Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 27 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸዉን እንደሚያጡ የጤና ሚኒስ | Medical Information- ጤና መረጃ®️🇪🇹

በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 27 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸዉን እንደሚያጡ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በኢትዮጵያ በየእለቱ ከወሊድ ጋር በተያያዘ 27 እናቶች ህይወታቸዉ እንደሚያልፍ በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ጤና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ብሩክ ሀይሉ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል። በየአመቱም 10 ሺህ ገደማ እናቶች በ እርግዝና ወቅት በሚያጋጥሙ የተለያዩ የጤና እክሎች ህይወታቸዉ ያልፋል ብለዋል።

ለሚመዘገቡት የሞት ቁጥሮች ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ ደም መፍሰስ ፣ በእርግዝና ግዜ የሚከሰት የደም ግፊትና ኢንፌክሽን ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸዉን አቶ ብሩክ ጠቁመዋል። ቅድመ እርግዝና እና ቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር አናሳ መሆኑም ለሚሰተዉ ሞት ሌላኛዉ ምክኒያት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ እ.ኤ.አ በ 2020 በተሰራ ጥናት በኢትዮጵያ ከ 100 ሺህ ወሊዶች ዉስጥ 2 መቶ 67 እናቶች በእኚሁ ምክኒያቶች ህይወታቸዉ ይቀጠፋል ብለዋል።

በአለም ጤና ድርጅት በአመቱ በተሰራ ሌላ ጥናት በአለማቀፍ ደረጃ በየእለቱ 8 መቶ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸዉ የሚያልፍ ሲሆን ይህም በየ 2 ደቂቃዉ የአንድ እናት ህይወት ያልፋል እንደማለትም ነዉ።

ከነዚህ ዉስጥ 87 በመቶ የሆነዉ ከሰሀራ በታች እና በደቡብ እስያ ባሉ ሀገራት ይመዘገባል ያሉ ሲሆን 95 በመቶ የሚሆነዉ ደግሞ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ሀገራት ነዉ ብለዋል።

#ዳጉ_ጆርናል