Get Mystery Box with random crypto!

የከንቲባው ልጅ ክፍል 2 ደራሲ ተስፋዬ በትሩ . . . . እቅፌ ውስጥ ሆና ስታለቅስ ደረቴ | ጦብያ💚💛❤️

የከንቲባው ልጅ

ክፍል 2

ደራሲ ተስፋዬ በትሩ
.
.
.
.
እቅፌ ውስጥ ሆና ስታለቅስ ደረቴ ላይ እምባዋ እንደ ጅረት ይፈስ ነበር ። የሷ እንደዛ ማልቀስ ሲገርመኝ ፡ የኔም እምባ ከየት መጣህ ሳይባል ጀርባዋ ላይ ዱብ ዱብ እያለ አጃዒብ አስባለኝ ። ቃል ሳታወጣ ስሜት ማጋባት ትችልበታለች ። በጣም እንደተጎዳች ታስታውቃለች ። ችግሩ ግን የማይሆን ሰው ላይ መውደቋ ነው ። እኔ እንኳን የሰውን ችግር ልቀርፍ ይቅርና ፡ የራሴንም የራሱ ጉዳይ ብዬ የተውኩ ሰው ነኝ ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም ፤ ብቻ እንደ ተቃቀፍን ደቂቃዎች ተቆጠሩ ። በኔ ፍቃድ ተላቀቅንና 'እሺ እቤት ላድርስሽ ...? የት ነው መሄድ የምትፈልጊው ...?' ስላት ፡ "ብቻዬን እዛ ቤት መሄድ አልፈልግም" አለችኝ እና ድጋሜ እቅፌ ውስጥ ገብታ ማልቀስ ጀመረች ። አሳዘነችኝ እና ድንገት ሳላስበው 'አያሳስብም ፡ አብረን እንሄዳለን' አልኳት ። "ያሉት ከሚጠፋ ... " ። መኪናዋ ውስጥ ገብተን ፡ መሪውን ወደ ዋላ አዙራ ፡ ሄጄ ወደ ማላውቅበት ሰፈር ወሰደችኝ ። ድሬዳዋ ከመጣሁ በዚህ በ2 ዓመት ውስጥ ፡ እንደዚህ አይነት ቤቶችን አይቼም አላውቅም ። ሲመስለኝ የሀብታሞች ወይንም የባለስልጣናት ሰፈር ይመስለኛል ። ይህን ሰፈር አልፈን ትንሽ ደቂቃ እንደሄድን ፡ ጭር ያለና ብዙም ሰው የሌለበት ፡ በዛላይ ምንም ሰፈር የሌለበት ቦታ ደረስን ። ግን መኪናው ውስጥ ሆኜ አንድ ቤት ይታየኛል ። መኪናውን በሩ ፊትለፊት አቁማ ፡ "ደርሰናል ፡ እንውረድ" አለችኝ ። የቤቱ አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ ካየዋቸው ለየት ያለና ያልተለመደ አይነት ነበር ። ጥበቃ የለውም መሰለኝ ፡ እራሷ የውጪውን በር ከፍታ ፡ መኪናዋን ጊቢ ውስጥ አቆመች ። እየመሸ ስለሆነ ብዙ ነገሩ እንደ ልብ አይታይም ። "ና ፡ አትፍራ ፡ እንደ ቤትህ እየው" ስትለኝ ፡ በልቤ ውስጥ 'አሜን' አልኩኝ ። እንደዚህ አይነት ቤት ስገባ የመጀመሪያዬ ነው ። ማን ያውቃል ምናልባትም የመጨረሻዬም ሊሆን ይችላል ። ወደ ሳሎን ቤቱ መራችኝና ሶፋ ላይ እንድቀመጥ በእጇ ጋበዘችኝ ። "ሚጠጣ ምን ላምጣልህ ...?" ብላኝ ፍሪጅ ከፈተች ። አይኔ በቅድሚያ ፍሪጁ ውስጥ ወዳለው ቢራ ላይ ቢያርፍም ፡ ጨዋ ለመሆን