Get Mystery Box with random crypto!

አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #6 “ማት? አንተ እኔን ብትሆን ምን ታደርግ ነበር ?' አልኩት | ወግ ብቻ

አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #6

“ማት? አንተ እኔን ብትሆን ምን ታደርግ ነበር ?" አልኩት ወንድሜን የሆነውን አንድ በአንድ ከነገርኩት በኋላ።

"እኔ አንቺን ልሆን አልችልም! ኸረ ማንም አንቺን ሊሆን አይችልም! እህቴ ማንም ያንቺ ልብ የለውምኮ!! ግን አያድርገውና ባንቺ ቦታ ብሆን ታውቂኛለሽ እዛው አንድ አይኑን በቦክስ ጠብቼው ሁለት ስንቅ ታመላልሺ ነበር።" አለኝ እየሳቀ።

"ማት የምሬን ጨንቆኝኮ ነው!"

"እህቴ ? " አለኝ ..... አለው የሆነ የሚያየኝ አስተያየት .... የስስት ዓይነት! በስሜ ጠርቶኝ አያውቅም። 'እህቴ' ነው የሚለኝ።

"ያለሽ እውነቱን ነው። ካንቺ የተሻለ ምክንያታዊ ሆኖ የሚወስን ሰው እኔም በአቅራቢያዬ አላውቅም! የሆነማኮ እነእማዬ ከእኔ ተደብቃው ያስተማሩሽ ጉብዝና አለ"

"አያድርገውና ብትሞትስ?" አልኩት

"ብትሞት ነው ወይስ ብትድን ይበልጥ ያስፈራሽ?"

"ማለት? "

"ማለትማ ገብቶሻል! ቅድም ከባባ ጋር ስትሆኚ የነበረውን አይቻለሁ። ውስጡ ካለነው በአንድ ጣት የማንሞላ ሰዎችሽ ውጪ ማንም እንዳይገባበት ደራርበሽ ያጠርሽውን አጥር ዘው ብሎ ገብቶብሻል። ያን አጥርሽን ሲያልፉ .... ስስት አታውቂም ነፍስሽንም : ያለሽንም ትሰጫለሽ! ከዛ ሲሄድብሽ ያለውን መሰበር ትፈሪዋለሽ!"

እሱ ክሽን አድርጎ በቃላት ሲያስቀምጠው የሆነ ያሳከከኝን ቦታ በትክክል ያገኘው 'አዎ !...እሱጋ' የሚያስብል አይነት ስሜት ተሰማኝ። የገለፀበት መንገድ ገርሞኝ

"አይገርምም! ፈሪ አድርጎኛል!" አልኩኝ

"እሱ ነው ፈሪ ያደረገሽ? እሱም በግድ አጥርሽን አልፎ አይደለም ውስጥ ያገኘሽው? ስታውቂው ውጣልኝ የማትዪበት ደረጃ ደርሶ አይደለም የተቀበልሽው? አስቢው እህቴ? መቼ ነው ከቤተሰብ ውጪ ለመጨረሻ ጊዜ ጓደኛ ኖሮሽ የሚያውቀው? ከአቢ በኋላ ሁሌም እንዲህ ነበርሽ። "

አቢ የአባዬ ታናሽ እህት የአክስቴ ልጅ ናት። እሷ እኛ ቤት ከመምጣቷ በፊት ምን ዓይነት ልጅ እንደነበርኩ አላስታውስም። አክስቴ በልጅነቷ ከትዳር ውጪ ነበር የወለደቻት። ጣሊያን ቪዛ አጊንታ ስትሄድ አቢ እኛ ቤት ስትመጣ 14 ዓመቴ ነው። በወራት ነበር የምትበልጠኝ። እህትም ጓደኛም አገኘሁ። እኔ የምማርበት ትምህርት ቤት ገባች። ለአራት ዓመት ከእርሷ ተለይቼ የሄድኩበትን ቦታ፣ ከእርሷ ተለይቼ የበላሁትን ምግብ፣ ሰምቼ ወይ አድርጌ እሷ የማታውቀው ነገር አላስታውስም። ውጤት አምጥተን የተለያየ ዩንቨርስቲ ሲደርሰን አይኖቼ እስኪፈርጡ አለቀስኩ። በዚህ መሃል እናቷ መጣች። እናቷ ስትመጣ በተደጋጋሚ ከእናቷ ጋር ለብቻ ማሳለፍ ሲጀምሩ የምሰራው ጠፋኝ። እሷ ሳትኖር ምንድነበር የማደርገው? ማሰብ አቃተኝ። የሆነ ቀን ግራ ሲገባኝ እማዬጋ ሱቅ ሄጄ ዋልኩ። ስመለስ አቢ አልነበረችም። ሻንጣዋን ይዛ ሄዳለች። ቻው እንኳን አላለችኝም። አባዬና ማት ሳሎን ቁጭ ብለው ነበር።

