Get Mystery Box with random crypto!

እናመሰግንሻለን ምሳወይ አባተ እንደ ምሳወይ ያሉ ጋራና ሸንተሩን እያቆራረጡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

እናመሰግንሻለን ምሳወይ አባተ እንደ ምሳወይ ያሉ ጋራና ሸንተሩን እያቆራረጡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ህዝባቸውን የሚያገለግሉ አሉ። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ደግሞ ቢሮ ወንበር ውስጥ ተቀምጠው ህዝቡን የሚያማርሩ አሉ። መኪና የሚገባቸው እንደ ምሳወይ በእግር እየተጓዙ ህዝቡን ለሚያገለግሉ ሆኖ ሳለ፣ አንድ ሰዓት እንኳን ቢሮ ቁጭ ብለው በትክክል ህዝቡን ማስተናገድ የማይችሉ ደግሞ ዘመናዊ መኪና ይዘው በጎርፍ ውሐ ረጭተውን ያልፋሉ።

ምሳወይ በአማራ ክልል በሰቆጣ ከተማ ከ17 ዓመት በላይ የጤና ባለሙያ ሁና አገልግላለች። "Global Citizen" ስለ ምሳወይ አባተ "This Health Worker Walks 6 Hours to Vaccinate Children in Ethiopia" በሚል ይዞት በወጣው ዘገባ፣ ምሳወይ ለህፃናት ክትባት ለመሥጠት የሰቆጣን አቀበትና ቁልቁለት፣ ተራራና ሸንተረር በማቆራረጥ 6 ሰዓት በእግሯ ትጓዛለች። በሰቆጣ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ለህፃናት ክትባት ትሰጣለች። ህዝቧን ስለቤተሰብ ምጣኔ፣ ስለእርግዝና፣ ስለጡት ማጥባት እና ስለተመጣጠነ ምግብ ታስተምራለች።

ነገም በጥዋቱ ተነስታ የክትባቱን ሳጥን በትከሻዋ በማንገት የቆቦ ሰንሰለታማ ተራሮችን ትወጣለች፤ ትወርዳለች። ወደ ወገኖቿ ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ መልክዓ ምድርን ታቆራርጣለች። ከስድስት ሰዓት በላይ ትጓዛለች....ይህ ለ17 ዓመት የኖረችበት ሕይወቷ ነው።

በተለይም በጦርነቱ ምክንያት በሰቆጣና አካባቢው ከሦስት ዓመት በላይ ክትባት ተቆርጦ በመቆየቱ ከአስፈላጊም በላይ ሆኗል። ምሳወይ ለግሎባል እንደተናገረችው ጤናማ የነበሩ ህፃናት በጦርነቱ ምክንያት ተጎሳቁለዋል። በክትባት እጥረት ታመዋል። ክብደታቸው ቀንሷል። "እናም ደሞዜ ትንሽ ቢሆንም የእነዚህን ህፃናት ህይወት ለመታደግ በመሆኑ በሥራዬ ደስተኛ ነኝ። የኔ ትልቁ ክፍያ የህፃናቶችን ሕይወት መታደግ ነው" ትላለች።

እንግዲህ ኢትዮጵያ እንደ ምሳወይ የሚያገለግሏት አሉ። እንደማትነጥፍ ላም እያለቧት የሚኖሩም አሉ። ሀቀኛ ነጋዴዎች አሉ፤ ፣ ከተመኑ በላይ አንድን ዕቃ አስወድደው የሚሸጡም አሉ። ንፁህ ወተት የሚሸጡ አሉ፤ በወተቱ ላይ ውሐ ጨምረው የሚሸጡ አሉ። በተመሳሳይ በቅቤ ላይ ለውዝ፣ በዱቄት ላይ ሳጋቶራ፣ በማር ላይ ስኳር ጨምረው የሚሸጡ ለማኅበረሰቡ ጤና የማይጨነቁ አሉ። ከታሪፉ በላይ የሚያስከፍሉ ሹፌሮች፣ ጉቦ ተቀብለው በንፁሃን ላይ የሚፈርዱ ዳኞች፣ ገንዘብ ተቀብለው በሀሰት የሚመሰክሩ፣ የሥራ ቅጥር ሲወጣ ገንዘብ ተቀብለው የሚቀጥሩ አሉ።

እንደ ምሳወይ በማለዳ ተነስተው ለሥራ የሚጓዙ አሉ፤
ዘግይተው ወይንም ሰዓቱ ሳይደርስ ቀድመው ከቢሮ የሚወጡ አሉ። እንደ ምሳወይ ደሞዝ በቅጡ ሳይከፋላቸው ባልተመቻቸ ሁኔታ ማኅበረሰባቸውን እንደ ሻማ እየቀለጡ የሚያገለግሉ አሉ፣ በጆርጅ አርዌል "የእንስሳት እርሻ" ውስጥ እንዳሉት ባህርያት በሥልጣናቸው ህዝብን ከማግለል ይልቅ የሚባልጉ፣ለራሳቸው ምቾት የሚጨነቁ አሉ።


እኛ ግን እንደ ምሳወይ እና እንደሷ ላሉ ብርቱ ሠራተኞች ክብረት ይስጥልን እንላለን

ማንኛውንም ሀሳብና አስተያየት በዚህ ሊንክ መላክ ይችላሉ @Tadeletibebut