Get Mystery Box with random crypto!

#መልከአ ቅዱስ ጊዮርጊስ። 1፤ ለፅንሰትከ ወለልደትከ:-ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ በአምላካችን በ | ውዳሴ ማርያም/wdasemaryam

#መልከአ ቅዱስ ጊዮርጊስ።

1፤ ለፅንሰትከ ወለልደትከ:-ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ መስቀልና በክብር እመቤታችን ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ለገጠማቸው ክቡር ፅንሰትህና ቡሩክ ልደትህ ሰላም እላለሁ።

ጊዮርጊስ ሆይ ጨካኝና ቁጡ በሆነው በዱድያኖስ አደባባይ ልዩ ልዩ ተአምራትን እንደማድረግህ። በጠዋት በማታ በከንቱ ነገር የሚነሳሱብኝ ጠላቶቼ ሁሉ እንድ አመድ በነው እንደ ጢስ ተነው ይጥፉ።

2፤ ለዝክረ ስምከ።

ጊዮርጊስ ሆይ ለስም አጠራርህና ለተቆላዘመው ለተለሸለሸው የራስ ፀጉርህ ሰላም እላለሁ ብሩህ ወጽዱል ለሆነው ፊትህና ርእስህም ሰላም እላለሁ። ተአምርኛው ሰማዕት ሆይ

አምላካዊ ሥልጣነ ኃይል የተጎናጸፍነህና። የማዳንክን መስቀል በርሴ ላይ አቀናጅ። ገድልህ ወንጌልንም በልቦናየ ሠሌዳ ላይ ጻፍ።

3፤ ለቀራንብቲከ።

ጊዮርጊስ ሆይ ዱፉላት ለሆኑት ቀራንብቶችህና ብሩሃት ለሚሆኑ አዕይንቶችህ ሰላም እላለሁ። የሮማን ከፋይ ለመሰሉት ጉንጮችህና አዕዛኖችህም ሰላም እላለሁ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የሰማዕታት ሁሉ አለቃ፤ እንደመሆንህ ቀድሞ ሰባዓ ነገሥታትን እንደደመሰስካቸው ነበልባላዊ በምትሆን ጸሎትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው።

4፤ ለአእናፊከ።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ እንደ ቀይ ሐር ፈትል (ኩብ) ለሚመስሉት ከናፍርህና አዕንፎችህም ሰላም እላለሁ። እንዲሁም ለፅዕድዋን አስናኖችህና አፍህ ሰላም እላለሁ።

ተአምረኛው ሰማዕት ሆይ፤ ቀድሞ የቢፉሞንን ልጅ ከስዕበተ ኅጢአት ሰውቱነን እንደቀደስከው መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ዕበቃ ዘንድ፤ ሰውነቴን በፍጽም መቀደስ ቀድሰው ከኃጢአት ርኳሰት ንጽህ አድርገኝ።

5 ለልሳንከ

ጊዮርጊስ ሆይ፤ የምስጋና አውታረ መዝሙር ለሆኑት ቃልህና አንደበትህ ሰላመ እላለሁ። የምስጋና ቁርባን ለሚነገርባቸው ጉረሮህና እስትንፋስህም ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ ሙታንን የማንሣት ሥልጣን ተሰጥቶሃልና። አቤቱ ቢሩታዊትን ከአፈ ዘንዶ እንደ አዳንካት እኔንም ከዕለት እኪት ከዘመን መንሱት በጸሎትህ አድነኝ።

6፤ ለክሣድከ።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ የመቆረጥና የመመተር ፍርድ ሰተፈረደባቸው መታክፎቶችህና ክሣድህ ሰላም እላለሁ ለተገረፈው ዘባንህና ለተቸነከረው እንግዳዓህም ሰላም እላለሁ።

ኃይሉ ሰማዕት ሆይ፤ እኔን ምስኪኑን አገልጋይህን ከሃይማኖት መራቆት ከምግባር እጦት ታድነኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልብሱ ተጋድሎህን በበጉ (በክርስቶስ) ደም አጥበህ ከአልውያን ቀማኞች ከከሐድያን ወንበዴዎች ጠብቀህ ክብረ ልብስህን በከብር ለመልበስ በቅተሃልና።

7፤ ለሕፅንከ።

ጊዮርጊስ ሆይ ዓሥራወ አዕዳውህን ለሚያንቀሳቅሰው ወርችህ ሰላም እላለሁ። ዳግመኛም የተአምራት መምህር ለሆነው ከንድህና እድ ከዉርናዕህ ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ትግልህ ሕይወት ሥነ ተጋድሎህም መድኃኒት ይሆነኝ ዘንድ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።

8፤ ልእመትከ።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ ልክብርተ ክንድህና ተባባሪዋ ለሆነችው መዳፍህም ሰላም እላለሁ። እንዲሁም ለጣቶችህና እንድ ዕንቍ ፊርጥ ለሚያበሩ የእጆችህም አጽፋር ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ የሰማዕታትና የጭፍሮቻቸው ሁሉ አለቃ ነህና አቤቱ በጥበብህ ከባሕረ ኅዘን አሻግረኝ በባሕር ላይ መሄድ ያልለመድ የባሕርን ጠባይ ሊያውቅ አይችልምና።

9፤ ለገቦከ።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ እንደ መስተዋት ለሚያንጸባርቀው ከርስህ ሰላም እላለሁ። ዳግመኛም እንድ ብርሌ ጽሩይ ለሆነው ልቦናህና ለመንትዮች ከ፤ ልያቶችህ ሰላም እላለሁ።

አባቴ ጊዮርጊስ ሆይ፤ በሕያው ክርስቶስ ሕያው ነህና አፈሩ ሳሩ ቅጠሉ የመዓዛው ሽታ ልቡናን ወደሚመስጠው አገርህ በአምባላይ ፈረስህ አፈናጠህ ትወስደኝ ዘንድ እማልድሃለሁ።

