#ነሐሴ_26 #አቡነ_ሃብተ_ማርያም_ጻድቅ እኒህ ጻድቅ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው:: "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው:: ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል:: ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች:: በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ ምጽዋትን ወዳጅ ቡርክት ሴት ነበረች:: እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር:: ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማሕጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች:: ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ 7 አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች:: ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕጻን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ:: ይሕችን ጸሎት በሕጻን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር:: የ5 ዓመት ሕጻን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል:: ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ:: ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:: የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል:: ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ት/ቤት ገብተው መጻሕፍትንም አጥንተው መንነዋል:: በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በሁዋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም:: ባሕር ውስጥ ሰጥመው 500 ጊዜ ይሰግዳሉ:: በየቀኑ 4ቱን ወንጌልና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያሉ:: (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው) በ40 ቀናት ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ:: ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው:: በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ:: (ካህን ናቸውና) ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ:: በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን መከፋትን አላሳደሩም:: በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር:: ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በሁዋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከተትሎ መጥቶ አላቸው:: "1.ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ 2.ስለ ምናኔሕ 3.ስለ ተባረከ ምንኩስናህ 4.ስለ ንጹሕ ድንግልናህ 5.ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ 6.ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ 7.ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን እሰጥሃለሁ::" "በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን 500 የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ አማንየ! በርእስየ! ብዬሃለሁ" አላቸው:: ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: በዝማሬም ወሰዷት:: አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን ክብራቸውን: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን:: ወስብሐት ለእግዚአብሔር @wdasemaryam 2.6K views✥ድንግል ሆይ ሁሉን ከሚያስብ ሁሉን ከማይዘነጋ ከልጅሽ አሳስቢ✥, 08:44