Get Mystery Box with random crypto!

'በእንተ እግዝእትነ ማርያም ተገብረ ኵሉ ዓለም፤ ፍጥረት ሁሉ ስለ እመቤታችን ማርያም ተፈጠረ፤' | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

"በእንተ እግዝእትነ ማርያም ተገብረ ኵሉ ዓለም፤ ፍጥረት ሁሉ ስለ እመቤታችን ማርያም ተፈጠረ፤"
***
ሁለት ራእያዊ (apocalyptic) ይዘት ያላቸው ጥንታውያን ድርሳናትን እንጥቀስ። ዕዝራ ሱቱኤል (4 Ezra) እና እረኛው ሔርማስ (The Shepherd of Hermas)። የመጀመሪያው ፍጥረት ሁሉ ለተመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ ለቤተ እስራኤል ሲባል ተፈጠረ፤ አሕዛብ ግን ምንም ናቸው ይላል። (6÷54-56) ሁለተኛው ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን በከበረች ሴት አምሳል በራእይ ያያታል፤ ፍጥረት ሁሉ ስለ እርሷ እንደተፈጠረ ይናገራል። በዚህ ላይ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት (ዮስጢኖስ ሰማዕት፣ ኦሪገን፣ አውግስጢኖስ፣ ጠርጡለስ ...) ብዙ ብለዋል።
ጠለቅ ብለን ስንመረምረው ዓለም የተፈጠረው ስለሚጠፉት ሳይሆን ስለሚድኑት ነው። ቤተ ክርስቲያን (መላእክትንም ቤተ እስራኤልንም ባጠቃለለ ሰፊ ትርጉሟ - አቅሌስያ ማለት ጉባኤ እግዚአብሔር ማለት ነውና) የዚህ ማዕከል ነች። እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረው ፍቅሩን እና ክብሩን ሊገልጥበት ነው፤ ይህ ደግሞ በፍጽምና ያገኘነው እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ባካፈላት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ ነች፤ ክርስቶስ የፈጠረው ዓለም ክብሩን እና ዓላማውን የሚያገኘው ከሚወዳት ከሙሽራው ከቤተ ክርስቲያን የተነሳ ነው።
***
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍጥረት ሁሉ ስለእኛ ተፈጠረ ያሉት ቤተ እስራኤል እና ቤተ ክርስቲያን የሚጋጠሙባት (ሁለቱንም በፍጽምና የምትወክል) ነች። ቤተ እስራኤልን ፍጥረት ስለ እነርሱ እንደተፈጠረ እስኪነገርላቸው ድረስ ከፍ ያደረጋቸው የእሥራኤል ተስፋቸውና ክብራቸው ክርስቶስ ከእነርሱ በሥጋ መወለዱ ነው፤ ይህ ደግሞ እውነተኛዋ 'የእስራኤል ሴት ልጅ - ወለተ እስራኤል) በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም የተፈጸመ ነው። የቤተ ክርስቲያን ክብሯ የመለኮት ማደሪያ እና የክርስቶስ አካል መሆኗ ነው፤ ይህ ደግሞ ቀድሞ በፍጽምና የተደረገው በቅድስት ድንግል ማርያም ነው። እንደ እግዚአብሔር ዓላማ ፍጹም እስራኤላዊ እና ፍጹም ክርስቲያን ከድንግል ማርያም በላይ ማን አለ? ከፍጡራን ወገን ቤተ ክርስቲያንን በፍጽምና ሊወክል የሚችል ከድንግል ማርያም በቀር ማን ነው? ማንም!
***
"ፍጥረት ሁሉ ስለ እመቤታችን ማርያም ተፈጠረ" የሚለው ከዚህ ጥልቅ መንፈሳዊ (mystical) እይታ አንጻር ማየት ያስፈልጋል። እመቤታችን በብቻዋ አካል ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ወክላ የተነገረላት ነው፤ በብዙ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜዎች (ለምሳሌ ሙሴ ያያት እፅ፣ ሰሎሞን የሚዘምርላት ሙሽራ ፣ በራእይ ዮሐንስ ያለችው አውሬው የሚያሳድዳት ሴት) እና በቤተ ክርስቲያን ጸሎቶች ድንግል ማርያምና ቤተ ክርስትያን አንድ ሆነው እናገኛለን። እናታችን ጽዮን አንድም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድም ድንግል ማርያም ናት።
ፍጥረት ስለ እመቤታችን ተፈጠረ ማለት እርሷን ለማምለክ ተፈጠረ ማለት አይደለም፤ ይህን የምትል ቤተ ክርስቲያን እንዴት ልትኖር ትችላለች? (ይህን የምትሉ ሰዎች ኸረ ተው አባቶቻችንን እንዲህ አትናቁ! ጅሎች ይመስሏችኋል እንዴ? ጅሎች ሳይሆኑ በጣም ምጡቆች (mystical) ናቸው!)
በርግጥ "በእንተ እግዝእትነ ማርያም ተገብረ ኵሉ ዓለም፤" የሚለው በቀጥታ ሲተረጎም "ፍጥረት ሁሉ ስለ እመቤታችን ማርያም ተፈጠረ፤" እንጂ "ፍጥረት ሁሉ እመቤታችን ለማመስገን ተፈጠረ" አይልም። (እኛ ቤት ውስጥ ውርስ ትርጉም ሀገር እያጠፋ ነው፤ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶች ግን እንደዚህ አልነበሩም)
ቢሆንም እንኳ ማመስገን አምልኮ የሚሆነው ለፕሮቴስታንት እና እስላሞች (ሁሉም አይመስሉኝም) እንጂ ለቤተ እስራኤል እና ትውፊታውያን አብያተ ክርስቲያናት አይደለም። ማመስገን ማለትም ግዴታ በቃል መናገር አይደለም፤ ፍጥረት ሁሉ የሚናገር (ነባቢ) አይደለምና። "ፍጥረት ስለ እመቤታችን ማርያም ተፈጠረ" ማለት ድንግል ማርያም በወከለቻቸው ቤተ እስራኤል እና የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከፍጥረቱ ጋር ለዘላለም ሲዋሐድ ፍጥረታት የተፈጠሩበት ክቡር ዓላማ ተፈጸመ፤ በዚህም የፍጥረታት ደስታ ሆነ ማለት ነው።
(አንድ ሰው ኦርቶዶክስ ክርስቲያንም ሆኖ እነዚህ በጣም ረቂቅ አገላለጾች ካልገቡት ብዙ መጨነቅ አይገባውም፤ እስኪገቡት ድረስ በመሠረታዊው አስተምህሮ አምኖ መኖር ይችላል። ያልገባኝ ሁሉ ስህተት ነው ማለት ግን ትዕቢት ነው።
በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ምእመናንን ለማወናበድ እና ለማጠራጠር የሚጠቀሙባቸውና ብዙ ማብራሪያ ከመፈለጋቸው የተነሳ በየጊዜው ሥራ የሚፈጥሩባትን እንዲህ ያሉ ጠጣር ንባባትን ከዘወትር አገልግሎት አውጥታ በተቻለ መጠን ግልጽ የሆኑ እና ለአብዛኛው ምዕመን የሚሆኑ ንባቦችን የያዙ የመጻሕፍት ቅጅዎች (abridged versions) ማውጣት ይኖርባታል፤ አጥንት መቆርጥም የሚችሉ ግን በሁሉም ይራቀቁ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት እንዳደረጉት። ይህ እንደ ልጅነታችን በትህትና የምናቀርበው ሐሳብ ነው!)

~በረከት አዝመራው~