ያክል ፡ 'ኮካ አርጊልኝ' አልኳት ። ለኔም ለራሷም ኮካኮላ ከፍታ ፡ ፊትለፊቴ ባለው ሶፋ ላይ ተቀመጠች ። በሁኔታው ግራ እንደተጋባሁ ስለተረዳች ፡ በራሷ ተነሳሽነት ታሪኳን እና ቅድም እኔላይ ስላሳየችው ነገሮች ልትነግረኝ ተዘጋጀች ። "እየውልህ የኔ ወንድም ፡ በመጀመሪያ ስለ ሁሉም ነገር በጣም ይቅርታ እሺ ፤ ስሜታዊ ሆኜ ስለነበር ነው ። በዛላይ የት መሄድ እና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ በገባኝበት ሰዓት ነው አንተን በመኪናዬ ውስጥ ያየሁክ" ብላ ታሪኳን ጀመረች ። "እናቴን አይቻት አላውቅም ፡ ያኔ ገና ስወለድ ነበር ያጣዋት ። የኔ ህይወት እንዲተርፍ ፡ የሷ ማለፍ ነበረበት ። ያኔ እንዳሁኑ በየቦታው ሆስፒታሎች ከመሠራታቸው በፊት ብዙም አልነበሩም ። እኔ ስወለድ እናቴን ብዙ ደም ፈሷት ስለነበር ፡ በአቅራቢያው ደግሞ ጤና ጣቢያ ስላልነበር ፡ በፈሰሳት ብዙ ደም ምክንያት አቅም አጥታ ህይወቷ አለፈ ። ብዙዎች አግኝተው ነው የሚያጡት ። እነደኔ አይነቱ እድለ ቢስ ግን ሳያገኝ ያጣል ። እናቴ ህይወቷን ሰውታ ህይወት ስለሰጠችኝ ፡ አባቴ ህይወት ብሎ ስም አወጣልኝ ። እስካሁን አልተዋወቅንም አይደል ...? ህይወት እባላለሁ" አለችኝ እና እጇን ለትውውቅ ዘረጋችልኝ ።
'ተስፋዬ እባላለሁ' አልኳት የዘረጋችልኝን እጅ እየጨበጥኩ ። ታሪኳን ቀጠለች ፡ "አባቴ ነው ያሳደገኝ ፡ የሚገርምህ እናት እንደሌለኝ ተሰምቶኝ አያውቅም ። እንደ እናትም ፣ እንደ አባትም ፣ ሆኖ ብቻውን ያሳደገኝ እሱ ነው ። አባቴ እንደ አባት ብቻ አይደለም ፡ እንደ ጓደኛም ጭምር ሆኖ ነው አብረን የኖርነው ። ከ 1 ነገር ውጪ አንድም ነገር ከልክሎኝ እና አጉድሎብኝ አያውቅም ። በነገራችን ላይ አባቴ ባለሥልጣን ነው ፡ ያውም የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ" ስትለኝ በሆዴ 'በቃ ተስፍሼ ቁርጥህን አወቅ ፡ ነገ ወይ ከርቸሌ ፡ ወይ ሲኦል ገብተሃል' አልኩኝ ። ስታወራ አይን አይኔን እያየች ስለነበር እንደፈራሁ ገብቷት ፡ "አይዞህ አትጨናነቅ ፡ አባቴ እነደምታስበው አስፈሪ እና ቁጡ ሰው አይደለም ፤ በተቃራኒው ደግ እና አዛኝ ነው ። ደግሞም ለጊዜው ሀገር ውስጥ ስለሌለ ማንም እዚህ ቤት አይመጣም ፈታ በል"። ስትለኝ ትንሽም ቢሆን ተረጋጋሁ እና ታሪኳን እንድትቀጥልልኝ በአይኔ ምልክት ሰጠዋት ። "እንዳልኩህ አባቴ የከተማችን ከንቲባ ነው ። በዚህም ምክንያት ብዙ ችግሮች እየደረሱበት ነው ። ለጊዜው የሱን እንተወውና