Get Mystery Box with random crypto!

ሰልማን አል-ዐውዳ ሚስቱን በመኪና አደጋ በማጣቱ ከሐዘን ጋር ጎጆ መቀለሱን የሰማችው የባለቤቱ ጓደ | ﷽ዚክረ መንዙማﷺ

ሰልማን አል-ዐውዳ ሚስቱን በመኪና አደጋ በማጣቱ ከሐዘን ጋር ጎጆ መቀለሱን የሰማችው የባለቤቱ ጓደኛ ብዕርን ከወረቀት ጋር አዋህዳ ደብዳቤን ላከችለት
Mahi Mahisho

ንግግሯን እንዲህ ትጀምራለች
"ከሚስትህ ጓደኞች መካከል አንዷ ነኝ የውድ ሚስትህ የኡሙ ሙዓዝ ሞት በእጅጉ አሳዝኖኛል። ያለፍክበትን ሀዘንም ሰምቻለሁ.. ምናልባት ያስታግስህ ዘንድ እነሆ ታሪኬን ፅፌልሀለው። ቀልብህን ከፍተህ አንብበው ...

ስለ ሐዘን የተነገረ ስለ ህመም የተተረከ የመጀመሪው ታሪክ አይደለም። እንደ እኔ የሚወዱትን ሰው አጥተው የሚሰቃዩ፣ ወላጅ ወንድሞቻቸውን ተነጥቀው የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ።

በሂጅሪያ አቆጣጠር በ1431 የረመዳን 27ኛው ቀን ላይ ይጀምራል። በአንድ መኪና ተሳፍረን ዑምራ ለማድረግ ወደተከበረው የአላህ ቤት ልንሄድ ከቤተሰቦቼ ጋር ወስነናል። ወንድሞቼ መኪናቸው ቤት አቁመው መጡ። ስምንት ነበርን.. ወላጆቼ፣ እህቶቼና ወንድሞቼ ሙሉ ቤተሰቡ አብሮን አለ። አባቴ እናቴን ጋቢና ከጎኑ አስቀምጦ መኪናውን ያሽከረክራል።

ሁላችንም ቁርኣንን ይዘናል። ጉዞው ረጅም ሰዓትን ስለሚፈጅ መኪና ውስጥ አኽትመን ልንወርድ አስበናል። ሐረም እስክንደርስ በዚክርና በዱዓ ልናሳልፍ ተስማምተናል። እህቴ እየቀራች ታለቅሳለች። ሌላኛዋም የዕንባ ጎርፍን ከዓይኗ ታፈልቃለች። ተራ በተራ እያየኋቸው
ዕንባቸው የሚፈሰው ለምን እንደሆነ ጠየቅኳቸው..?
"ቁርአንን ሳነብ የአላህ ድምፅ ለኔ ቅርብ ሆኖ አገኘዋለሁ" አለችኝ አንዷ።

እኔም ንግግሯን ሰምቼ በጥልቅ ማስተንተን መቅራቴን ቀጠልኩ። አባቴ እየነዳ ዕንቅልፍ አሸለበው። መኪናው ከተራራው አናት ላይ መንከባለል ጀመረ። ጥልቀት ወደሆነ ሸለቆ እየተንከባለለ ይገለባብጠን ያዘ። ከዛፍ ጋር ተላትሜ ቀረሁ የቀሩት ቤተሰቦቼ ሸለቆው ውስጥ ወደቁ።
የመግሪብ ሰላት አዛን እያለ ነበር። አላፈጠርንም ብዙ ደም ከሰውነቴ በመፍሰሱ ራሴን ሳትኩ። አስታውሳለሁ ስነቃ ባባ እያልኩ መጮኽ ጀመርኩ። እየተንፏቀቅኩ መፈለጉን ተያያዝኩት።

የአካል ስብራትና ጉዳት ቢደርስብኝም ድንጋጤው ህመሜን አስረስቶ በሆዴ እያንከባለለ እነሱ ዘንድ አደረሰኝ። እናቴን መጎተት ጀመርኩ። ሞታ አገኘኋት። አባያዋ ሰውነቷ ላይ እንደ ከፈን ተጠቅልሏል። ከሰውነት አካሏ አመልካች ጣቷ ብቻ ነበር የሚታየው። ሁሉም ተሰትሯል። እህቶቼን ሰውነታቸው ተገልጧል። ልሸፍናቸው ሞከርኩ.. ወደማይቀረው አለም ተሸጋግረው አገኘኋቸው። አመልካች ጣታቸው ለሸሃዳ እንደተቀሰረ ነው። ወንድሞቼም ሞተዋል። እንደምንም እየተሳብኩ እነሱንም እየሳብኩ አንድ ቦታ ሰበሰብኳቸው።

