ማማት ካልሰለቸሽ... °°°°°°°°°°°°°°°°°° ጸጉሩን አጎፍሮ፥ ጺሙን አንጨብሮ፥ በነተበ ሹራብ ስካርፑን ጠምጥሞ፣ በብርሃን ዘመን ይመጣል ፀልሞ፤ ይኼ የፍካት ፀር . . . ውበትን ቆልምሞ። ፧ በመጽሐፍ ገጾች ላይ ዐይኖቹን ወሽቆ፣ የሌለሁኝ ያህል ዋጋ ክብሬን ፍቆ፤ ከምንም ሳይቆጥረኝ ጥሎኝ ይከንፋል፣ መኖሬን ደርምሶ ዓለሙን ያስፋፋል፤ አትስሙ የሱን ጉድ . . . እጅግ ይከረፋል። ፧ ጨለምተኛ ነው ከራሱ በስተቀር አያፈቅርም ሌላ፣ ገፍትሮ ይጥላል ማስደፈር አይሻም የልብ አጥሩን ኬላ። ስንት ጊዜ አንኳኳሁ ቆፈቆፍኩ በብርቱ፣ ተከርችሞ ቀርቷል መክፈቻ ጉጠቱ። ፧ የሰው ስቃይ፣ ሕመም ቆስቁሶ እየሰማ . . . ድርሰቱን ያደራል፣ የራሱን በደል ግን ከፍኖ ይቀብራል። መናገር አይሻም ማዳፈን ነው ወልፉ፣ እንግልት ብርታቱን ሰሚ እንዳይኖረው ዘግቶታል በቁልፉ። . . ምናምን እያልሽ . . . ታሚኛለሽ አሉ!! : : ግድ የለም ቦጭቂኝ!! ግድ የለም ሸርድጂኝ!! ግን ደግሞ እወቂ፥ ሐሜት እና አሽሙር አይጥለኝም ጠልፎ፣ ከጽልመት ገላ ላይ ፈልቅቄ መዛለሁ የብርሃን ወጨፎ። ፧ ዝለፊኝ አብዝተሽ!! ውቀሽኝ አጥብቀሽ!! ግን ደግሞ ተረጂ፥ ላፈቀረ ሁሉ ልብ አይከፈትም፣ ማጣት ብቻ አይደለም ልኩን ካላወቀ ያስከፋል ማግኘትም። ፧ እሚኝ አይደንቀኝም!! ስደቢኝ አላዝንም!! ግን ደግሞ እመኚ፥ ህይወቴ ተነጥፏል ከድርሰት ጫንቃ ላይ፣ ማንበብ እና መጻፍ ሀሴት ያለብሰኛል ካንቺ ግብዣ በላይ። . : ፧ #ኤልዳን @yegtm_hywet @yegtm_hywet 366 viewsቼ በል ጋሜ, 04:11