"አቢስ?" አልኩኝ

"አቢ ከእናቷ ጋር ሄዳለች!" አለኝ አባዬ

"ልታድር? " አልኩኝ ማደሯ እየከፋኝ

"አይደለም ልጄ! ተመልሳ አትመጣም! ከእናቷ ጋር ወደውጪ ሄዳለች። ዛሬ ነው በረራቸው !" አለኝ ምንም እንዳልሆነ ቀለል አድርጎ።

ያውቁ ነበር እንደምትሄድ። ራሷ ትንገራት ብለው ነበር ዝም ያሉኝ። እሷ ልትነግረኝም ..... ቻው ልትለኝም ግድ አልሰጣትም። ማልቀስ እየፈለግኩ ግን አላለቀስኩም። ዝም አልኩኝ። ለቀናት ዝም አልኩኝ። ለእኔ ብዙ ነገሬ ናት ብዬ ለማስባት ሴት ለሷ ምኗም አልነበርኩም ብዬ ሳስብ ልቤን ክብድ ይለኛል። እኔና እሷ የምንቀመጥበት የነበረ ካፌ ብቻዬን ቁጭ ብዬ 'የምሯን ነው ግን? አብረን የሳቅነውን፣ ያለቀስነውን፣ አብረን የሰራነውን ተንኮል፣ የተማከርነውን ....የምሯን ረስታው ነው?' እላለሁ። ከወር በኋላ ደውላ

"ቻው ያላልኩሽ ፈርቼሽ ነው!" ከማለት የተሻለ ማብራሪያ እንኳን አልሰጠችኝም። በቃ ህይወቷን ቀጠለች። እኔ ግን ጎደለችብኝ። የሆነ ቀን ከቤት ደወልኩላት። ከኢትዮጵያ ጣሊያን! በቅጡ ሰላም እንኳን ሳትለኝ "ፌቪዬ ልወጣ ስል ነው የደወልሽው እደውልልሻለሁ!" ብላ ዘጋችው። የእኔ በህይወቷ መጉደል ቁርስ የመዝለል ያህል እንኳን ሳይከብዳት ህይወቷን ቀጠለች:: ..... ጠበቅኳት። የሆነ ቀን 'ናፈቅሽኝ' ትለኛለች ብዬ ...... የሆነ ቀን የሄደችበት ሀገር የገጠማትን ልታወራኝ መልሳ ትደውላለች ብዬ ........ ጊቢ ሸበላ ወንድ አይቼ እንደው ደውላ ታበሽቀኛለች ብዬ ....... ቢያንስ ለልደቴ እንኳን አትረሳኝም ብዬ ......... ከዓመታት በኋላ ወደሀገር ቤት እስከተመለሰችበት ጊዜ ድረስ አልደወለችም። .....

