰብ ? ህዝብስ ማን ነው?

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከደቂቃዎች በፊት ፥ ሀዋሳ የሚከበረውን " የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን" አከባበር አስመልክቶ ለኢቢሲ መረጃ ሲሰጡ << …76ቱም ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን ፣ አለባበሳቸውን ፣ አመጋገባቸውን ፣ ….ወዘተ የሚያሳይ ዝግጅት አድርገው ሀዋሳ ይገባሉ! >> የሚል አይነት መግለጫ ሲሰጡ የመጣብኝ ጥያቄ ነው፡፡

በኢትዮጵያዊያ ውስጥ ወያኔ ይዞት ከመጣው የብሔር ፖለቲካና ይህን ተከትሎ ለፖለቲካ ፍጆታ ከሚከበረው "የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን" በፊትም ሆነ በኃላ በርካታ ብዘሀነት ፣ ባህል ፣ ወግ ፣ ቋንቋ ፣ አኗኗር ፣ ወዘተ ያላቸው ህዝቦች እንደሚኖሩ የታሪክ ፀሀፍቱም ፣ ከያኒውም ጎብኚውም ሲገልፅ እናውቃለን፡፡ ህገ-መንግስቱ የሚያውቃቸውም የማያውቃቸውም እንዳሉ ታዝበን አልፈናል፡፡ የተወለዱም የሞቱም "ብሔርና ብሔረሰቦች" እንደነበሩ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ትምህርት ቤት "ኢትዮጵያ ከ83 ብሔርና ብሔረሰቦች አሏት!" ተብለን ስንማር አድገናል፡፡

ለመሆኑ ግን በኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም ሆነ "ህገ-መንግስት" የሚሉት የሀገር ማፍረሻ ውል የሚያውቃቸው " ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች" ስንት እንደሆኑ እርግጠኛ ሆናችሁ ታውቁታላችሁ ? ብሔር ማንኛው ነው? ብሔረሰብስ ? ህዝቦችስ ? ልዩነትና አንድነቱስ ምንድን ነው ?

የህግ-ባለሙያው ወንድማችን - Wubishet Mulat - ውብሸት ሙላት የዛሬ 5 አመት ገደማ ይሄን እኔ ያነሳሁትን ጥያቄ በአንድ ፅሁፉ አንስቶት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ውብሸት ከተለያዩ ምንጮች አሰባስቦና ዋቢ ጠቅሶ ካሰፈረው ፅሁፉ ውስጥ ተከታዩ ይገኝበታል ፦

- በደርግ ፦

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ተቋም ጥናት ውጤት ላይ መረዳት እንደሚቻለው 89 ናቸው፡፡ ነገር ግን ጥናቱ 89 ብቻ አለመሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ታሪካቸው በአጭሩ የተጻፈው የ75ቱ ብቻ ሲሆን የሌሎቹ ግን ስማቸው ብቻ ተዘርዝሯል፡፡

-በሽግግር ወቅት ፦

☞ በ1984 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 7/84 ላይ 63 ብቻ ተዘርዝረዋል፡፡

☞ በ1987 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝብ ቤት ቆጠራ እና የፌደሬሽን ምክር ቤት በሕዝብና ቤት ቆርራው ሪፖርት መሠረት 84 ተቆጥረዋል፡፡

☞ የፌደሬሽን ምክር ቤት መቀመጫ የነበራቸው ደግሞ 67 ብቻ ነበሩ፡፡

☞ ከ1993 ጀምሮ በነበረው የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ወደ 76 ከፍ ያለ ሲሆን ፤ በ2008 ዓ.ም ሥራውን የጀመረው የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ መቀመጫ ያላቸው 77 ናቸው፡፡

- በ1999 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝብና ቤት ቆጠራ

በዚህ ጊዜ በተደረገው ቆጠራ ደግሞ 85 ሲሆን በ1987 ላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አምስቱ ያልተካተቱ ሲሆን ሌሎች ስድስት ግን ተጨምረዋል፡፡ አምስት “ሞተው” ስድስት “ተወልደዋል” ማለት ነው።

"መብታቸውን መልሻለሁ!" የሚል መንግሥት ያላት ፣ የአብዝኃኛው አገራዊ እና መንግሥታዊ መዋቅሮቻችን መሠረታት "ብሔር" የሆኑባት ፥ " የብሔሮች ፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን" የምታከብር ፤ ነገር ግን ብዛታቸውን እንኳን በቅጡ የማታውቅ ሀገር - ኢትዮጵያ!

" በኢትዮጵያ ስንት ብሔሮች ፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ይገኛሉ?" ቢባል በትክክል ማንም መመለስ የሚችል ያለ አይመስለኝም፡፡

ሠላም!