Get Mystery Box with random crypto!

​​ ባ ል አ ስ ይ ዞ ቁ ማ ር ክ ፍ ል ስ ም ን ት ፀ ሐ ፊ ዘ ሪ ሁ | የልብ ቃል ሚዲያ

​​ ባ ል አ ስ ይ ዞ ቁ ማ ር
ክ ፍ ል ስ ም ን ት
ፀ ሐ ፊ ዘ ሪ ሁ ን ገ መቹ
ባል አስይዞ ቁማር
ምዕራፍ-ስምንት
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ
///

  ‹‹..ለምንድነው በርሬ የመጣሁት…?››እራሷን ጠየቀች… አዎ ላፓቶፑን አስታቅፋው ፊቷን አዙራ ለመሄድ ነበር…እንደዛ ለማድረግ ታዲያ መኪናዋን ለምን ወደጊቢው ውስጥ አስገብታ አቆመች..?‹‹አሮጊቷ ናቸው  ሀሳቤን ያዛቡብኝ፡፡››ስትል ለራሷ ሰበብ ሰጠች፡፡
‹‹ልዩ ሰላም አደርሽ…?ግቢ ..አረ ብርድ ላይ …››ተንስፈሰፈ….፡፡እርግጥ የሆነ ቀን መጥታ በራፉን እንደምታንኳኳ እርግጠኛ ነበር..ማታ ፌስቡኩን ዲአክቲቬት ሲያደርግም ለዛ አላማ እሷን ለማመቻቸት ነበር.. ግን ደግሞ ፈፅሞ በዚህ ፍጥነት በዚህ ለሊት እሷን በደጁ ቆማ አያታለሁ ብሎ አልጠበቀም…በዛም የተነሳ በጣም ነው የደነገጠው..
‹‹ብርዱ ››  ሲላት የእውነት በረዳት….ገባችና ቆመች፡፡ …በራፉን ዘጋና‹‹ ነይ ..››እጇን ይዞ ወደመኝታ  ቤቱ ጎተታት…ዝም ብላ ተጎተተችለት…አልጋው ጠርዝ ላይ እንድትቀመጥ አመቻቸላት…፡፡
‹‹ስንት ሰዓት ነው…?እንዲህ ነግቷል እንዴ ?አለና ሞባይሉን ከጠረጴዛ ላይ አንስቶ ተመለከተ …የሰዓቱን ገና ለሊት መሆን ሲያይ ደነገጠ ፡፡
ከእግር እስከፀጉሯ እየመረመራት‹‹ደህና ነሽ ግን ?›› ባለማመን ጠየቃት.፡፡
‹‹ደህና አልመስልም?››
‹‹እሱማ በጣም ደህና ትመስያለሽ..እብጠትሽም ቁስልሽም ከቦታው የለም…..ግን በዚህ ሰዓት ስትመጪ ችግር ከተፈጠረ ብዬ ነው?››
‹‹ለምን ፌስቡክህን ዲአክትቤት አደረከው?››
‹‹ስላበሳጨሁሽ እዝኜ ነው››
‹‹ስለአበሳጨኸኝማ አይደለም..እኔ  መርዝ ንግግሮቼን እንዳልክልህና ይበልጥ እንዳላፍር እራሴንም እንዳልጠየፍ ስለፈለክ ነው፡፡››አለችው…ከተናገረችው ውስጥ ምንም ስህተት ስላልነበረበት ዝም አለ፡፡
‹‹እንካ ይሄው ላፓቶፕህ..ከቦርሳዎ አወጣችና ሰጠችው…..ኪሷ ገባችና    የተጠቀለለ ብር አውጥታ አንድ በአንድ እየቆጠረች.  ይሄ ለህክምና ያዋጠኸው ነው፣ይሄ  ደግሞ ለላዳ የከፈልክልኝ ነው፣ይሄ ደግሞ ወደቤት ስሄድ የላዳ ብለህ እዛ ኮመዲኖ ላይ ያስቀመጥክልኝ ነው፣ልክ በአራጣ ተበድሮ ብድሩን አንድ በአንድ እየቆጠረ እንደሚያስረክብ ሰው እጁ ላይ እያስቀመጠች ስትንጣጣበት እሱ ያለምንም ተቃውሞ ተቀበላትና እንደነገሩ ፊት ለፊቱ ጠረጴዛ ላይ ወርወር አደረገው..ላፕቶፕንም አስቀመጠው…
እና በሚያምሩ አይኖቹ ፊት ለፊት አያያት…ብዙ ብዙ ነገር እንዲል ፈልጋለች...እንዲሰድባት..እንዲረግማት ..እንዲያደንቃት..  እንዲያዝንላት… ብቻ አንድ መስመር  ይዞ  የሚናገራን ነገር ከአንደበቱ መስማት ፈልጋለች..እሱ ግን ንፉግ ነው የሆነባት.. የምትፈልገውን አልሰጣትም…፡፡
‹‹አሁን ለሊት ነው.. አንቺም በርዶሽ እየተንቀጠቀጥሽ ነው… ጫማሽን አውልቂና አልጋ ላይ ውጪ፡፡ኔም ገና እንቅልፌን አልጠገብኩም.. ትንሽ እንተኛና ሲነጋ ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን፡፡››አላት፡፡
