Get Mystery Box with random crypto!

✞________«ሰው እናታችን ጽዮን ይላል»________✞ «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፥ ወብእሲ ተወ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

✞________«ሰው እናታችን ጽዮን ይላል»________✞
«እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፥ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ፤ ወውእቱ ልዑል ሣረራ። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጧም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።» ይላል። መዝ ፹፮፥፭። ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን እናት ብሏታል። እናት፦ ወላጅ፥ መገኛ፥የአባት ሁለተኛ ናት። እግዚአብሔር በአሠርቱ ትእዛዛት፦ «አክብር አባከ ወእመከ፤ ከመ ይኩንከ ጽድቀ፥ ወይኑኅ መዋዕሊከ በውስተ ምድር ዘይሁበከ እግዚአብሔር አምላክከ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ (ቸርነቱ ረድኤቱ ይደረግልህ ዘንድ) ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚስጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም፤ » እንዳለ፦ እናት ከአባት እኲል ክብር ይገባታል። ዘጸ ፳ ፥፲፪። ጽዮን ማለት ደግሞ አምባ መጠጊያ ማለት ነው።
ጽዮን ማርያም ፤
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «ጽዮን» ተብላ ትጠራለች። ምክንያቱም ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት እንደ ሆነ ሁሉ እመቤታችንም፦ ለነፍስና ለሥጋ ፥ለኃጥአንና ለጻድቃን፥ አምባ መጠጊያ ናትና። ቅዱስ ዳዊት፦ «እስመ ኀረያ እግዚ አብሔር ለጽዮን ፥ ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ ፥ ዛቲ ይእቲ ምእራፍየ ለዓለም፤ ዝየ አኅደር እስመ ኅረይክዋ። እግዚአብሔር ጽዮን መርጧታልና ፥ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» ያለው እመቤታችንን ነው። መዝ ፩፻፴፮ ፥ ፲፫። ምክንያቱም ፦ ለእናትነት መርጦ ያደረው በእርሷ ማኅፀን ነውና። «ለ ዘላለም መረፊያዬ ናት፤» ማለቱም፦ እርሱ የዘለዓለም አምላክ እንደሆነ ፥ እርሷም ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ተብላ እንደምትኖር የሚያመለክት ነው። በሌላ ምዕራፍም፦ « ደብረ ጽዮን ዘአፍቀረ ፥ ሐነፀ መቅደሶ በአርያም ፥ወሳረረ ውስተ ምድር ዘለዓለም። የወደ ደውን የጽዮንን ተራራ ፥ መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ። ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።» ብሏል። መዝ ፸፯፥፷፰።
ጽርሐ አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንዱ ነው። በዚያ፦ ኪሩቤል የሚሸክሙት ፥ ሱራፌል የሚያጥኑት የእግዚአብሔር የእሳት ዙፋን አለ። ዙፋኑም በሰባት የእሳት መጋረጃዎች የተጋረደ ነው። ኢሳ ፮፥፩ ፣፪ኛ ሳሙ ፬፥፬ ፣ ሕዝ ፩፥፭-፲፰ ፣ ራእ ፬፥፮-፱። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «በሰማይ ባለ ጽርሐ አርያም ፈንታ በምድር ላይ አርያምን ሆንሽ፤» ብሏታል። ከ ዚህም፦ ቅዱስ ዳዊት «የወደደውን የጽዮንን ተራራ፥ መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፤» ያለው ለእመቤታችን እንደሆነ እንረዳለን።
ድንግልናዋን በተመለከተም፦ «ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፥ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጸዮን ፥ እስመ አጽንዐ መናግሥተ ኆኃትኪ ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ፥ ጽዮንም ሆይ አምላክሽን አመስግኚ ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፤» ብሏል። መዝ ፩፻፵፯፥፩። ይህም ፦ ለጊዜው ለከተማይቱ ሲሆን ለፍጸሜው ለእመቤታችን ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ፥ ጽዮን ፥ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን በድንግልና በፀነ ሰች ጊዜ፦ «ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች። ልቡናዬም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች።» በማለት አመስግናለች። ሉቃ ፩፥፵፮። የእርሷ ሰውነት፦ የሥጋን ንጽሕና ፥ የልብን ንጽሕና ፥ የነፍስን ንጽሕና ፥ አስተባብራ አንድ አድርጋ ይዛ የተገኘች ናት። «የዶጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና፤» የተባለውም ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን ነው። እመቤታችን፦ ቅድመ ወሊድ ፥ ጊዜ ወሊድ ፥ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። ይኽንንም ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ፤ ወንድ ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች ፤ ስሙ ንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» በማለት ተናግሯል። ኢሳ ፯፥፲፬። ነቢዩ ሕዝቅኤልም፦ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስ ተውጭ ወዳለው በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ (ድንግል ማር ያም ለዘለዓለም በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)። ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘ ግታ ትኖራለች። (አምላክ በማኅፀኗ ተፀንሶ፥ ከእርሷ ተወልዷልና በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)።» ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪።
ደብረ ጽዮንና ታቦተ ጽዮን ምሳሌዋ የሆኑላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረላት፦ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላታል። ይህም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፥ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ ፥ ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስን፦ «እነኋት እናትህ፤» ብሎታል። ዮሐ ፲፱፥፳፭።
✞✞✞✞✞ሰናይ ሚዲያ✞✞✞✞✞

Share


https://youtube.com/channel/UCzj1rOCD7-WVTFN7VU8RmZw