የኔን ጥቂት ልንገርህ ። "እስካሁን ድረስ አባቴ ስልጣን ላይ ከወጣ በዋላ ያየሁት ዘመድ ፣ ጎረቤት ፣ ጓደኛም የለም ። ከአባቴ ውጪ ቀርቤ የማውቀው ሰው የለኝም ። ብዙ ጊዜ ከቤት ስለማልወጣ ሰውን በአካል ሳይሆን በቴሌቪዥን ነው የማየው ። በአጭሩ በብቸኝነት የምሰቃይ ሴት ነኝ ። ከአባቴ ጋር ከቅዳሜ ምሽት እስከ እሁድ ሙሉ ቀን አብረን እናሳልፋለን ። ከዚያ ውጪ ግን አምስቱንም ቀናት ስራ ላይ ነው የሚያሳልፈው ። አልፎ አልፎ ደህንነቴን ለማወቅ ካልሆነ በስተቀር እዚህ አይመጣም ። በስልክ ግን በየሰዓቱ እናወራለን ማለት ይቻላል ። ቢያንስ በቀን #5 ጊዜ እንደዋወላለን ። ሰሞኑን ግን ምን እንደሆነብኝ እንጃ ከደወለልኝ ድፍን #3 ቀን ሞላው ። አሜሪካን ሀገር አስተካክዬ የምመጣው ነገር አለኝ ብሎ ነበር ከ #5 ቀን በፊት የሄደው ። የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ቀናት ደውሎልኝ በሰላም አውርተን ነበር ። ከዛ በዋላ ግን ስለሱ የማውቀው ምንም ነገር የለም ። በዚህ ጉዳይ በጣም ስለተጨነኩ እና ቤቱ ያለወትሮው ሊበላኝ ስለደረሰ ነበር ከዚህ ቤት ለመውጣት ያሰብኩት ። ግን የት መሄድና ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላወኩም ። በዛ መሀል ነበር አንተን በመኪናዬ ውስጥ ያየሁክ ። ሳይክ በቃ ፡ ዘመዴን ያገኘሁ ነበር የመሰለኝ ። ለዛም ነው ቅድም እንደዛ ያለቀስኩብህ ። ብቻዬን እዚህ ቤት ውስጥ ያሳለፍኩትን የብቸኝነት ስቃይ ከኔና ከፈጣሪ ውጪ ማንም አያውቅም ። በቲቪ ብዙ ፊልሞችን ሳይ ነፃነታቸውን አይቼ እቀናባቸዋለው ። አባቴ በስራው ምከንያት ስለሚጠነቀቅልኝ ፡ ሰራተኛም ፣ ጥበቃም የለንም ። ከሱ ውጪ ይሄን ቤት የሚያውቀው ሰው ያለም አይመስለኝም ። በተረፈ መኪና መንዳት እና ምግብ ማብሰል አባቴ በስርዓት አስተምሮኛል ። ሲጀምር ብዙም የምግብ ፍላጎት ስለሌለኝ ያን ያክል አያስጨንቀኝም ። ስራዬ ሁሉ ቲቪ ማየት ፣ መፅሐፍ ማንበብ እና መተኛት ብቻ ነው ። ይሄ ሁሉ የሆነው እንግዲህ የዛሬ #4 ዓመት አካባቢ ልክ አባቴ ወደ ስልጣን እንደመጣ ነው ። ትምህርቴንም አቋርጫለሁ ፤ አሁን እንደምታየኝ በልጅነቴ የቤት እመቤት ሆኜ ቀርቻለሁ" ። ብላኝ በድንገት ከሶፋው ላይ ብድግ አለች ።

ይቀጥላል...

╔═══❖• •❖═══╗
          መልካም ጊዜ
╚═══❖• •❖═══╝
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅልን
❥❥__⚘_❥❥

@Saymre