Get Mystery Box with random crypto!

ያች ምስኪን ነፍስ!! ... እነሆ የፈጠርኳትን ነፍሰ ገደልኳት። አይኔን ወደፈጠርኳቸው | ከኢትኤል ብዕር ነጠብጣቦች......✍️

ያች ምስኪን ነፍስ!!
... እነሆ የፈጠርኳትን ነፍሰ ገደልኳት። አይኔን ወደፈጠርኳቸው ፍጡር ስልከው ይህቺ አሳዛኝ ፍጥረቴ ብቻዋን ክልውስ ክልውስ ስትል አየኋት እና ፍፃሜዋን አደረስኩት። ደስታና ሀዘኗን አላውቅም። ሞቷን ግን አፈጠንሁት። ምናልባት ይህች ነፍስ ደስታዋ ላይ ይሆናል የቆጨሁባት። ወይም ሀዘኗ ላይ ይሆናል የገደልኋት። ህልሟን ሳታሳካ ብኩን አድርጊያትም ይሆናል። እሷን በማጣት የሚሰቃዩ ዘመዶች ይኖሩ ይሆናል ። ግን ሀዘናቸው ደስታቸው አይገባኝም። እነሱን ካልሆንሁ ይህቺን ምስኪን ነፍስ ህመሟን እና ደስታዋን ሁኜ ካልኖርኩት በእርግጥም አይገባኝም። ስለዚህ የፈጠርኳትን ነፍስ ያለምንም እርህራሄ ገደልኳት።
በሞቷ ለምን ገደልካት ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ማንም አይከሰኝም። ህይወት ስዘራባት ለምን አመጣሃት ብሎ የጠየቀኝ የለምና። ለምን ኑሯ ለምን እንደሞተች እንኳ በጉያዋ ያሉት አይረዷትም። እናም እላችኋለሁ የፈጠርኳቸውን ፍጥረቶች በሙሉ ተራቸውን እየጠበቅሁ እገላለሁ። በገደልሁት ምትክ ደግሞ ሌላ ህይወት እፈጥራለሁ። ህይወት አትቆምም እና.......
እነሆ ለዚች ነፍስ እኔ ፈጣሪ ነኝ። እርግጥ ነው ከመኖር ወደ አለመኖር በሰከንዶች ውስጥ ቀይሪያታለሁ። ሀይሌን ተጠቅሜ ህልሟን ነጥቂያለሁ። እንደራሴ ሳስበው እንዳንዴ ታሳዝነኛለች። ምናልባትም እኔ ከፈጣሪ የሞት ትዛዝ ቢላክብኝ ውስጤ ይረበሻል። ምንም ያህል ፈጣሪዋ ብሆንም ለኔም ፈጣሪ አለኝ። እኔንም ቀን ጠብቆ ና የሚለኝ። የፈጣሪነት ትርጉሙ የገባኝ ይህቺን ፍጥረት ፈጥሬ በምፈልገው መንገድ አስጉዤ መልሼ ስመለከታት በመንገዷ መገረሜ እና በቀላሉ ህይወት እንደሰጠኋት ህይወቷን በቀላሉ መንጠቅ መቻሌ ነው። ከህይወት ወደ ሞት ስቀይራት ከዚች ነፍስ በፀጥታ ስመለከተው ብዙ ጅምር ህልም ነበራት። የሀዘን ድር በዘመዶቿ ላይ ተብትቢያለሁ። ግን ምንም አይመስለኝ። አልፀፀትም ! ህልሟን እንድታሟላ እንዲሁም እንዲከሽፍ ዋናው መንሴኤ እኔ ብሆንም እኔ ነኝ ፈጣሪዋ። እኔ ስለሷ ሀጢያት እንዲሁም ስለሷ መጎሳቆል ደንታ የለኝም። ስለሷ ስል ከልጅልጇ በቃል መንገድ ተወልጄ በመስቀል አልቸነከርላትም። በተፈቀደላት መንገድ እንድትጓዝ አንዴ ቀርጫታለሁና!!!
እነሆ የፈጠርኳትን ነፍስ ገደልኳት።
እሰየው ገደልኳት
ከመኖር ወደ አለመኖር ቀየርኳት!
በሷ ሞት ምትክም ሌላ ባይተዋር ፍጥረት ፈጠርሁ!
ህይወት አትቆምምና.......
ወዳጆቼ የአለም ፍፃሜ አለ ቢሏችሁ አትመኑ! አለም በማይታወቅ ውህድ የተሰራ ነውና። አስቀያሚ ቅርፅ ብናስይዘውም ከጀርባው ብዙ ውብ ነገሮች አሉ። ማየት እስከምንፈልገው ብቻ እያዬን ህይወትን አስቀያሚ ቅርፅ አስያዝናት። ችግሩ ያለው ከማን መሰላችሁ? ከዚሁ ከእኛ አእምሮ ውስጥ ነው። አእምሯችን ጠማማ ነገሮችን ብቻ ያስባል። ጠማማ ሁነን ደግሞ ቀርተናል። አየህ የአለም ከፋቱ ይሄ ነው የአለም መጨረሻ ማለት። ከዚያ ውጭ አለም ታልፋለች ለሚለው አበባል ሳቅበትና በፌዝ ተመልከተው። ዓለም የምታልፈው አንተ ስታልፍ ብቻ ነው። የኔ አለም አኔ ነኝ። እኔ ሳልፍ ፍጥረት ብትቀጥልም የኔ አለም ለተምፃቱ ደረሰ እላለሁ። አለም ማለት አንተ ነህ። አለም ማለት አንቺ ነሽ!!
ይኑካ ነኝ