Get Mystery Box with random crypto!

ይህ በእንዲህ እያለ ..! በእውቀቱ ስዩም ስሚ! ሁሉ ነገር ዱሮ ቀረ ሲሉሽ ሀሰት እንዳይመስል | ውብ ታሪኮች ®

ይህ በእንዲህ እያለ ..!
በእውቀቱ ስዩም


ስሚ! ሁሉ ነገር ዱሮ ቀረ ሲሉሽ ሀሰት እንዳይመስልሽ! የድሮ ጴንጤ የምር ጻድቅ ነበር፤ አይጠጣም፤ ከአፉም ክፉ አይወጣም፤ በእምነቱም ብዙ መከራ ይቀበል ነበር፤ ትዝ ይለኛል፤ ልጅ እግር እያለን እንቻለው ሰይፉ የተባለ የሰፈራችን ጴንጤ ነበር፤ እና አምልኮ ሲመለስ ስሚዛ ስር አድፍጠን እንጠብቅና እናበራየዋለን፤ እሚገርመኝ ነገር፤ እንቻለው ስንደበድበው በመመከት ፋንታ እጆቹን ደረቱ ላይ አመሳቅሎ ፥ አንጋጦ እያየ የሚወርደበትን በትር በጸጋ ይቀበላል፤ ከሰማይ ርዳታ እየጠበቀ መሆን አለበት፤ ርዳታው ሲዘገይ ፥ ጥፊውና ካልቾው ሲበረታ፤ እንቻለው ከድብደባ የተረፈውን ሰውነቱን ሸካክፎ በሩጫ ወደ ቤቱ ይሸመጥጣል፤” እህ! ሰማእትነትም ቢሆን ልክ አለው!” የሚል ይመስለኛል በልቡ ዛሬ ግራ ጉንጩን ብትመታው ቀኙን የሚያዞርልህ ወንጌላዊ ያለ አይመስለኝም፤ እንዲያውም ግራ ጉንጩ አጠገብ አያስደርስህም፤ ግራ ጉንጩ ላይ ከመድረስህ በፊት ቦዲጋርዶቹ እንደ ሸንኮራ ቀንጥሰው ለጠብታ አንቡላንስ ያስረክቡሀል::

ባህታዊ ራሱ ድሮ ቀረ! የድሮ ባህታዊ ፤ ዱር ጥሶ፤ ጤዛ ልሶ፤ ድንጋይ ተንተርሶ፤ የሌሊትን ግርማ ታግሶ ለህዝቡ ይጸልይ ነበር፤ የዛሬ ባህታዊ መሀል ከተማውን ጥሶ፥ ላፕቶፕ ተባጥሶ፤ የኔትወርክ መቆራረጥን ታግሶ ፥ ትንቢት ሰክሶ ፥ በዩቲብ ላይ ሲሸቅል ታገኘዋለህ፤

የእምነት አመል እንደየጊዜው ይለዋወጣል፤

በአለም ላይ ሁለት አይነት ሰዎች አሉ፤ ችግር የሚፈቱና ችግር የሚፈተፍቱ! ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር በያይነቱ ተትረፍርፏል! ችግሩን መፍታት ቀላል አይደለም፤ ለምሳሌ ሀኪም ለመሆን በትንሹ ሰባት አመት መማርና መመራመር ይጠይቃል፤ ባንጻሩ ሰው ባንድ ጀንበር ብቻ በሽታ ላይ ይወድቃል፤ የችግረኞች መብዛት እና የችግር ፈቺዎች ማነስ አንድ ነገር ፈጠረ፤ የችግር የመፈታት ቸሎታ ተላይ ተሰማይ ተሰጥቶናል እሚሉ አጭበርባሪዎች ከየቦታው እንዲፈለፈሉ ምክንያት ሆነ፤

ዛሬ፥ በሀይማኖት ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ ስፍር ቁጥር የለውም፤ የሀይማኖት ከበርቴዎች ግብር አይከፍሉም፤ በአስራት ፥ በመባ በስጦታ የሚሰበስቡት በአካውንታቸው ስር ከመርመስምስ አልፎ ለልማት ሲውል አናይም፤ በበጎ ሰዎች አይን ሲገባ፥ ሀይማኖት ለበጎ አላማ መሳርያ ሊሆን ይችላል ብየ አስባለሁ፤ግን እየሆነ ያለው ሌላ ነው፤

የእምነት ሊቃውንት፥ በሰናይ ምግባር ላይ የተመሰረተ ስበከት ሲሰብኩ ከሰማችሁ ስንት ጊዜ ሆናችሁ? ዛሬ ዛሬ “ስብከት የተአምር ሰርከስ ከማሳየት እና ከማዝናናት አያልፍም! ይሄ ሁሉ , መስጊድ፤ ይሄ ሁሉ ቤተክስያን ባለበት አገር ፤ ግድያ፤ዝርፍያ፥ ቅጥፈት፥ዘረኛነት ደፈራ፥ አደንዛዥ እጽ፥ በዚህ መጠን መንሰራፋት ነበረበት? የሆነ አጀንዳ ሲመጣ ከየአቅጣጫው የሚጎረፈው የዘለፋ አይነት፥ እውነት በሀይማኖት ከታነጸ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ነው? የሀይማኖት ሰዎች በቤትስራቸው ላይ እንደተኙበት አያሳይም?

ውሻ በቀደደው ልግባ ብየ ነው፤ አመሰግናለሁ።

@WubTarikoch