የማታዋ ጨረቃ ምሽቱን አድምቃዋለች። የውሻ ድምፅና ጨለማው ከአየሩ ጋር ተዋህዷል። ወደመኪናው ተመልሼ በእንፉቅቅ አባቴ ጋር ደረስኩ። በህይወት አለ። መላ ሰውነቱ እየደማ ነው። ወደ ደረቴ አስጠግቼ አቀፍኩት። "እዚህ ረጅም ሰዓት አትቆዪ.. ወደ ተራራው ጫፍ ወደ መንገዱ ሂጂና ሰው እንዲረዳሽ ተጣሪ ወንድሞችሽን አድኚ" አለኝ በተቆራረጠ ድምፅ።

የውሻዎቹን ድምፅና ጨለማውን መፍራቴን ነገርኩት። ጭኑን ተደግፌ "እየደማሁ ነው መንቀሳቀስ ከብዶኛል" አልኩት። ወደ ደረቱ አስጠጋኝና አደራ ዲንሽ ላይ አደራ እያለ ሸሃዳ ይዞ ወደማይቀረው ዓለም ተሸጋገረ። ብቻዬን ቀረሁ።

እያለቀስኩ ዱዓና ዚክር ላይ ተጠምጄ ራሴን ሳትኩ። አደጋው ከተፈጠረ ሁለተኛውን ቀን ይዟል። መኪናው ሲወድቅ ማንም አላየንም ነበርና ሊረዳን የመጣ ሰው አላገኘንም። በሶስተኛው ቀን አንድ እረኛ ከብቶቹን አሰማርቶ ሲንጎራደድ ከርቀት ተመለከተን። ለጥበቃዎች አሳውቆ በሄሊኮፕተር የታገዘ የነፍስ አድን ቡድን ወደሆስፒታል ይዞን አቀና።

አምስት ወራት ሙሉ ኮማ ውስጥ ቆየሁ። ስነቃ የሆነውን ነገር አስታወስኩ። ቅዠትና ህልም መስሎ ታየኝ። አባቴን እናቴን ወንድሞቼንና እህቶቼን በአንድ ጀንበር አጣሁ። ክስተተሀ ምናል ባልነቃሁ እኔም እነሱን በተከተልኩ አስባለኝ። ሁለት አመታት በሀገረ ካናዳ ጭንቅላቴ፣ አንገቴ፣ ጀርባዬና ዳሌዬ የደረሰባቸውን ከባድ ስብራት እየታከምኩ ህክምና ላይ አሳለፍኩ። በደም መፍሰስ ምክንያት እናት የመሆንን በረከት አጣሁ። ብዙ ሙከራዎች በዶክተሮች ቢደረጉም አልተሳኩም። ሕይወቴን ወይም ልጆች የማግኘት ፀጋዬን ሊያሳጣኝ የሚችለው ቀዶ ጥገና ምርጫው ከባድ ነበር ግን ሆነ።

አሁን ደህና ነኝ አልሀምዱሊላህ። ወደ ስራዬ ተመልሻለሁ ..ወደ ሪያድ ተዛውሬ ከአዲሱ ህይወቴ ጋር መኖር ጀምሬያለሁ .... ያሸይኽ... በሕይወትህ ውድ የሆነውን ሰው ያጣኸው አንተ ብቻ እንዳልሆንክ እንድታውቅ ታሪኬን አካፈልኩህ።

የእህቶቼ ሰርግ ሁለት ሳምንት ነበር የቀረው። ከመሞሸራቸው በፊት ዑምራ ማድረግ ፈልገን ወደ መካ በማቅናት ላይ ሳለን የአላህ ውሳኔ ቀደመ። አሁንም የሰርግ ልብሳቸው እኔ ጋር ነው። እስክሞት ድረስም አብሮኝ ይቆያል" በማለት ታሪኳን ትቋጫለች።

የቀደምት ታላላቅ ዑለማዎቻችንን እና በህይወት ያሉትን ዑለማዎቻችንን መንዙማዉች እና ስራዎች እንዲሁም አዳዲስ መንዙማውች ልክ እንደተለቀቁ የሚቀርብበት ቻናል በተጨማሪም በዚህ ቻናል
ስለ ወርቃማው ታሪካችን እናወራለን።
ዑለሞቻችንን እናወሳለን፤
ጀግኖቻችንን እንዘክራለን፤
ሳይንቲስቶቻችንን እናነሳለን።
ሰብስክራይብ በማረግ ቤተሰብ ይሆኑ ለወዳጆም ሼር ያርጉ
http://youtube.com/@zikrmenzumaneshidatube

Facebook page
https://www.facebook.com/profile.php?id=100066797534886

Join Tg
https://t.me/ZEKR_MENZUMA