10፤ለኅሊናከ።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ ለውሳጣዊ ገንዘቦችህና ሃሳቦችህም ሁሉ ከቶ ችሎታ ሣይኖረኝ ደፍሬ ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ አዲሱን የወይን ድርሰት በማከታተል አጠጣኝ የኖረ የወይን ጠጅ በኔ ዘንድ አለና እኔም እኮ አዲሱን የምስጋና ውይን ጠጅ አቀርብሃለሁ።

11፤ ለሐቌከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ ለተከበሩት አቍያጾችህና ጽኑዕ ለሆነው ወገብህ ሰላም እላለሁ። ከሁለቱ አእጋሮችህም ጋር ለአብራኮችህ ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማአዕት ሆይ፤ የምክርና የጥበብ መገኛ ነህና ከዚህ ዓለም የጨለማ ጻዕር ጋር በኃይለ ጸሎትህ ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ሰማያዊት ጉባዔ አሳርገኝ።

12፤ ለስኳንዊከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይል፤ ከሁለቱ ተረከዞችህ ጋር ለጫሞችህ ሰላም እላለሁ። እንደከበረ ዕንቍ ለሚያበሩት ለእግር ጽፍሮችህና ጣቶችህም ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ ደቁን ምሰሶ በማለምለም ተአምራትህን ገልጸሃልና። ከጽኑ መከራ በጸሎትህ አድነኝ። ሰውን ለሥድቃይ የሚዳርጉ ረኅብ ቸነፈር ከእሱ ይፈልቃሉና።

13፤ ለቆምክ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የዘምባባ በቀልት ለሚመስለው ሥነ ቆምህ ሰላም እላለሁ። እንዲሁም ለሥነ መልክእህና ለፀዓተ ነፍስህ ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ጊዮርጊስ ሆይ፤ የማስተዋልና የጥበብ መከታ ነህና። ደመና ዝናማትን እንደሚያዘንም ፍጹም የሆነ የሕይወት መንፈስ ከፈጣሪ ዘንድ ላክልኝ።

14 ለግንዘት ሥጋከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ መካነ መቃብሩ በልዳ አገር ለሚገኘው ግንዘተ ሥጋህ ሰላም እላለሁ።

ከድንግል ማርያም ፍልሰት ጋር ለሚተባበረው ፍልሰትህም ሰላም እላለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ የእልፍ አዕላፍ ጭፍራ ኃይል አለቃ እንደመሆንህ መጠን። ኅብረ መልኳ መስታወት፤ ጠፈሯ መብረቅ ወደ ሆነው ብርሃናዊት አዳራሽህ በረዴትህ ነጥቀህ ወደዚያ አስገባኝ።

15፤ አኮ አኮ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ መጻሕፍትንና ድርሳናትን በማብዛት ሳይሆን በጥቂት ቃላት ብቻ የአፍ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።

ተአምር ሠሪው ሰማዕት ሆይ፤ ፈዋሴ ዱያን እንደመሆንህ ከወፍ በሽታ ፈውሰህ የምታድን ነህና ልመናዬንና ጸሎቴን ዘወትር ቸል ሳትል ስማኝ ከሱ በሺ የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ነገሮች ይተላለፋሉና።

16፤ ሰላም ለከ።

የልዳው ጊዮርጊስ ሆይ፤ ለአንተ ሰላምታ ይገባል። ፈረሰኛው ጊዮርጊስ ሆይ፤ ሰላምታ ይገባሃል።

የተወደደው የልጅዋ የኢየሱስ ክርስቶስና የድንግል ማርያም ዕውነተኛ ምስክር ሆይ፤ ሰላምታ ይገባሃል። የጥበብ መገኛዋ አዳራሽ ሆይ፤ ሰላምታ ላንተ ይገባሃል።

17፤ ሰላም ለከ።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ልዩ ልዩ ሥቃዮችን የታገሥህ ጊዮርጊስ ሆይ ሰላምታ ይገባሃል። ሥጋህ ለዓራት ለስድስት ክፍል የተከፋፈለው ጊዮርጊስ ሆይ፤ ናርዶስ ከሚባል የሽቱ አበባ ይልቅ መዓዛህ ይጥመኛልና ሰላምታ ይገባሃል።

18፤ ሰላም ለከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ ጥበብ አሳደገችህ፤ ማደሪያዋም አደረገችህ፤ በተሰጠህም ቃለ አእምሮ በሴትየዋ ያደረገውን ጸላዔ ሠናይ አስወጥትህ ሰደድክ። ጊዮርጊስ ሆይ፤ ስለዚህም ስመ መንታ ተባልክ።

19፤ ሰላም ለከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የመታሰቢያህ ዜና እጅግ ለሚጥመው ፈጽሞም ለሚያምረው ሰላምታ ይገባል። ጼና መዓዛህም ከዱር አበቦች ሽታ ይልቅ የጣፈጠ ነው። ጊዮርጊስ ሆይ ዕንቈ ባሕርይ ነህ እኮን።

20፤ ሰላም ለሀገሩ።

ስለቀናችው ሃይማኖት ነፍስህን አሳልፈህ የሰጠህ ጊዮርጊስ ሆይ፤ ሰላምታ ይገባሃል።

ጊዮርጊስ ሆይ፤ በልዩ ልዩ ቅመም ተቀምሞ ከሚሠራ ሽቶ ይልቅ በብዙ ዋጋ የማይገኝ መዓዛው የጣፈጠ ሽቱ አንተ ነህ።

21፤ሰላም ለከ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ፤ የዘምባባ በቀልት ለሚመስለው ሥነ ቆምህ ሰላም እላለሁ።