ለመጮህ ፈለገች…ገፍትራውና ሰድባው እቤቱን ለቃለት ልትወጣም ዳዳት...ግን እንደዛ እየተመኘች ባለችበት ሰዓት ትዕዛዟን አክብራ  ጎንበስ ብላ ጫማዋን እያወለቀች ነው…ልብ እና አዕምሮ ሁለቱም የራሳችው የሆነው መደማመጥ አቁመው በየፊናቸው ያሰኛችውን ሲያደርጉ ማለት እንዲህ ነው፡፡ጫማዋን አወለቅችና ልክ እንደለመደች የፍሬንዷ አልጋ ሙሉ በሙሉ ወጣች…እሱ ለሊቱን ሙሉ ተኝቶበት ከወጣበት ቦታ አልጋ ልብሱንና ብርድ ልብሱን ገልጣ ገባች….፡፡
‹‹እሱስ ተከትሎኝ መጥቶ ከጎኔ ይተኛ ይሆን እንዴ.?››ይሄንን ያሰበችው ከተኛች በኃላ ነው….ግን እንዲተኛ ፈልጋለች ወይስ  አልፈለገችም..?›ለዚህ ጥያቄ በውስጧ የተቀመጠ አውንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ የለም…፡፡
ቃል ከተቀመጠበት ወንበር ተነሳ.. በግርጌ በኩል ያለውን አልጋ ልብስ እና ብርድ ልብስ ገለጠና ከጎኗ ያለውን አንዱን ትራስ በማንሳት በተቃራኒው ቦታ በማስቀመጥ ከውስጥ ገብቶ ከሰውነቷ እንዳይነካካና እንዳያሳቅቃት ወይም እንዳይፈታተናት እስከቻለው ድረስ ርቀቱን በመጠበቅ  ጠርዙን ይዞ ተኛ፡፡እንግዲህ  የተመሰቃቀለ አስተኛኘት ተኙ ማለት ነው….
‹‹እንደ እኔ አይነት የተመሰቃቀለ አስተሳሰብ  ያለው ሰው የተመሰቃቀለ አስተኛኘት ተኝቶ እንዴት ነው የሚሆነው…?፡፡››በውስጧ አብሰለሰለች፡፡
ሳታስበው ቃላለቶች ከአንደበቷ አመለጧት‹‹ምነው ፈራሀኝ እንዴ..?››አለችው፡፡
‹‹..ይህ ማለት እንግዲህ ምን ማለት ነው ?››እራሷን ነው በትዝብት የጠየቀችው፡፡
እስቲ አስቡት…እንድትተኛ የምፈልገው በትክክሉ እንደእኔው ወደላይ ዞረህ ነው እያለችው አይደል…?ይህ ንግግር ደግሞ ጥሩ መንዛሪና ተርጓሚ ካገኘ  ከዛም በላይ ስውር መልእክት ሊኖረው ይችላል ፡፡እንድታቅፈኝና ከመንቀጥቀጤ እንድትታደገኝ እፈልጋለሁ የሚል የተለጠጠ መልእክት ያስተላልፋል…አጋኖ ተርጎሚ ካገኘ ደግሞ ከዛም በላይ..፡፡
ጭራሽ ይባስ ብሎ ‹‹አረ በፍፅም….ይልቅስ የፈለኩት ሳሎን መተኛት ነበር…እንደዚህ ታስቢያለሽ ብዬ ነው እዚህ የተኛሁት፡፡››አላት፡፡ይሄ መልስ ደግሞ እሷ ከምታውቃቸው ወንዶች ሁሉ ልታገኘው የማትችል ግራ የሆነ ግን ደግሞ ትክክለኛ ሀሳብ ያዘለ መልስ ነው፡፡
‹‹መተኛትህ ካልቀረ ታዲያ በትክክል ተኛ..››አለችው፡፡
‹‹እሺ››ብሎ ትራሱን ይዞ  ከጀርባዋ ዞሮ ተስተካክሎ ተኛ….አቅጣጫውን አስተካከለ እንጂ በመሀከላቸው ያለውን ክፍተት ለማጥበብ እልደፈረም… ፍላጎቱም አልነበረውም፡፡እሷም ከዛ በላይ አልፈለገችምኩ ..አልጠየቀቻምም.፡፡
በመከፋትና በከፍተኛ ብስጭት የመጣችው ልጅ ከስንት ጊዜ በኃላ ደስ የሚል ስሜት ተሰማት..እንደው ደስ የሚል ስሜት ማለት ምን ማለት ነው ካላችሁ…?የሆነ ፍፅማዊ መረጋጋት፤መረበሽም መቆጨትም የሌለበት…በሸለቆ ውስጥ እንደሚንኳለል የምንጭ ውሀ ጥርትና ኩልል ብሎ የሚፈስ የአእምሮ ሞገድ..አዎ እንደዛ ነው እየተሰማት ያለው…እና  እንቅልፏ መጣ፡፡
ይ ቀ ጥ ላ ል . . .

FOLLOW US
|.TELEGRAM
|.FACEBOOK
|.YOUTUBE