"የህይወት አንዱ አካል ነው። ሰዎች ወደ ህይወትሽ ይመጣሉ ይሄዳሉ። የሆነው መንገድሽ ላይ መቀበልንም መሸኘትንም መልመድ የለብሽም?" አለኝ ማት በሀሳብ መጋለቤን እያስተዋለ። ስልኬ ሲጠራ አየውና በጥያቄ አየኝ

"ባክህ ባለመኪናው ነው። የገጫት!" አልኩት ግሩም የሚለውን ሲያይ ሌላ ነገር አስቦ እንደሆነ እየገባኝ።

"እኔ ተናግሪያለሁ!" አለኝ በተንኮል። ስልኩን አነሳሁትና ግሩም ሊያገኘኝ እንደሚፈልግ ነግሮኝ ልጄ ከትምህርት ቤት ከተመለሰች በኃላ ባባን ለሷ ትቼው ልንገኛኝ ተቀጣጥረን ዘጋሁት።

"አባቷ ምንም አድርጎ ቢሆን እውነቱን እንዳለ ማወቅ አለባት። ሳይዘገይ ብታውቅ ደግሞ ጥሩ ይመስለኛል።" አለ ማት ግሩም ስለአሸናፊ ሊነግረኝ በአካል ቢሆን ይሻላል እንዳለኝ ስነግረው።

"አውቃለሁ። ግን..."

"አንቺ አለሽላት ምንም አትሆንም! እያወቅሽ እንዳልነገርሻት ከምታውቅ እውነቱ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን እሱን ብታውቅ ይሻላል። "

ማት ቤቴን ለቆ ከወጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ባባ ከእንቅልፉ ነቅቶ አጠገቤ መጣ። አይኖቹን እያሻሸ በቅጡ ሳይገልጥ የተቀመጥኩበት ሶፋ ላይ እግሮቹን አውጥቶ ጭንቅላቱን ጭኔ ላይ አስደግፎ ተጋደመ። ልምድ እንደሆነ ነገር ........ ብዙ ጊዜ አድርጎት እንደሚያውቅ ነገር.......ለቀናት ሳይሆን ብዙ ጊዜ እንደሚያውቀኝ ነገር። ሳላስበው ፈገግ አልኩ።

ሊሄድብኝ እንደሚችል እያወቅኩም ቢሆን ያለስስት ልወደው፣ ልጠብቀው፣ የእኔ እስከማይሆን ቀን ድረስ የእኔ ላደርገው ለራሴ ቃል ገባሁ። ቀኑ ደርሶ ትቶኝ ሲሄድ አምኜ እቀበላለሁ! አልኩ። ልጄ ስትመጣ እዛው እግሬ ላይ እሱ እንቅልፍ ወስዶት በተቀመጥኩበት ሶፋውን ደገፍ ብዬ ሸለብ አድርጎኝ ነበር።

"ነፍስ አጥፍቶ ነው!" አለኝ ግሩም አንዱ ካፌ በተቀመጥንበት ሊነግረኝ ሲታሽ ቆይቶ!

"አሸናፊ በሌላ በምንም ሊታሰር ይችላል። ነፍስ ማጥፋት? በፍፁም!" አልኩኝ የሰማሁትን እንኳን ለማብሰልሰል ሰከንድ ሳልወስድ እርግጠኛ ሆኜ :: መደንገጥ ነበር የነበረብኝ አይደል? እንደዛ አይደለም የተሰማኝ

"እኔ እንጃ! ሰዎች እኮ ይቀየራሉ! አንቺ የምታውቂው ሰው ላይሆን ይችላል አሁን"አለኝ

"ትናንት ያየሁት አሸናፊ ምንም አልተቀየረም! የዛሬ 15 ዓመት የማውቀው አሸናፊ ነው።" ካልኩት በኋላ ነው ዓይኖቹን አፍጥጦ በመገረም ሲያየኝ ስለእኔና ስለአሸናፊ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ያስታወስኩት።

"የልጄ አባት ነው!" ካልኩት በኋላ ለማስረዳት ብዙ እንደሚፈጅ ሲገባኝ ተውኩት። እሱም አልጠየቀኝም። "እሺ ስንት ዓመት ነው የተፈረደበት? "

"አስራ አራት"

"በፍፁም እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ አሸናፊ እንኳን ሰው ለመግደል ለጥፊ እጁን አያነሳም።"

"እኔ ስለማላውቀው ምንም ልልሽ አልችልም ሰዎች ግን አይደለም በ15 ዓመት በ15 ቀን ሊቀይራቸው የሚችል አጋጣሚ ይፈጠራል።"

"ሟች ምን አይነት ሰው ነው? መረጃ አለህ?"