2022-09-01 17:32:17
የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ለአንድ ወር ሲሰለጥኑ የቆዩ ባለ ልዩ ተሰጥኦ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስመረቀ
በዩኒቨርሲቲ አዲስ ከተቋቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አንዱ ነው- STEM (የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሂሳብ) ማዕከል።
ማዕከሉ በ2014 ዓ.ም STEMpower ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ካምፓስ የተቋቋመ ነው።
የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል ከድርጅቱ በተገኘ የ 8.7 ሚሊየን ብር ድጋፍ የተሟላ የኮምፒዩተርና የኤሌክትሮኒክስ ላብራቶሪዎችን በተደራጀ መልኩ አካቶ ይዞ ይገኛል።
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ (STEM) ትምህርቶች ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ተኮር ትምህርት በማሰልጠን ቴክኖሎጂና ፈጠራን ማስፋፋት የማዕከሉ ግብ እንደሆነ ከማዕከሉ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል ነሐሴ 4/2014 ዓ.ም በዎላይታ ዞን ሶዶ ከተማ እና ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ካሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 50 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን ተቀብሎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ታውቋል።
በማዕከሉ ለአንድ ወር ሲሰለጥኑ የቆዩት 50 ሥልጠናቸውን በሚገባ መከታተላቸው ተረጋግጦ በዛሬው ዕለት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ፥ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ፣ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውብዓለም ግርማ፥ የፋይናንስ ዳይሬክተር ተክሉ መና እና ሌሌች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
በተማሪዎቹ የምረቃ ሥነ ስርዓት መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዶ/ር ውብዓለም ግርማ በበጋ ዕረፍት ወቅት ማዕከሉ ነሐሴ 4/ 2022 በወላይታ አካባቢ ላሉ የሶዶ ከተማ እና ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች 50 ተማሪዎች ተቀብሎ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በኮምፒዩተርና ኤሌክትሮኒክስ ላብራቶሪዎች ውስጥ የSTEM ትምህርት ለመቅሰም ከተመለመሉ 50 ተማሪዎች ውስጥ 27 ወንድ እና 23 ሴት ተማሪዎች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው STEM ማዕከል በመጀመሪያው ዙር የከተማ አቀፍ ፕሮግራሙ ከዎላይታ ዞን ሶዶ ከተማ እና ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ የተሟላ የመኝታ እና የምግብ አገልግሎ በመስጠት መጀመሩን ዶ/ር ውብዓለም ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ለአንድ ወር ትምህርታቸውን በሚገባ ሲከታተሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዛሬው ዕለትም ለምረቃ በቅተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት ዶ/ር ውብዓለም፤ በቀጣይ ተማሪዎች የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ በስፋት እንሰራለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ ማዕከሉ የሳይንስ ዕውቀትና ዝንባሌ ያላቸውን ወጣት ተማሪዎችን ከንድፈ ሃሳብ በተጨማሪ በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰልጣኝ ተማሪዎች ነገ የፈጠራ እና ሳይንስ ባለቤት እንድትሆኑ የሚያስችላችሁን ተግባር ተኮር ዕውቀትና ክዕሎት በመቅሰማችሁ እድለኞች ናችሁ ሲሉም ተናግረዋል ዶ/ር መስፍን።
ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማር እና ፈጠራ ስራ መጎልበት በቀጣይም በተለየ መልኩ እገዛ ያደርጋል ሲሉም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ለሰልጣኞቹ ሁሌም ራዕይ ኖሮን የሳይንስ ልማት እውን እንዲሆን ሁላችንም በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ለውጥ ማምጣት ካለብን ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ዘርፉን በሰው ኃይልም ሆነ በግብዓት በመደገፍ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ዓመት በተለየ መልኩ በርካታ ተማሪዎችን ተቀብለን ለማሰልጠን እና ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ጥረት የሚያደርጉ ተማሪዎችን ተቀብለን ለማሰልጠን ከወዲሁ ዝግጁ ነን ሲሉም ፕ/ር ታከለ ተቁመዋል።
ሰልጣኝ ተማሪዎቹ በማዕከሉ ስለነበራቸው ቆይታ እና ቀጣይ መኖር ስላለበት አግባባዊ የትምህርት እና ስልጠና ግንኙነት ላይ ለነሱት ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በማዕከሉ የሚገኘውን የተደራጀ የኮምፒዩተርና የኤሌክትሮኒክስ ላብራቶሪዎችን ጉብኝት አድርገዋል።
የWT ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ
ዌብሳይት፡ wolaitatimes.com
ቴለግራም፡ https://t.me/WolaitaTimes
WT መዝናኛ፦ https://www.facebook.com/WT-መዝናኛ-105588772237484/
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/wolaitatime/
ዩቲዩብ፡ https://youtube.com/channel/UCQy9hoOijiE8FStts2SmtXw
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/wolaitatimes/
344 views14:32