Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል 2 የመድኃኔዓለም ወገኖች ሆይ! የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ መሆኑንና የትዕግሥቱን ብዛት አይተን | ሊቀ መዘምራን

ክፍል 2

የመድኃኔዓለም ወገኖች ሆይ! የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ መሆኑንና የትዕግሥቱን ብዛት አይተን እናደንቅ ዘንድ ከመጻሕፍት ጠቅሰን እንነግራችኋለን፡፡ አይሁድ ጌታችን አብርሃም ሳይወለድ በፊት እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን አምላክ መሆኑን ቢነግራቸው ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፡፡ እሱ ግን ጊዜው ገና ነበርና ተሰውሮአቸው በመካከላቸው አልፎ ሲሄድ በፍጹም አላዩትም ነበር፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም:- ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡›› ዮሐ 8፡56-59፡፡

ዳግመኛም በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው አይሁድ መድኃኔዓለምን ሊይዙት የጦር መሣሪያቸውን ሰብስበው ወደ ጌቴሴማኒ በመጡ ጊዜ ‹‹ማንን ትፈለጋላችሁ?›› ቢላቸው ‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ›› ቢላቸው ከአንደበቱ የወጣውን መለኮታዊ ቃል ብቻ መቋቋም አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀው ተዘርረዋል፡፡ ይህም ክስተት በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል ላይ ምዕራፍ 18 ከቁጥር አንድ ጀምሮ ይመለከቷል፡፡) እናም የጌታችን ሞቱ በፍጹም ፈቃዱ ባይሆን ኖሮ በጌቴሴማኒ ሊይዙት የመጡት ክፉዎች አይሁድን እንደመጀመሪያው ሁሉ በተሠወራቸው ነበር አሊያም ከአንደበቱ በሚወጣው አምላካዊ ቃሉ ብቻ ባጠፋቸው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችን ወደዚህች ምድር የመጣበትን ዓላማ ይፈጽም ዘንድ እንዲገድሉት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ቢሰጣቸው ያን ሁሉ እጅግ አሠቃቂ መከራ አደረሱበትና ለመስቀል ሞት አበቁት፡፡

ወዮ ለዚህ ለመድኃኒዓለም ፍጹም ትዕግስት አንክሮ ይገባል! ዓለምን በመዳፉ የያዘ አምላክ በአይሁድ እጅ እንደሌባ ተያዘ፡፡ ሠራዊተ መላእክት ለምሥጋና በፊቱ የሚቆሙለት መድኃኔዓለም እርሱ ሊፈረድበት በፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡ በእስራት ያሉትን የሚፈታ እርሱ በብረት ችንካር ተቸነከረ፡፡ ሰማይን በከዋክብት ምድርም በአበባ ያስጌጠ እርሱ ግን የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፡፡ ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብ እርሱ ተጠማሁ አለ፡፡ ወዮ የመድኃኔዓለም የማዳኑ ምሥጢር ምንኛ ድንቅ ነው!!! ለዚህ ባሕርይው አንክሮ ይገባል፡፡

በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞት በአንድነት እናለቅስ ዘንድ ቅዱሳን ሁላችሁ ኑ! መድኃኒታችን ሙቷልና ፍጥረታት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ መያዝንና መታሠርን የተቀበለ መድኃኒታችን ሙቷልና፡፡ ጥፊንና ግርፋትን የተቀበለ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ መደብደብንና መመታትን የታገሰ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ ሄኖክ እግዚአብሔር ‹‹በሴም ቤት ይደር›› ብሎ አብ ስለራሱ የተናገረለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አብርሃም ቃልኪዳን የገባልህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ይስሐቅ ከሰይፍ ቤዛ የሆነህን

የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ያዕቆብ በበረሃ የታገለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮብ በደመና የታየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሙሴ ስለ እርሱ ‹እንደእኔ ያለ ነቢይ ይነሣል› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳዊት ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ በበረሃ ዛፍም አገኘነው›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤርሚያስ ‹‹የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበሉ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ኢሳይያስ ‹‹ወልድ ሰው ለመሆን ተገለጠልን፣ ሕፃን ተወለደልን፣ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅኤል ‹‹አምላክ ወደ ተዘጋች ደጃፍ ገባ፣ ከተዘጋች በርም ወጣ›› ብለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳንኤል ነጭ ሐር ለብሶ ያየኸውን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤልያስ ከሞት በፊት የሰወረህ በእሳት ፈረሶች ያሳረገህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅያስ የፀሐይ መግባቱን ያሳየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ምናሴ ችንካሮችህን ከእግር ብረት የፈታ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮስያስ ፋሲካውን ያደረግህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ከእሳት ምድጃ ያዳናች የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አብያና ሲላ ፌንቶስ ከመወለዱ አስቀድሞ ያመናችሁበት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ የቀድሞ አባቶች ነቢያት ሁላችሁ ከፋራን ተራራና ከቴማን ይመጣል ያላችሁት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አሞፅ በአድማስ ቅጥር ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዘካርያስ በተራራዎች መካከል ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዕዝራ በአርፋድ በረሃ ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ስምዖን በክንድህ የታቀፍከውን ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዮሴፍ እንደ አንተ የተሸጠ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ጠራቢ ዮሴፍ በትከሻህ ያዘልከው በክንድህ የተሸከምከው ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከሕፃንነትህ ጀምሮ በበረሃ ያለ እናት ያለ አባት ያሳደገህ መንገዱንም እንድትጠርግለት ያዘጋጀህና መለኮትን እንድታጠምቅ የመረጠህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ክፍል 3 ይቀጥላል.....

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች
•➢ ሼር // SHARE

•✥• @Z_TEWODROS •✥•
•✥• @Z_TEWODROS •✥•
•✥• @Z_TEWODROS •✥•