Get Mystery Box with random crypto!

የቡና አቅራቢና ላኪዎች ባለፉት ሳምንታት በመዲናዋ ቡና በጫኑ መኪኖች ላይ የደረሰው ዘረፉ እንዳሳሰ | TIKVAH-MAGAZINE

የቡና አቅራቢና ላኪዎች ባለፉት ሳምንታት በመዲናዋ ቡና በጫኑ መኪኖች ላይ የደረሰው ዘረፉ እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

በቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ላኪዎችና አቅራቢዎች ከተለያዩ አከባቢዎች በጭነት መኪና ተጓጉዘው ወደ ውጭ በሚላኩ ቡናዎች ላይ በአዲስ አበባ አልፎ አልፎ እየተከሰተ ያለው ስርቆት ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ገልጸዋል። ይህ ስጋት ባለፉት ሳምንታት ሶስት ቡና የጫኑ መኪኖች ከተዘረፉ በኋላ የተፈጠረ ነው።

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ እያንዳንዳቸው በአማካይ 61 ኪሎ ግራም ቡና የያዙ፤ 300 ጆንያ ቡና የጫነ መኪና የቃሊቲ ጉምሩክ ኬላን ካለፈ በኋላ መዘረፉ ተገልጿል። ይህ 11 ሚሊየን ብር ያወጣል ተብሎ የሚገመተው ቡና መነሻው ከሲዳማ ክልል ቤንሳ ወረዳ ነበር።

መኪናው ቡናውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በአዲስ አበባ በተዘጋጁ መጋዘኖች ለማራገፍ በመንገድ ላይ ነበር። ከጥቂትም ሳምንታት በፊትም እንዲሁ ሁለት ተጨማሪ የጭነት መኪናዎች የቡና አቅራቢዎች እና የቡና ላኪ መኪኖች ላይ ተመሳሳይ ዝርፊያ ተከስቷል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ በሦስት የጭነት መኪናዎች ላይ የተፈጸመው ዘረፋ ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል። የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር መሥሪያ ቤታቸው የቡና ስርቆት ሪፖርቶች ከላኪዎች እንደደረሰው አረጋግጠው "እነዚህ ክስተቶች ከጀመሩ ጥቂት ሳምንታት አልፈዋል፤ እና መፍትሄ ለማግኘት ከህግ አስከባሪዎች ጋር እየሰራን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ከፍተኛ አመራር አባል እና አቅራቢ ዘረፋ ከተፈጸመባቸው ሁለቱ የማኅበሩ አባላት መሆናቸውን አንስተው በቅርቡ ስለተፈጸመው ዝርፊያ ሲናገሩ፥ "መኪናው ቡናውን ወደ አዲስ አበባ ሲያጓጉዝ ነበር። ከዚያም ሹፌሩና ረዳቱ ቃሊቲ ካለፉ በኋላ ተዘርፈናል ብለው ደወሉ።  እነሱ ወንበዴዎቹን ያውቋቸው እንደሆን ባናውቅም የሚገርመው የጭነት መኪናው ሙሉ ይዘቱ በአዲስ አበባ መዘረፉ ነው።" ሲሉ ነው የገለጹት። አሽከርካሪው እና ረዳቱ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውንም አክለዋል።

ጥቃት ከደረሰባቸው አንዱ በበኩላቸው፥ “የላላ የጸጥታ ጥበቃ ባለበት አካባቢ እንኳን ምንም አይነት ዘረፋ አልደረሰብንም። ህግ የማስከበር ስራ በተጠናከረበት እና የህግ የበላይነት በሚከበርበት አካባቢ እንዴት እንዘረፋለን ብለን እንገምት?" ብለዋል። "ቡናውን ለዓለም አቀፍ ደንበኞቼ ሸጫለሁ፤ አሁን ምን ልልክላቸው ነው?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

ዘገባው የሪፖርተር ሲሆን ዘረፋ የተፈጸመባቸው አቅራቢዎችና ላኪዎች ጉዳዩን ያስረዱት ፖሊስ ጉዳዩ ላይ ምርመራ ከመጀመሩ በፊት መሆኑን በዘገባው ጠቁሟል።

@tikvahethmagazine