Get Mystery Box with random crypto!

የደብረ ማርቆስ ሆስፒታሉ ዶክተር ማዜሊ ትዝታዎች (ዶ/ር አበበ ሐረገ-ወይን) ዶክተር ማዜሊ ኢትዮ | Medical Information- ጤና መረጃ®️🇪🇹

የደብረ ማርቆስ ሆስፒታሉ ዶክተር ማዜሊ ትዝታዎች
(ዶ/ር አበበ ሐረገ-ወይን)

ዶክተር ማዜሊ ኢትዮጵያ የገቡት ሶላቶ ሆነው በጣሊያን ጊዜ ነበር። ሀኪም ናቸው የሚል ማስረጃ ባይኖራቸውም በደብረ ማርቆስ አካባቢ ያለው ህዝብ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሚያምናቸው አዳኝ ነበሩ። ሆስፒታል በሚሰሩበት ዘመንም ብዙ ቀዶ ጥገና ያደርጉ ነበር።

ጡረታ ከወጡ በኋላ ከደብረ ማርቆስ ወጣ ብለው ክሊኒክ ከፈቱ። እዚያ በየቀኑ ለመታከም የሚመጣው ህዝብ ብዛት ለታላቅ በአል የተሰበሰበ ይመስል ነበር። በሸክም ሄዶ በእግሩ የሚመለሰው ብዙ ነበር። እኛ ሀበሻ ሀኪሞች ዶክተር ማዜሊ ባለመሆናችን እንናቅ ነበር። ዶክተር ማዜሊ ዋና መዳህኒታቸው በመርፌ የሚሰጥ ነው። ዋናው መርፌያቸው በደም ስር የሚሰጠው ካልቾ መርፌ ነበር። በሳቸው የተነሳ የጎጃም ሰው ክኒን አይወስድም ነበር። ካዘዝንለትም ሆስፒታል ግቢ በትኖት ይሄድ ነበር። እኛጋ በሽተኛ የሚመጣው ማዜሊጋ መሄድ ሳይችል ነበር ማዜሊ አማርኛ ትንሽ ቢኮላተፉም በደምብ ያውቁ ነበር። ቤታቸው መንደር ነው ሊባል ይችላል። ሚስቶቻቸው እንጂ ሚስታቸው አይባልም ነበር። ሰፈሩም ከጎረምሳ ጀምሮ እስከ ሙጭቅላ ብዙ ክልስ ልጆች ይታዩ ነበር።

ማዜሊ አይናቸውን የሙከፍቱት ዳግም ፉት በሚለት ነበር። እንዲያውም ከዳግም ሌላ ውሀም አይጠጡም ነበር። ምንም አላደረጋቸውም። ማዜሊ ድሀ በነጻም ስለሚያክሙ ተወዳጅ ነበሩ። ሁለት የሚያስቁ ነገሮች ስለ እሳቸው የሰማሁትን አጫውታችኋለሁ።

የመጀመሪያው አንዲት ሴት ኬረዳ ልጃቸውን ማዜሊ እንዲመረምሩ ይዘው ይመጣሉ። መርምረው ሲጨርሱ እናትዬዋ መቼም ወስፋት ነው በዝቶ ሆዷን የነፋት እባኮ በመዳህኒት ያውጡልኝ አሉ። ማዜሊም ልክ ኖት እሜቴ ወስፋት ነው ግን ብዙ ሳይሆን አንድ ትልቅ ነው። ዘጠኝ ወር ቆይቶ በራሱ የሚወጣ ስለሆነ ጥቂት ወራት ይጠብቁ አሏቸው።

ሁለተኛው ደሞ አንዲት ታዋቂ ሴት ሆዴን እየነፋኝ ተቸግሬያለሁና መፍትሄ ይፈልጉልኝ አሉ። ማዜሊም ሰገራ ለምርመራ ነገ ይዘሽ ነይ አሉ። ሴትዮዋ በማግስቱ በፎጣ የተጠቀለለ ትልቅ እቃ በሰራተኛ አሸክመው መጡ። ላቦሬቶሪ እዚህ ይስጡ ነው የተባሉት ቢሏቸው ዶክተር ሊያዩት ነው ያዘዙኝ እንጂ ለናንተ መጫወቻ አይደለም አሉ። ተራቸው ደርሶ ዶክተር ማዜሊጋ ገቡ። ማዜሊንም ያሉኝን አምጥቻለሁ ክፈቺው አሉ። ሲከፈት ትልቁ ፖፖ በሰገራ ሞልቷል። ዶክተር ማዜሊም አፍንጫቸውን ይዘው ፣ ይሄን ሁሉ ባንድ ሌሊት ነው የሰበሰብሺው? ብለው ጠየቁ። ሴቲቷም በኩራት ዛዲያማ ማነው? እኔው ነኛ አሉ። ማዜሊም ይሄ ሁሉ ከወጣልሽ ተፈውሰሻል ሂጂ ቤትሽ አሏት።

(የዶክተር ማዜሊ ፎቶ አንባቢ ስለጨመረልኝ አመሰግናለሁ)

@tenamereja