Get Mystery Box with random crypto!

+++ የተሰጠ እንባ +++ የሰው ልጅ ደካማ ነው። በውስጡ የሚፈራረቁበትን ስሜቶች ተሸክሞ ለማቆ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+++ የተሰጠ እንባ +++

የሰው ልጅ ደካማ ነው። በውስጡ የሚፈራረቁበትን ስሜቶች ተሸክሞ ለማቆየት ይቸገራል። በጣም ሲደሰት ወይም በጣም ሲያዝን እነዚህን ስሜቶች የሚያስተነፍስበት ሳቅ ወይም ልቅሶ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ሰውነት ይጨነቃል። አዲስ የወይን ጠጅ እንደ ገባበት አሮጌ አቁማዳ እቀደድ እቀደድ ይላል። ከባዱን የስሜት ሰደድ እሳት የሚያበርድበት ትኩስ እንባ ከዓይን ካላዘነመ ዕረፍት የሚባል ነገር አያገኝም። ዓይን አላነባ ሲል የውስጥ ሕዋሳት የሕመም እንባ ማንባት ይጀምራሉ።

የሕክምና ሰዎች እንደሚናገሩት ሦስት ዓይነት እንባዎች አሉ። የመጀመሪያው ዓይን ውስጥ ባዕድ (ቆሻሻ) ነገር ሲገባ የምናነባው ቅጽበታዊ እንባ (Reflex tear) ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይናችን እንዳይደርቅና ራሱን ከinfection ለመከላከል ሲል የሚያመነጨው የማይቋረጥ እንባ (Continuous tear) ነው። ይህም እንባ 98% ውኃ ነው። ሦስተኛውና በጣም ጠቃሚው እንባ ደግሞ የውስጥ ስሜት ፈንቅሎ የሚያወጣው እንባ (Emotional tear) ነው። ተጨማሪ ጥናቶች ቢፈልግም የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚሉት  በተለይ በኃዘን ጊዜ የሚፈስሰው እንባ ከሌሎቹ እንባዎች በተለየ በሰውነት ውስጥ የተለቀቀውን stress hormone ይዞ በማስወጣት ውጥረትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ እንባ ጋር ተያይዘው በሰውነት ውስጥ የሚለቀቁት እንደ oxytocin እና endorphins ያሉት ሆርሞኖች ደግሞ መረጋጋትና ዕረፍትን እንድናገኝ ያግዙናል።

ይህን የእንባ ጸጋ ለእኛ የሰጠ የሰውን ድካም የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው። ልቅሶውንም ለውስጥ ውጥረት ማስተንፈሻ ብቻ ሳይሆን፣ የነፍሳችንን ጉድፍ የምናጠራበትና ወደ እርሱ ይዘን የምንቀርበው የተወደደ መባ አደረገልን። የፈጣሪን የምሕረት ልቡን የምናውክበትና ፈጥኖ እንዲታረቀን ደጅ የምንጠናበትን የእንባ ምንጭ እርሱ ባለቤቱ ከዓይናችን ሥር አኖረ።(መኃል 6፥5) ሊቁ ዮሐንስ ዘሰዋስው እንደ ተናገረው ይህንንም እንባ ወደ ሰማይ ለምንወጣበት የብርሃን መሰላል አንደኛው እርከን አድርጎ ሰጠን።

የምትወደውን ሰው አጥተህ የምታነባ አንተ ሰው "እንዲህ ሳዝን ወዴት አለህ?" ብለህ ፈጣሪህን አትክሰስ። እግዚአብሔርን እንባህ ውስጥ ፈልገው ታገኘዋለህ። የውስጥህን ኃዘን ከሚያበርድበትና ስብራትህን ከሚጠግንበት መንገዶቹ አንዱ  "በሰጠህ እንባ" ነው።

"በደሌንና ነውሬን የሚያጥብ ዕንባ ስጠኝ። አቤቱ አንተን የሚያገለግል ዕንባን ስጠኝ። አቤቱ ልዩ ዕንባን ስጠኝ"
(ውዳሴ አምላክ)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
አዲስ አበባ