Get Mystery Box with random crypto!

ነቢያት ጌታ 'ይወርዳል ይወለዳል' ብለው የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸም ተመኝተው ጾሙ ጸለዩ:: እኛ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

ነቢያት ጌታ "ይወርዳል ይወለዳል" ብለው የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸም ተመኝተው ጾሙ ጸለዩ:: እኛ ስለምን እንጾማለን? ክርስቶስ ተወልዶ ፣ ተጠምቆ ፣ አስተምሮ ፣ ተሰቅሎ ፣ ሞቶ ፣ ተነሥቶ ፣ ዐርጎ ፣ በአባቱ ቀኝ አይደለምን? አሁን ለምን እንጾማለን? ብለን እናስባለን::

ጌታ በእኔና አንተ ልብ ውስጥ እውነት ተወልዶአልን? እውነት የእኛ ልብ እንደ ቤተልሔም ግርግም ለክርስቶስ ማደሪያ ሆኖአል? ማደሪያ አሳጥተን ከእናቱ ጋር አልመለስነውም?

የጥምቀቱ ትሕትና በእኛ ልብ መቼ ደረሰ? የስቅለቱ ሕማም መች በእኛ ሕሊና ተጻፈ? የትንሣኤው ተስፋ የዕርገቱ ልዕልና በእኛ ልቡና መቼ ዐረፈ?

ስለዚህ ነቢያት "ውረድ ተወለድ" ብለው የጾሙትን ጾም እንጾማለን:: ጌታ ሆይ በእኔ ሕይወትም ውስጥ ውረድ ተወለድ የእኔን ሰውነት ማደሪያህ አድርገው:: ሕዋሳቶቼ ከኃጢአት አርፈው እንደ ቤተልሔም ግርግም ማደሪያህ ይሁኑ::

የቤተልሔም እንስሳት ትንፋሽ ገበሩልህ ፣ የቢታንያ ድንጋዮች ዘማሪ ቢጠፋ ሊዘምሩ ዝግጁ ነበሩ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለክብርህ ተቀደደ ፣ ጨረቃ ላንተ ደም ለበሰች ፣ ፀሐይ ስላንተ ጨለመች ፣ ከዋክብት ለስምህ ረገፉ ፣ ዓለቶች ለፍቅርህ ተሰነጠቁ::

ከቤተልሔም እንስሳት ፣ ከቢታንያ ድንጋዮች ፣ ከቤተ መቅደስ መጋረጃ እኔ እንዴት አንሼ ልገኝ? የቢታንያ ድንጋይ ያወቀህን ያህል ሳላውቅህ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ የተረዳህን ያህል ሳልረዳህ እንዴት ልኑር?

ዓለት ላንተ ሲሰነጠቅ የኔ ልብ ለምን ከዓለት ደነደነ? ጨረቃ ደም ስታለቅስ እኔ መከራህ ለምን አልተሰማኝም?
ሙታን በሞትህ ሲነሡ እኔ ምነው ከኃጢአት ሞት መነሣት ተሳነኝ?

ለዚህ ነው በእኔ ሕይወት ገና አልተወለድክም የምለው::

ስለዚህ ጌታ ሆይ የነቢያትህን ጾም ጸሎት ሰምተህ የወረድህ የተወለድህ ጌታ ሆይ በእኔም ሕይወት ውረድ ተወለድና እኔም ከመላእክት ጋር አብሬ ልዘምር ፣ ከሰብአ ሰገል ጋር ሥጦታህን ልቁጠር ፣ ከእረኞች ጋራ ልደነቅ:: ልደትህ ሳይገባኝ ምጽዓትህ እንዳይደርስብኝ እርዳኝ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጾመ ነቢያት 2015 ዓ.ም.