Get Mystery Box with random crypto!

++ ጌታ ሆይ እኔ እሆንን? ++ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ፊት በዚያች ምሽት በጭንቀት ቆመዋል፡፡ ከእ | መንፈሳዊ ትረካ እና አጫጭር ጽሑፎች

++ ጌታ ሆይ እኔ እሆንን? ++

ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ፊት በዚያች ምሽት በጭንቀት ቆመዋል፡፡ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሠጠኛል ብሎ ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ተጨንቀዋል፡፡ ጌታ ሆይ እኔ እሆንን? እያሉ ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ተራ በተራ ጠየቁት፡፡

የቀሩት ሊሸጠው ተስማምቶ የመጣው ይሁዳና ወንጌላዊው ዮሐንስ ናቸው፡፡ ይሁዳ እኔ እሆንን ማለቱ ልቡ እያወቀ ስለነበር ከዐሥሩ ጋር አብረን አንቆጥረውም፡፡ ዮሐንስ ደግሞ ለጌታ ካለው የፍቅር ጥልቀት የተነሣ እኔ እሸጠው ይሆን? የሚል ሥጋት ስላልነበረበት ‘’ጌታ ሆይ አሳልፎ የሚሠጥህ ማነው?’’ አለ እንጂ እኔ እሆንን አላለም፡፡ የሐዋርያቱ የጭንቀት ጥያቄ በማግሥቱ መልስ አግኝቷል፡፡ ሆኖም ይህንን ትሕትና የተሞላ ጥያቄያቸውን ለእኛ ሳይበጅ አይቀርም፡፡

በዙሪያችን ለተደረጉ ፣ ለሚደረጉ ክፉ ነገሮች ሁሉ ምክንያቱ ምንድር ነው? ጥፋቱ የማን ነው? መነሻው ምንድርን ነው? ብንባል ሁላችንም ጣት የምንቀስርበት ሰው አናጣም፡፡
አዳም ዕጸ በለስን ለመብላቱ ‘’ም ክን ያቴ ሔዋን ናት ‘’ አለ
ሔዋን ‘’ዕባብ አሳተኝ ‘ አለች
ዕባብም ጠያቂ ቢያገኝ ሰይጣን ማለቱ አይቀርም ነበር፡፡
አንዳቸውም ‘’ጌታ ሆይ እኔ እሆንን?’’ ማለት አልቻሉም፡፡ እንደ ዳዊት ‘’እኔ መተላለፌን አውቃለሁ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊትህ ነው’’ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ለሚሆኑ ነገሮች ሁሉ የምንከስሰው ሰው አናጣም:: መፍትሔው ግን ራስን ማየት ነው:: "እስመ አዕይንቲሁ ለጠቢብ ዲበ ርእሱ" (የጠቢብ ዓይኖቹ በራሱ ላይ ናቸው) እንዲል

ቅዱሳን በምንም ነገር ራሳቸውን ይወቅሱ ነበር:: በገድላቸው ብዛት በሚጸልዩበት ሥፍራ ዶፍ ዝናብ እየወረደ ሳለ እርሳቸውን እንዳይነካቸው በቆሙበት ሥፍራ እንዳይዘንም ያደረገላቸው ዳግማዊው ኤልያስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉትን እናስታውስ:: በቆሙበት ሥፍራ ዝናም እንዳልዘነመ ሲያዩ "ይህችን መሬት በኃጢአቴ ዝናም አስከለከልኳት" ነበር ያሉት:: ጌታ ሆይ እኔ እሆንን? ማለት ይህም አይደል?

የሙሴ ወንድም አሮን በእስራኤል ግፊት ጣኦት ሠራ፡፡ ከወርቅ አቅልጦ ጥጃ አምላክ አድርጎ ሠራላቸው፡፡ ከሠራ በኋላም መሥዋዕት ለጣኦቱ አቀረበ፡፡
ሙሴ መጥቶ ሲቆጣ ሲያይ ግን አሮን ፈራና በሕዝቡ አሳበበ የራሱን ድርሻ በተመለከተ ግን እንዲህ አለ
‘ወርቅ ሰጡኝ በእሳት ላይ ጣልሁት ይህ ጥጃ ወጣ’ {ዘጸ 32፡24}
ራሱ ከእጃቸው ተቀብሎ በመቅረጫ ቀርጾ የሠራውን ጣኦት ‘ስጥለው ጥጃ ሆነ’ አለ፡፡ ራሱ ሕዝቡን ‘ስድ ለቅቋቸው’ የነበረ በመሆኑ ‘’ጌታ ሆይ እኔ እሆንን?’’ ብሎ ራሱን ሊከስስ ይጠበቅበት ነበር፡፡

በትምህርት ቤት ሕይወታችን የማይረሱ ቀናት ግሬድ የሚለጠፉባቸው ቀናት ናቸው፡፡ ከብዙ የመታወቂያ ቁጥር መካከል ውጤቱን ያየ ተማሪ በዚያ የትምህርት ዓይነት A እንዳገኘ ሲያውቅ ለጓደኞቹ ‘’A አገኘሁ እኮ’’ ይላል፡፡ በተቃራኒው ‘F’ ያገኘ ከሆነ ‘’F ሠጠኝ’’ ይላል እንጂ ‘F አገኘሁ’ አይልም፡፡ A ከሆነ ያገኘው ተማሪው ነው ፤ F ከሆነ ግን በድክመቴ አገኘሁ ከማለት ይልቅ ጥፋቱ የመምህሩ ይሆናል፡፡ ነገሩን አልኩ እንጂ ሀገር ሰላም ብሎ የቆመ በር ጋር ስንጋጭም ‘በሩ መታኝ’ እንጂ መታሁት አንልም፡፡
እናም በሕይወታችን ለሆኑትና ለሚሆኑት ነገሮች ‘ጌታ ሆይ እኔ እሆንን? ማለት ትልቅ ጸሎት ነው፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 20 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